ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ውሳኔ ማድረግን በተመለከተ ግሩም ምክር ይሰጠናል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጥበብንና ማስተዋልን እንድናገኝ’ ይረዳናል። (ምሳሌ 4:5) አንዳንድ ጊዜ ከሁሉ የተሻለው ውሳኔ የትኛው እንደሆነ ይነግረናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የጥበብ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ምክሮችን ይሰጠናል።
በዚህ ርዕስ ውስጥ
ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ምክሮች
ውሳኔ ለማድረግ አትቸኩል። መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ . . . አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) በችኮላ ውሳኔ ካደረግክ አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን ሳታስተውል ልታልፍ ትችላለህ። ጊዜ ወስደህ ያሉህን አማራጮች በጥንቃቄ ገምግም።—1 ተሰሎንቄ 5:21
በስሜትህ ላይ ብቻ ተመሥርተህ ውሳኔ አታድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ ልባችንን ሁልጊዜ ማመን እንደማንችል ይናገራል። (ምሳሌ 28:26፤ ኤርምያስ 17:9) ለምሳሌ ስንበሳጭ፣ ስናዝን፣ ተስፋ ስንቆርጥ፣ ስንቸኩል ወይም በጣም ሲደክመን ጥሩ ውሳኔ ላናደርግ እንችላለን።—ምሳሌ 24:10፤ 29:22
ጥበብ ለማግኘት ጸልይ። (ያዕቆብ 1:5) አምላክ እንዲህ ያሉ ጸሎቶችን መመለስ ያስደስተዋል። እሱ ልጆቹ አላስፈላጊ ችግር ውስጥ እንዲገቡ የማይፈልግ አሳቢ አባት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣልና፤ ከአፉ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ ይወጣል” ይላል። a (ምሳሌ 2:6) ይሖዋ በዋነኝነት ጥበብ የሚሰጠን በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ምርምር አድርግ። ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ አስተማማኝ መረጃ ያስፈልግሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበበኛ ሰው ያዳምጣል፤ ደግሞም ተጨማሪ ትምህርት ይቀስማል” ይላል። (ምሳሌ 1:5) ታዲያ ጠቃሚና አስተማማኝ መረጃ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?
በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚል መርምር። ለእኛ የሚበጀን ምን እንደሆነ የሚያውቀው ፈጣሪያችን ስለሆነ ከሁሉ የተሻለ አስተማማኝ ምክር ማግኘት የምንችለው ከቃሉ ነው። (መዝሙር 25:12) ከአንዳንድ ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማድረግ እንዳለብን በቀጥታ ይነግረናል፤ ይህን መረጃ የሚሰጠን በሕግ ወይም በትእዛዝ መልክ ሊሆን ይችላል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ከአብዛኞቹ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማድረግ እንዳለብን በቀጥታ አይነግረንም። ከዚህ ይልቅ በመሠረታዊ ሥርዓቶች አማካኝነት ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ ይመራናል። እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች የግል ፍላጎታችንን ባገናዘበ መልኩ የጥበብ ውሳኔ እንድናደርግ ይረዱናል። ከምታደርገው ውሳኔ ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ ምርምር አድርግ። እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን በዚህ ድረ ገጽ ላይ በነፃ ማግኘት ትችላለህ። b
አንዳንድ ውሳኔዎችን ለማድረግ ሌሎች አስተማማኝ የመረጃ ምንጮችንም ማየት ሊያስፈልግህ ይችላል። ለምሳሌ አንድን ዕቃ፣ በተለይም ውድ ዕቃ ከመግዛትህ በፊት ስለ ዕቃውና ስለ አምራቹ ምርምር ማድረግህ ጠቃሚ ነው። ዕቃው ቢበላሽ ወይም መመለስ ብትፈልግ ምን ማድረግ እንደምትችል ማጣራትህም ጥበብ ይሆናል። ደግሞም ዕቃው የምትፈልገውን አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን በሚገባ ማጣራት አለብህ።
መጽሐፍ ቅዱስ “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል” ይላል። (ምሳሌ 15:22) ስለዚህ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት እምነት የሚጣልባቸውን ሰዎች አማክር። ለምሳሌ ከሕክምና ጋር የተያያዘ ውሳኔ ስታደርግ ሐኪም ማማከርህ ጥበብ ይሆናል። (ማቴዎስ 9:12) አንዳንድ ውሳኔዎችን ስታደርግ እንደ አንተ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠማቸውን ሰዎች ማነጋገር ትችላለህ። ሆኖም ውሳኔውን ማድረግ ያለብህና የውሳኔውን ውጤት የምትቀበለው አንተ እንጂ ያማከርካቸው ሰዎች እንዳልሆኑ አስታውስ።—ገላትያ 6:4, 5
