የወጣቶች ጥያቄ
ከአስተማሪዬ ጋር መስማማት የምችለው እንዴት ነው?
እንደ ጦር የሚፈሩ አስተማሪዎች
ይዋል ይደር እንጂ ሁሉም ተማሪ ማለት ይቻላል የሚያዳላ፣ ከተማሪዎቹ ብዙ የሚጠብቅ ወይም ክፉ የሆነ አስተማሪ ያጋጥመዋል።
ሉዊስ የተባለ የ21 ዓመት ወጣት እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “ደስ የማይሉ ስድቦችን የምትሳደብና ተማሪዎችን የምታመናጭቅ አስተማሪ ነበረችን። ጡረታ ልትወጣ የቀራት ጊዜ አጭር ስለነበር በዚህ ምክንያት እንደማትባረር ተማምና ሊሆን ይችላል።”
የ25 ዓመቷ ሜላኒ፣ አስተማሪዋ እሷን ብቻ ነጥላ ጠምዳት እንደነበር ታስታውሳለች። እንዲህ ብላለች፦ “ታሠቃየኝ የነበረው የዋነኞቹ ሃይማኖቶች ተከታይ ስላልሆንኩ ነው። ‘ወደፊት ሰዎች ብዙ በደል ስለሚያደርሱብሽ ለዚያ እያዘጋጀሁሽ ነው’ ትለኝ ነበር።”
ከአስተማሪህ ጋር መግባባት ስለከበደህ ብቻ የትምህርት ዘመንህ በችግር የተሞላ እንደሚሆን አታስብ። እስቲ የሚከተሉትን ምክሮች ተግባር ላይ ለማዋል ሞክር፦
ሊረዱህ የሚችሉ ምክሮች
እንደ ሁኔታው ማስተካከያ አድርግ። አስተማሪዎች ከተማሪዎቻቸው የሚጠብቁት ነገር ይለያያል። አስተማሪህ ከአንተ ምን እንደሚፈልግ ለማወቅ ሞክር፤ ከዚያም በተቻለህ መጠን የሚፈልገውን ለማሟላት ጥረት አድርግ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጥበበኛ ሰው ያዳምጣል፤ ደግሞም ተጨማሪ ትምህርት ይቀስማል።”—ምሳሌ 1:5
“አስተማሪዬ የምትፈልገውን ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ፤ ስለዚህ የተሰጠኝን ሥራ ልክ እሷ ባለችው መንገድ ለመሥራት የቻልኩትን ያህል ጥረት አደረግኩ። እንዲህ ማድረጌ ከእሷ ጋር መግባባት እንድችል ረድቶኛል።”—ክሪስቶፈር
አክብሮት አሳይ። አስተማሪዎችህን በአክብሮት ለማነጋገር ሞክር። ትክክል እንደሆንክ ቢሰማህም እንኳ የአጸፋ መልስ ከመስጠት ተቆጠብ። አስተማሪዎችህ እንደ ተማሪ እንጂ እንደ እኩያ እንደማይቆጥሩህ አስታውስ፤ ደግሞም ልክ ናቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።”—ቆላስይስ 4:6
“አብዛኛውን ጊዜ ተማሪዎች ለአስተማሪዎች የሚገባቸውን ክብር አይሰጡም፤ ስለዚህ ለአስተማሪዎቻችሁ አክብሮት ለማሳየት የምታደርጉት ጥረት ለእናንተ ባላቸው አመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።”—ሲዬራ
ስሜታቸውን ተረዳላቸው። አስተማሪዎችም ሰዎች ናቸው። ልክ እንደ ማንኛውም ሰው የሚያስጨንቋቸውና የሚያሳስቧቸው ነገሮች ይኖራሉ። ስለዚህ ‘አስተማሪዬ ክፉ ነው’ ወይም ‘አስተማሪዬ አይወደኝም’ ብለህ ለመደምደም አትቸኩል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን።”—ያዕቆብ 3:2 የግርጌ ማስታወሻ
“የአስተማሪዎች ሥራ በጣም ከባድ ነው። እነዚያ ሁሉ ልጆች ሥርዓት ይዘው እንዲማሩ ማድረግ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን መገመት ያዳግታል። አስተማሪዬ ቢያንስ ስለ እኔ እንዳትጨነቅ በማድረግ ጫናዋን ላቀልላት እሞክር ነበር።”—አሌክሲስ
ወላጆችህን አማክራቸው። ከማንም ይበልጥ ሊደግፉህ የሚችሉት ወላጆችህ ናቸው። የትምህርት ቤት ሕይወትህ የተሳካ እንዲሆን ይፈልጋሉ፤ ደግሞም የሚሰጡህ ምክር፣ አስቸጋሪ ከሆነ አስተማሪ ጋር እንድትግባባ ሊረዳህ ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል።”—ምሳሌ 15:22
“ወላጆች ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከወጣቶች የተሻለ ተሞክሮ አላቸው። ስለዚህ ምክራቸውን ስሙ። ይህ ስኬታማ እንድትሆኑ ይረዳችኋል።”—ኦሊቪያ
አስተማሪህን ማነጋገር የምትችለው እንዴት ነው?
