አምላክ አንዳንድ ጸሎቶችን የማይመልሰው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ ለአንዳንድ ጸሎቶች መልስ የማይሰጥበት ጊዜ አለ። አምላክ፣ አንድ ሰው የሚያቀርበውን ጸሎት የማይሰማባቸውን ሁለት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት፦
1. ጸሎቱ ከአምላክ ፈቃድ ውጪ ከሆነ
አምላክ ከእሱ ፈቃድ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት መሥፈርቶቹ ጋር የሚቃረኑ ጸሎቶችን አይሰማም። (1 ዮሐንስ 5:14) ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስግብግብ መሆን እንደሌለብን ይናገራል። ቁማር ደግሞ ስግብግብነትን የሚያበረታታ ጨዋታ ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ስለዚህ ሎተሪ ለማሸነፍ ብትጸልይ አምላክ ይህን ጸሎትህን አይሰማም። አምላክ ‘የፈለግኩትን ነገር በፈለግኩት ጊዜ ያደርግልኛል’ ብለህ መጠበቅ አይኖርብህም። እንዲያውም ይህ ባለመሆኑ አመስጋኝ መሆን ይኖርብሃል። አምላክን የፈለግነውን ነገር መጠየቅ የምንችል ቢሆን ኖሮ ሌሎች ምን ብለው ይጠይቁታል የሚለው ነገር ያስፈራን ነበር።—ያዕቆብ 4:3
2. ግለሰቡ የዓመፅ ድርጊቶችን የሚፈጽም ከሆነ
አምላክ ሆን ብለው እሱን የሚያሳዝን ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት አይሰማም። ለምሳሌ ያህል አምላክ፣ እሱን እንደሚያገለግሉ እየተናገሩ የዓመፅ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል።” (ኢሳይያስ 1:15) እነዚህ ሰዎች አካሄዳቸውን በማስተካከል ከእሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ቢያድሱ ኖሮ ጸሎታቸውን ይሰማ ነበር።—ኢሳይያስ 1:18