ሁሉንም ሁኔታዎች ከግምት አስገባ። የሰበሰብከውን መረጃ መሠረት በማድረግ ያሉህን አማራጮች እንዲሁም እያንዳንዱ አማራጭ ያለውን ጥሩና መጥፎ ጎን በዝርዝር ማስፈር ትችላለህ። ከዚያም ውሳኔህ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት በሐቀኝነት ገምግም። (ዘዳግም 32:29) ለምሳሌ ውሳኔህ በአንተ፣ በቤተሰብህ ወይም በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል? (ምሳሌ 22:3፤ ሮም 14:19) እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች አንጻር ማገናዘብህ ጥበብና ፍቅር የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንድታደርግ ይረዳሃል።
ውሳኔ አድርግ። አንዳንድ ጊዜ ስለ ውሳኔያችን ጥርጣሬ ስለገባን ብቻ ውሳኔ ከማድረግ ወደኋላ እንል ይሆናል። ሆኖም ውሳኔ ሳናደርግ ከቀረን ጥሩ አጋጣሚ ሊያመልጠን ወይም የማንፈልገው ሁኔታ ውስጥ ልንገባ እንችላለን። በሌላ አነጋገር፣ ውሳኔ አለማድረግ መጥፎ ውሳኔ የማድረግን ያህል ጎጂ ሊሆን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፤ ደመናትንም የሚመለከት አያጭድም” የሚል ከግብርና ጋር የተያያዘ ምሳሌ ይገኛል።—መክብብ 11:4
ከሁሉ የተሻለ ውሳኔም በሁሉም አቅጣጫ ጥሩ ይሆናል ማለት እንዳልሆነም አስታውስ። ብዙውን ጊዜ አንድ ነገር ስንመርጥ የሆነ ነገር መሥዋዕት ማድረግ ይጠበቅብናል። በተጨማሪም ያልተጠበቀ ክስተት ሊፈጠር ይችላል። (መክብብ 9:11) ስለዚህ ማግኘት የምትችለውን ከሁሉ የተሻለ መረጃ መሠረት አድርገህ፣ የተሻለ ውጤት ያስገኛል ብለህ የምታስበውን ውሳኔ አድርግ።
ያደረግኩትን ውሳኔ መቀየር ይኖርብኛል?
ሁሉም ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ነው ማለት አይደለም። የአንተ ሁኔታ ሊቀየር ይችላል፤ ወይም ደግሞ ያደረግከው ውሳኔ ያልተጠበቀ ውጤት እንዳመጣ ታስተውል ይሆናል። በመሆኑም ሁኔታውን ድጋሚ በማጤን የፈለግከውን ውጤት ለማግኘት የሚረዳህን ሌላ አማራጭ መከተልህ የጥበብ እርምጃ ሊሆን ይችላል።
ይሁን እንጂ መቀየር የሌለባቸው አንዳንድ ውሳኔዎች አሉ። (መዝሙር 15:4) ለምሳሌ አምላክ ባለትዳሮች የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸዋል። c (ሚልክያስ 2:16፤ ማቴዎስ 19:6) በትዳር ውስጥ ችግር ሲያጋጥም ባለትዳሮቹ ትዳራቸውን ከማፍረስ ይልቅ ችግሩን ለመፍታት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ልቀለብሰው የማልችል መጥፎ ውሳኔ አድርጌ ከሆነስ?
ሁላችንም መጥፎ ወይም ጥበብ የጎደለው ውሳኔ የምናደርግበት ጊዜ ይኖራል። (ያዕቆብ 3:2 የግርጌ ማስታወሻ) በዚህ ጊዜ የጸጸት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማን ይችላል፤ ይህም ተፈጥሯዊ ነው። (መዝሙር 69:5) እንዲህ ያለው ስሜት ያንን ስህተት እንዳንደግመው ከረዳን ጥሩ ነገር ነው። (ምሳሌ 14:9) ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት አእምሯዊ ወይም ስሜታዊ ጉዳት ሊያስከትልብን ስለሚችል እንዲህ ካለው ስሜት መራቅ እንዳለብን ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 2:7) d መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ መሐሪና ሩኅሩኅ” እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 103:8-13) ስለዚህ ልትቀለብሰው የማትችል መጥፎ ውሳኔ አድርገህ ከሆነ ከስህተትህ ለመማር ጥረት አድርግ፤ እንዲሁም ሁኔታውን ለማሻሻል አቅምህ የፈቀደውን አድርግ።
a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።—መዝሙር 83:18
b ከምታደርገው ውሳኔ ጋር የተያያዘ ቃል ወይም ሐረግ በማስገባት ከjw.org ላይ መረጃ መፈለግ ትችላለህ። ይህ ድረ ገጽ መጽሐፍ ቅዱስ ስለተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የሚሰጠውን ምክር ይዟል። በተጨማሪም አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ማውጫ” በመጠቀም አንዳንድ ቃላትን መፈለግ ትችላለህ።
c የአምላክ ዓላማ ባለትዳሮች በሕይወት እስካሉ ድረስ አብረው እንዲኖሩ ነው። አምላክ ፍቺ መፈጸምንና ሌላ ማግባትን የሚፈቅደው አንደኛው የትዳር አጋር የፆታ ብልግና ከፈጸመ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 19:9) በትዳርህ ውስጥ ችግር ካጋጠመህ መጽሐፍ ቅዱስ ችግሩን ፍቅርና ጥበብ በሚንጸባረቅበት መንገድ እንድትፈታው ይረዳሃል።
d ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል—መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ስሜት ለማሸነፍ ሊረዳኝ ይችላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።