አንዳንድ ጊዜ ስለሚሰማህ ስሜት ከአስተማሪህ ጋር መነጋገር ሊያስፈልግህ ይችላል። ከአስተማሪህ ጋር ፊት ለፊት መፋጠጥ ያስፈራህ ይሆናል፤ ሆኖም አትጨነቅ። ይህ ክርክር ሳይሆን ውይይት ነው። ካሰብከው በላይ ቀላልና ውጤታማ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰላም የሚገኝበትን . . . ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።”—ሮም 14:19
“አስተማሪያችሁ እናንተን ብቻ እንደጠመደቻችሁ ከተሰማችሁ ቅር የሚያሰኛትን ነገር አድርጋችሁ እንደሆነ ጠይቋት። የምትሰጣችሁ መልስ ማሻሻያ የምታደርጉበትን አቅጣጫ ሊጠቁማችሁ ይችላል።”—ጁሊያና
“ስለተፈጠረው ችግር ከአስተማሪያችሁ ጋር ስትነጋገሩ መረጋጋታችሁ አስፈላጊ ነው፤ በተጨማሪም ከትምህርት ሰዓት በፊት ወይም በኋላ በግል ማነጋገራችሁ የተሻለ ይሆናል። አስተማሪያችሁ ምክንያታዊ ሆኖ ሊያዳምጣችሁና ጉዳዩን በዚህ መንገድ ስለያዛችሁት ሊያከብራችሁ ይችላል።”—ቤንጃሚን
እውነተኛ ታሪክ
“ውጤቴ ጥሩ አልነበረም፤ አስተማሪዬ ደግሞ ምንም ልታግዘኝ ፈቃደኛ አልነበረችም። በጣም ስላስመረረችኝ ትምህርት ለማቋረጥ ሁሉ አስቤ ነበር።
“አንድን ሌላ አስተማሪ ስለ ጉዳዩ አማከርኩት። እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘በደንብ ስለማታውቅሽ ነው፤ አንቺም ብትሆኚ በደንብ አታውቂያትም። በጣም እንደተቸገርሽ ብትነግሪያት ጥሩ ነው። እንዲህ ማድረግሽ እሷን ለማነጋገር የሚፈሩ ሌሎች ተማሪዎችን ጭምር ሊጠቅም ይችላል።’
“እሷን ማነጋገር ፈጽሞ አልፈለግኩም ነበር! ግን ስለነገረኝ ነገር አሰብኩበት፤ ደግሞም ልክ ነበር። ግንኙነታችን እንዲስተካከል ከፈለግኩ ቅድሚያውን መውሰድ ነበረብኝ።
“ስለዚህ በቀጣዩ ቀን ወደ አስተማሪዬ ሄጄ ‘የምታስተምሪውን ትምህርት እወደዋለሁ፤ ደግሞም በደንብ እንዲገባኝ እፈልጋለሁ። ሆኖም ትምህርቱ ስለከበደኝ ምን እንደማደርግ ግራ ገብቶኛል’ ብዬ በአክብሮት ነገርኳት። እሷም አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ጠቆመችኝ፤ እንዲያውም ከትምህርት በኋላ ወይም በኢ-ሜይል አማካኝነት ልትረዳኝ እንደምትችል ገለጸችልኝ።
“በጣም ገረመኝ! አስተማሪዬን ማነጋገሬ በመካከላችን ያለው ግንኙነት እንዲሻሻልና የትምህርት ቤት ሕይወቴ አስደሳች እንዲሆን ረድቶኛል።”—ማሪያ
ጠቃሚ ምክር፦ ከአስተማሪህ ጋር መግባባት ከከበደህ፣ ሁኔታውን ለወደፊት ሕይወትህ እንደሚጠቅም ሥልጠና አድርገህ ውሰደው። የ22 ዓመቷ ኬቲ እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርት ከጨረሳችሁ በኋላም ቢሆን አስቸጋሪ ባሕርይ ያለው አለቃ ሊያጋጥማችሁ ይችላል። አስቸጋሪ ባሕርይ ካለው አስተማሪ ጋር መግባባት ከቻላችሁ ወደፊት ተመሳሳይ ባሕርይ ያለው ሰው ሲያጋጥማችሁ በተሻለ መንገድ መያዝ ትችላላችሁ።”