የይሖዋ ምሥክር መሆን የምችለው እንዴት ነው?
በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ኢየሱስ አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ሊወስዳቸው የሚገቡትን እርምጃዎች ጠቅሷል። ይህ ጥቅስ አንድ ሰው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለበት ይናገራል፤ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ደግሞ ስለ ይሖዋ መናገርን ወይም ምሥክርነት መስጠትን ይጨምራል።
እርምጃ 1፦ መጽሐፍ ቅዱስን መማር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‘እያስተማሩ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ አዟቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) “ደቀ መዝሙር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ቀጥተኛ ፍቺ “ተማሪ” የሚል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ትምህርቶች በአጠቃላይ በተለይም ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ደስተኛና አርኪ ሕይወት እንድንመራ ያስችሉናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የይሖዋ ምሥክሮች ያለ ምንም ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስተምሩህ ፈቃደኞች ናቸው።—ማቴዎስ 10:7, 8፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13
እርምጃ 2፦ የተማርከውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ። ኢየሱስ፣ የሚማሩት ሰዎች እሱ ‘ያዘዛቸውን ነገሮች ሁሉ መጠበቅ’ እንዳለባቸውም ተናግሯል። (ማቴዎስ 28:20) ይህ አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱስን የምትማረው የጭንቅላት እውቀት ለማግኘት ብቻ መሆን እንደሌለበት ያሳያል፤ ከዚህ ይልቅ የምትማረው ነገር በአስተሳሰብህና በባሕርይህ ላይ ጉልህ ለውጥ እንድታደርግ ሊያነሳሳህ ይገባል። (የሐዋርያት ሥራ 10:42፤ ኤፌሶን 4:22-29፤ ዕብራውያን 10:24, 25) ኢየሱስ ያዘዛቸውን ነገሮች የሚጠብቁ ሰዎች በራሳቸው ተነሳስተው እሱን ለመከተል ውሳኔ ያደርጋሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ሕይወታቸውን ለይሖዋ አምላክ በመወሰን ነው።—ማቴዎስ 16:24
እርምጃ 3፦ መጠመቅ። (ማቴዎስ 28:19) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠመቅ ከመቀበር ጋር ተመሳስሏል። (ከሮም 6:2-4 ጋር አወዳድር።) መጠመቅ፣ ለቀድሞ ሕይወት መሞትንና ለአዲስ ሕይወት ሕያው መሆንን ያመለክታል። በመሆኑም ስትጠመቅ ኢየሱስ የገለጻቸውን የመጀመሪያዎቹን ሁለት እርምጃዎች መውሰድህንና አምላክ ንጹሕ ሕሊና እንዲሰጥህ መጠየቅህን በሕዝብ ፊት እያሳየህ ነው ማለት ነው።—ዕብራውያን 9:14፤ 1 ጴጥሮስ 3:21
ለጥምቀት ዝግጁ እንደሆንኩ እንዴት ማወቅ እችላለሁ?
የጉባኤህን ሽማግሌዎች አነጋግር። እንዲህ ማድረግህ ሽማግሌዎቹ ጥምቀት ምን ነገሮችን እንደሚጨምር መረዳትህን፣ የተማርካቸውን ነገሮች ተግባራዊ እያደረግክ መሆኑንና ራስህን ለአምላክ የምትወስነው በራስህ ተነሳሽነት መሆኑን ለማረጋገጥ ያስችላቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 20:28፤ 1 ጴጥሮስ 5:1-3