መኪናቸውን አቁመው እርዳታ አበረከቱ
ቦብ አልበርታ፣ ካናዳ ውስጥ በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር እየነዳ ሳለ የኋላ ጎማው ፈነዳ፤ አየሩ በጣም ቀዝቃዛ ነው፤ ነፋሱም በኃይል ይነፍስ ነበር። ቦብ መጀመሪያ ላይ ምን እንደተፈጠረ ስላላወቀ የቀረውን 5 ኪሎ ሜትር እየነዳ ቤቱ ለመድረስ አስቦ ነበር።
ቦብ በአካባቢው ላለው የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቀጥሎ የተከናወነውን ነገር ገልጿል፤ እንዲህ ብሏል፦ “አምስት ወጣቶችን የያዘ መኪና ወደ መኪናዬ ተጠጋ፤ ከዚያም ወጣቶቹ መስኮታቸውን ከፍተው የመኪናዬ ጎማ መፈንዳቱን ነገሩኝ። መኪናዬን ሳቆም እነሱም አቆሙና ‘ጎማህን እንቀይርልህ’ አሉኝ። ትርፍ ጎማና ክሪክ መያዜን እንኳ አላወቅኩም ነበር። መኪናዬ ሥር ገብተው ጎማውንና ክሪኩን ሲያወጡ ከዚያም ጎማውን ሲቀይሩ እኔ መንገዱ ዳር በተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ ተቀምጬ አያቸው ነበር። አየሩ በጣም ቀዝቃዛ ነበር፤ በረዶም እየወረደ ነበር። ወጣቶቹ ዝንጥ ብለው የነበረ ቢሆንም መኪናዬን አስተካክለው ጉዞዬን እንድቀጥል ረዱኝ። እነሱ ባይረዱኝ ኖሮ ይህን ማድረግ አልችልም ነበር።
“ለእነዚህ አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ። በወቅቱ በዚያ አካባቢ ወዳሉ ቤቶች ሄደው መልእክታቸውን እየሰበኩ ነበር። እነዚህ ልጆች በእርግጥም የሚሰብኩትን ነገር በተግባር ያውሉታል። ከብዙ ችግር አድነውኛል፤ ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ። በዚያ ቀን እንዲህ ያሉ ደግ ወጣቶች መንገድ ላይ አገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር።”