በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ብነቀስ ምን ችግር አለው?

ብነቀስ ምን ችግር አለው?

 ብዙዎች መነቀስ የሚፈልጉት ለምንድን ነው?

 ራያን የተባለ ወጣት “አንዳንድ ንቅሳቶች ውብ የሥነ ጥበብ ሥራዎች እንደሆኑ ይሰማኛል” በማለት ተናግሯል።

 ለመነቀስ የፈልግክበት ምክንያት ስለ መነቀስ ባለህ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ጂሊየን የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አብራኝ ትማር የነበረች ልጅ፣ በልጅነቷ እናቷ ሞተችባት። ስለዚህ አሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ስትገባ አንገቷ ላይ ከኋላ በኩል የእናቷን ስም ተነቀሰች። እንዲህ ዓይነት ንቅሳት ደስ የሚል ይመስለኛል።”

 ምክንያትህ ምንም ሆነ ምን፣ ቆዳህ ላይ የማይለቅ ምልክት ከማድረግህ በፊት ጊዜ ወስደህ ስለ ጉዳዩ በጥንቃቄ ማሰብ አለብህ! ለመነቀስ እያሰብክ ከሆነ ራስህን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብሃል? ከሁሉ የተሻለውን ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱህስ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ናቸው?

 ልታስብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?

 በጤና ላይ ምን ጉዳት ያስከትላል? የማዮ ክሊኒክ ድረ ገጽ እንዲህ ይላል፦ “በምንነቀስበት ጊዜ ቆዳችን ይበሳል፤ ይህ ደግሞ ቆዳችንን ለኢንፌክሽኖችና ለሌሎች ችግሮች ሊያጋልጠው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በንቅሳቱ ዙሪያ ግራኑሎማ ተብለው የሚጠሩ እብጠቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ንቅሳት፣ ኪሎይድ ማለትም ጠባሳ የሚሠሩት ሕብረ ሕዋሳት ከልክ በላይ በማደጋቸው ምክንያት የሚፈጠር እብጠት ሊያስከትል ይችላል።” ድረ ገጹ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “የምትነቀስበት መሣሪያ በተበከለ ደም የተበከለ ከሆነ በደም አማካኝነት ለሚተላለፉ በሽታዎች ልትጋለጥ ትችላለህ።”

 ሌሎች ስለ አንተ ባላቸው አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? ወደድክም ጠላህ ውጫዊ ገጽታህ ስለ አንተ ማንነት የሚናገረው ነገር ይኖራል። ሰዎች ውጫዊ ገጽታህን ብቻ በማየት ብስለት እንዳለህ ወይም እንደሌለህ፣ እምነት የሚጣልብህ እንደሆንክ ወይም እንዳልሆንክ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። ሳማንታ የተባለች ወጣት “የተነቀሱ ሰዎች ሳይ መጠጥና ጭፈራ የሚያበዙ ሰዎች ናቸው ወደ አእምሮዬ የሚመጡት” በማለት ተናግራለች።

 ሜላኒ የተባለች የ18 ዓመት ወጣት ደግሞ ጉዳዩን ከሌላ አቅጣጫ ተመልክታዋለች። እንዲህ ብላለች፦ “ንቅሳት የተፈጥሮ ውበትን የሚደብቅ ይመስለኛል። የሚነቀሱ ሰዎች ሌሎች ትክክለኛ ማንነታቸውን እንዲያዩ የሚፈልጉ አይመስለኝም፤ ስለዚህ ራሳቸውን በንቅሳት ለመደበቅ ይሞክራሉ።”

 ከጊዜ በኋላ ንቅሳቱ ቢያስጠላህስ? ስትወፍር ወይም ትንሽ ዕድሜህ ሲጨምር ንቅሳቱ ሊለጠጥ ወይም ቅርጹ ሊበላሽ ይችላል። ጆሴፍ የተባለ ወጣት “አንድ ሰው ከተነቀሰ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ንቅሳቱ ምን እንደሚመስል አይቻለሁ፤ ደስ አይልም” ብሏል።

 የ21 ዓመቱ አለን “አብዛኛውን ጊዜ ንቅሳቶች ጊዜ ያልፍባቸዋል” በማለት ተናግሯል። አክሎም “በአንድ ወቅት፣ ለተነቀሰው ሰው ልዩ ትርጉም የነበረው ንቅሳት ከጥቂት ዓመታት በኋላ ያን ያህል አስፈላጊ ላይሆን ይችላል” ብሏል።

 አለን የተናገረው ነገር ትክክል ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሰዎች ዕድሜያቸው ሲጨምር አመለካከታቸው፣ ምርጫቸውም ሆነ የሚወዱት ነገር ይቀየራል፤ ንቅሳታቸውን ግን መቀየር አይችሉም። ቴሬሳ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ወቅት የነበረኝን የሞኝነት አስተሳሰብ የሚያስታውሰኝ ንቅሳት በመነቀስ ዓመታት ካለፉ በኋላ የምጸጸትበትን ተጨማሪ ነገር ማድረግ አልፈልግም።”

 በዚህ ረገድ የሚረዱህ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው?

 ብስለት ያለው ሰው አንድ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ጊዜ ወስዶ ውሳኔው የሚያስከትለውን ውጤት ያመዛዝናል። (ምሳሌ 21:5፤ ዕብራውያን 5:14) እስቲ በዚህ ረገድ ሊረዱህ የሚችሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ተመልከት።

  •  ቆላስይስ 3:20 “ልጆች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ጌታን ያስደስተዋልና።”

      ከወላጆችህ ጋር እየኖርክ የእነሱን መመሪያ የማታከብር ከሆነ ውጤቱ ምን ይሆናል?

  •  1 ጴጥሮስ 3:3, 4 “ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በማጌጥ ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ የወርቅ ጌጣጌጦች በማድረግ ወይም ያማረ ልብስ በመልበስ አይሁን፤ ከዚህ ይልቅ ውበታችሁ የማይጠፋውን ጌጥ ይኸውም በአምላክ ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የሰከነና ገር መንፈስ የተላበሰ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን።”

      መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‘ለተሰወረው የልብ ሰው’ ይህን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምን ይመስልሃል?

  •  1 ጢሞቴዎስ 2:9 “ሴቶች . . . በልከኝነትና በማስተዋል . . . ራሳቸውን ያስውቡ።”

      “ልከኝነት” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው? ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ልከኝነት ከንቅሳት ይበልጥ ማራኪ የሚሆነው ለምንድን ነው?

  •  ሮም 12:1 “ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ።] . . . ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።”

      አምላክ ሰውነትህን የምትይዝበትን መንገድ በቁም ነገር ይመለከተዋል የምንለው ለምንድን ነው?

 በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ በርካታ ሰዎች ላለመነቀስ ወስነዋል። እንዲያውም ከመነቀስ የተሻለ አማራጭ አግኝተዋል። ቀድም ሲል የተጠቀሰችው ቴሬሳ እንዲህ ብላለች፦ “በጣም የምትወዱት ሰው ካለ ምን ያህል እንደምትወዱት ንገሩት፤ የምትወዱት አባባል ወይም መፈክር ካለ ደግሞ ሕይወታችሁን በዚያ መሠረት ለመምራት ሞክሩ። ሰውነታችሁ ላይ ከመነቀስ ይልቅ የምታምኑበትን ነገር ኑሩበት።”