የሕይወት ትርጉሙ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ በተለያየ መንገድ ሊቀርብ ይችላል፤ የተፈጠርነው ለምንድን ነው? ወይም የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ የተፈጠርንበት ዓላማ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት እንደሆነ ይናገራል። እስቲ ይህን ሐቅ የሚያረጋግጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሐሳቦችን እንመልከት።
አምላክ ፈጣሪያችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] ፈጠረን፤ እኛም የእርሱ ነን” ይላል።—መዝሙር 100:3፤ ራእይ 4:11
አምላክ እኛን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የፈጠረው በዓላማ ነው።—ኢሳይያስ 45:18
አምላክ የፈጠረን ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ሲሆን ይህም የሕይወትን ትርጉም የማወቅ ፍላጎትን ይጨምራል። (ማቴዎስ 5:3) አምላክ ይህን ፍላጎታችንን እንድናረካ ይፈልጋል።—መዝሙር 145:16
ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለንን ፍላጎት ማርካት የምንችለው ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና በመመሥረት ነው። አንዳንዶች የአምላክ ወዳጅ መሆን የማይቻል ነገር እንደሆነ ቢያስቡም መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት ያበረታታናል።—ያዕቆብ 4:8፤ 2:23
የአምላክ ወዳጅ ለመሆን ከእሱ ዓላማ ጋር ተስማምተን መኖር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 12:13 ላይ ስለ ሕይወት ዓላማ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “አምላክን ፍራ ትዕዛዛቱንም ጠብቅ፤ ምክንያቱም የተፈጠርነው ለዚህ ዓላማ ነው።”—ጉድ ኒውስ ትራንስሌሽን
አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥር ካወጣው ዓላማ ጋር በሚስማማ መልኩ መከራን እንደሚያስወግድና ለወዳጆቹ ማለትም እሱን ለሚያመልኩ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው መተማመን እንችላለን።—መዝሙር 37:10, 11