የወጣቶች ጥያቄ
ኃይሌ እንዳይሟጠጥና እንዳልዝል ምን ሊረዳኝ ይችላል?
ሥራ በጣም ይበዛብሃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ኃይልህ እንዳይሟጠጥና እንዳትዝል የሚረዱ ጠቃሚ ነጥቦችን ይጠቁምሃል!
መንስኤው ምንድን ነው?
የሥራ መብዛት። ጁሊ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች የበለጠ እንድንሠራ፣ ማሻሻያ እንድናደርግ፣ ከፍ ያሉ ግቦች እንድናወጣና ውጤት እንድናስመዘግብ ጫና ይደረግብናል። እንዲህ ያለውን ቀጣይ የሆነ ግፊት መቋቋም ከባድ ነው።”
ቴክኖሎጂ። ዘመናዊ ስልኮች፣ ታብሌቶችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሰዎች በማንኛውም ጊዜ እንዲያገኙን ያስችላሉ፤ ይህ ደግሞ ውጥረት ሊፈጥርብንና በጊዜ ሂደት እንድንዝል ሊያደርገን ይችላል።
እንቅልፍ ማጣት። ሚራንዳ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ወጣቶች በትምህርት፣ በሥራና በመዝናኛ ምክንያት ጠዋት የመነሳትና አምሽተው የመተኛት ልማድ አላቸው፤ እነዚህ ወጣቶች የማያቋርጥ ሽክርክሪት ውስጥ ገብተዋል።” እንዲህ ያለው ልማድ አብዛኛውን ጊዜ እንድንዝል ሊያደርገን ይችላል።
ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ጠንክሮ መሥራትን ያበረታታል። (ምሳሌ 6:6-8፤ ሮም 12:11) ሆኖም ጤናችንን ጨምሮ በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ እስኪያስፈልገን ድረስ መሥራትን አይደግፍም።
“በአንድ ወቅት በተለያዩ ሥራዎች ከመወጠሬ የተነሳ ቀኑን ሙሉ ምግብ ሳልበላ ዋልኩ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ፣ የሚሰጡኝን ኃላፊነቶች በሙሉ መቀበል ጥሩ እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጌ ጤናዬንም ጭምር ሊነካው ይችላል።”—አሽሊ
በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል” በማለት የሚናገር መሆኑ ተገቢ ነው። (መክብብ 9:4) ከአቅምህ በላይ ስትሠራ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እንደ አንበሳ ዓይነት ጥንካሬ እንዳለህ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም ኃይልህ እስኪሟጠጥና እስክትዝል ድረስ መሥራትህ በጤናህ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
አልችልም ማለትን ተማር። መጽሐፍ ቅዱስ “ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። (ምሳሌ 11:2) ልካቸውን የሚያውቁ ሰዎች የአቅም ገደብ እንዳለባቸው ስለሚገነዘቡ ሊሸከሙ ከሚችሉት በላይ ኃላፊነት አይቀበሉም።
“የተሰጠውን ኃላፊነት ሁሉ የሚቀበልና ‘አልችልም’ ማለትን የማያውቅ ሰው የመዛል አጋጣሚው በጣም ሰፊ ነው። ይህ ሰው ልኩን አያውቅም። ደግሞም ይዋል ይደር እንጂ መዛሉ አይቀርም።”—ጆርዳን
በቂ እረፍት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል” ይላል። (መክብብ 4:6) እንቅልፍ “የአንጎል ምግብ” እንደሆነ ቢነገርም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ያሉ አብዛኞቹ ወጣቶች በቀን ውስጥ የሚያስፈልጋቸውን ከስምንት እስከ አሥር ሰዓት የሚሆን እንቅልፍ እያገኙ አይደለም።
“ፕሮግራሜ በጣም የተጣበበ በነበረበት ወቅት በቂ እንቅልፍ የማልተኛባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ተጨማሪ የእንቅልፍ ሰዓት ማግኘቴ በቀጣዩ ቀን ይበልጥ ውጤታማ ሆኜ እንድሠራና ደስተኛ እንድሆን ይረዳኛል።”—ብሩክሊን
የተደራጀህ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) ጊዜህን አብቃቅተህ የመጠቀም ችሎታ ማዳበርህ ለቀሪው ሕይወትህ በሙሉ ይጠቅምሃል።
“ፕሮግራም ማውጣት አላስፈላጊ ውጥረትን በእጅጉ ይቀንሳል። ፕሮግራምህ በጽሑፍ ሰፍሮ ስታየው የቱ ጋ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለብህ በቀላሉ መለየት ትችላለህ፤ ይህም እንዳትዝል ይረዳሃል።”—ቨኔሳ