በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ምንድን ነው?

ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ምንድን ነው?

 ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፔንስልቬንያው የጋራ ብልጽግና ሕግ መሠረት በ1884 የተቋቋመ አትራፊ ያልሆነ ኮርፖሬሽን ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ኮርፖሬሽን መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማተምን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚያከናውኑትን ሥራ ለማካሄድ ይጠቀሙበታል።

 የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ እንደሚገልጸው ኮርፖሬሽኑ ዓላማ አድርጎ የተነሳው “በሃይማኖት፣ በትምህርትና በእርዳታ” ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን ሲሆን በተለይ ደግሞ “በክርስቶስ ኢየሱስ ስለሚመራው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ወንጌል መስበክና ማስተማር” ላይ ያተኩራል። የማኅበሩ አባል መሆን የሚችሉት የተጋበዙ ሰዎች ብቻ ናቸው፤ አንድ ሰው የለገሰው ገንዘብ መጠን አባል በመሆኑና ባለመሆኑ ላይ ለውጥ አያመጣም። የኮርፖሬሽኑ አባላትና ዳይሬክተሮች የይሖዋ ምሥክሮችን የበላይ አካል ይረዳሉ።

ሕጋዊ አካላትን ማስተባበር

 የይሖዋ ምሥክሮች ከዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ በተጨማሪ በተለያዩ አገራት ያሉ ሕጋዊ ማኅበራትን ይጠቀማሉ። ከእነዚህ ሕጋዊ ማኅበራት መካከል አንዳንዶቹ “ዎች ታወር” የሚለውን ሐረግ በስማቸው ውስጥ የያዙ ናቸው።

 እነዚህ የተለያዩ ሕጋዊ አካላት ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ሥራዎችን ለማከናወን አስችለውናል፤ ለምሳሌ፦

  •   የጽሑፍ ዝግጅትና ሕትመት። እስከ አሁን 253 ሚሊዮን ገደማ መጽሐፍ ቅዱሶችን አትመናል። ጽሑፎቻችን ከ1,050 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይዘጋጃሉ። ኢንተርኔት ላይ jw.org በተባለው ድረ ገጻችን አማካኝነት ሰዎች ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዲሁም “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” እንደሚሉት ላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይችላሉ፤ እነዚህን አገልግሎቶች የምንሰጠው ያለክፍያ ነው።

  •   ትምህርት። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥባቸው የተለያዩ ትምህርት ቤቶች አሉን። ለምሳሌ፣ ከ1943 አንስቶ 10,000 ያህል የይሖዋ ምሥክሮች በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከሚሰጠው መጠነ ሰፊ ሥልጠና ተጠቀሚ ሆነዋል፤ ይህም ሚስዮናዊ ሆነው እንዲያገለግሉ ወይም ዓለም አቀፉን ሥራ እንዲያጠናክሩ አስችሏቸዋል። በተጨማሪም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች (የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑም ይገኙበታል) በሁሉም ጉባኤዎቻችን ውስጥ በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ይሰጣል። ከዚህም ሌላ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ሰዎችን የምናስተምርበት ዝግጅት አለን፤ መማሪያ መጽሐፉ ደግሞ በ136 ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል።

  •   እርዳታ። በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ እንሰጣለን። ለምሳሌ፣ በ1994 በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ እና በ2010 በሄይቲ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ሰጥተናል።

 በምንጠቀምባቸው ኮርፖሬሽኖችና ሕጋዊ አካላት አማካኝነት ብዙ ሥራዎችን ማከናወን የቻልን ቢሆንም የሥራችን ቀጣይነት በአንዳቸውም ላይ የተመካ አይደለም። እያንዳንዱ ክርስቲያን ከአምላክ የተሰጠውን ምሥራቹን የመስበክና የማስተማር ተልእኮ የመወጣት ኃላፊነት አለበት። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ሥራችንን የሚደግፈውም ሆነ ቀጣይ በሆነ መልኩ “የሚያሳድገው” አምላክ እንደሆነ እናምናለን።—1 ቆሮንቶስ 3:6, 7