ራሴን የማጥፋት ሐሳብ ሲመጣብኝ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳኝ ይችላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አዎ! መጽሐፍ ቅዱስ “ያዘኑትን የሚያጽናናው አምላክ” ያጻፈው መጽሐፍ ነው። (2 ቆሮንቶስ 7:6) ስለ አእምሮ ጤንነት የሚያስተምር መጽሐፍ ባይሆንም ራሳቸውን ለማጥፋት ያስቡ የነበሩ በርካታ ሰዎችን ረድቷል። በውስጡ የሚገኘው ጠቃሚ ምክር አንተንም ሊረዳህ ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ጠቃሚ ምክር ይሰጣል?
● ስሜትህን አውጥተህ ተናገር።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17
የጥቅሱ ትርጉም፦ የሚያስጨንቁ ሐሳቦች ወደ አእምሯችን ሲመጡ የሌሎች እርዳታ ያስፈልገናል።
ስሜትህን አምቀህ ለመያዝ የምትሞክር ከሆነ የውስጥህን ጭንቀት መሸከም ሊከብድህ ይችላል። ስሜትህን አውጥተህ ለሌሎች መናገርህ ግን ጭንቀቱ ቀለል እንዲልልህ አልፎ ተርፎም ጉዳዩን ከሌላ አቅጣጫ እንድታየው ሊረዳህ ይችላል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ስሜትህን ዛሬውኑ ለሆነ ሰው ምናልባትም ለቤተሰብህ አባል ወይም ለምትቀርበው ጓደኛህ ተናገር። የሚሰማህን ስሜት በጽሑፍ መግለጽም ትችላለህ።
● የባለሙያ እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።”—ማቴዎስ 9:12
የጥቅሱ ትርጉም፦ ከታመምን የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይኖርብናል።
ራስን የማጥፋት ሐሳብ፣ የአእምሯዊ ወይም የስሜታዊ ሕመም ምልክት ሊሆን ይችላል። ልክ እንደ አካላዊ ሕመም ሁሉ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ሕመምም የሚያሳፍር ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሕክምና እርዳታ ሊሻሻል የሚችል ነገር ነው።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በተቻለህ ፍጥነት የባለሙያ እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ።
● አምላክ እንደሚያስብልህ አስታውስ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አምስት ድንቢጦች አነስተኛ ዋጋ ባላቸው ሁለት ሳንቲሞች ይሸጡ የለም? ሆኖም አንዷም እንኳ በአምላክ ዘንድ አትረሳም። . . . አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።”—ሉቃስ 12:6, 7
የጥቅሱ ትርጉም፦ በአምላክ ፊት ውድ ነህ።
ብቻህን እንደተተውክ ይሰማህ ይሆናል፤ ሆኖም አምላክ ያለህበትን ሁኔታ ጠንቅቆ ያውቃል። በሕይወት መኖር ቢያስጠላህም አምላክ ስለ አንተ ያስባል። መዝሙር 51:17 “አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም” ይላል። አምላክ ስለሚወድህ በሕይወት እንድትኖር ይፈልጋል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ አምላክ እንደሚወድህ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን መርምር። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀውን ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 24 አንብብ።
● ወደ አምላክ ጸልይ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7
የጥቅሱ ትርጉም፦ አምላክ ያስጨነቀህን ማንኛውንም ነገር ምንም ሳትሸሽግ በግልጽ እንድትነግረው ግብዣ አቅርቦልሃል።
አምላክ ውስጣዊ ሰላም እንድታገኝና ሁኔታህን መቋቋም የምትችልበት አቅም እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13) በዚህ መንገድ፣ በቅን ልቦና ተነሳስተው የእሱን እርዳታ የሚጠይቁ ሰዎችን ይደግፋቸዋል።—መዝሙር 55:22
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ዛሬውኑ ወደ አምላክ ጸልይ። ይሖዋ የተባለውን ስሙን እየጠራህ ወደ እሱ ጸልይ፤ የሚሰማህን ስሜት ሁሉ ንገረው። (መዝሙር 83:18) እንዲሁም ብርታት እንዲሰጥህ ጠይቀው።
● መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚሰጣቸው ተስፋዎች ላይ አሰላስል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እኛ ለሕይወታችን እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን።”—ዕብራውያን 6:19 የግርጌ ማስታወሻ
የጥቅሱ ትርጉም፦ ስሜትህ በማዕበል እየተናወጠ እንዳለ ጀልባ አንዴ ወደ ላይ አንዴ ደግሞ ወደ ታች ሊዋዥቅ ይችላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ ግን ባለህበት ተረጋግተህ እንድትቆም ይረዳሃል።
ይህ ተስፋ እንዲሁ የሕልም እንጀራ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለሥቃያችን ሁሉ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች እንደሚያስወግድልን በገባው ቃል ላይ የተመሠረተ ነው።—ራእይ 21:4
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለውን ብሮሹር ትምህርት 5 በማንበብ መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ስለሚሰጠው ተስፋ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አድርግ።
● ደስታ የሚሰጡህን ነገሮች አድርግ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው።”—ምሳሌ 17:22
የጥቅሱ ትርጉም፦ የሚያስደስቱንን ነገሮች ማድረጋችን አእምሯዊም ሆነ ስሜታዊ ጤንነታችን እንዲሻሻል ሊረዳን ይችላል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ደስታ የሚሰጡህን ነገሮች አድርግ። ለምሳሌ መንፈስ የሚያድስ ሙዚቃ ልታዳምጥ፣ የሚያበረታታ ነገር ልታነብ ወይም ሌሎች የሚያስደስቱ ነገሮችን ልታደርግ ትችላለህ። በተጨማሪም ትንሽ ቢሆንም እንኳ ሌሎችን ለመርዳት የምታደርገው ጥረት ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን ያደርግሃል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
● ጤንነትህን ጠብቅ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል።”—1 ጢሞቴዎስ 4:8
የጥቅሱ ትርጉም፦ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጋችን፣ በቂ እንቅልፍ መተኛታችንና ጤናማ ምግቦችን መመገባችን ጠቃሚ ነው።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ለ15 ደቂቃ ያህል ብቻ ቢሆንም እንኳ ወጣ ብለህ የእግር ጉዞ አድርግ።
● ዛሬ የሚሰማህ ስሜትም ሆነ በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠሙህ ሌሎች ሁኔታዎች እንደሚለወጡ አስታውስ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን . . . አታውቁም።”—ያዕቆብ 4:14
የጥቅሱ ትርጉም፦ ከአቅምህ በላይ እንደሆነ የሚሰማህ ችግርም እንኳ ጊዜያዊ ሊሆን ይችላል።
ዛሬ ያለህበት ሁኔታ ምንም ያህል ጭልምልም ያለ ቢመስል ነገ ሊለወጥ ይችላል። ስለዚህ ችግሩን መቋቋም የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ። (2 ቆሮንቶስ 4:8) ያለህበት አስጨናቂ ሁኔታ በጊዜ ሂደት ይለወጥ ይሆናል፤ ራስህን ካጠፋህ ግን ሁኔታውን መመለስ የምትችልበት ምንም መንገድ የለም።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በጣም ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ ሞታቸውን ተመኝተው ስለነበሩ ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን አንብብ፤ የእነዚህ ሰዎች ችግር ምናልባትም ፈጽሞ ባልጠበቁት መንገድ መፍትሔ ያገኘው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሞታቸውን ተመኝተው ስለነበሩ ሰዎች የሚገልጽ ዘገባ ይዟል?
አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ ሞተው መገላገልን ተመኝተው ስለነበሩ አንዳንድ ሰዎች ይናገራል። አምላክ እነዚህን ሰዎች አልገሠጻቸውም፤ ከዚህ ይልቅ እርዳታ አድርጎላቸዋል። አንተንም ሊረዳህ ይችላል።
ኤልያስ
● ይህ ሰው ማን ነው? ኤልያስ ደፋር ነቢይ ነበር። ሆኖም ተስፋ የቆረጠበት ወቅት ነበር። ያዕቆብ 5:17 “ኤልያስ እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው ነበር” ይላል።
● ሞቱን ተመኝቶ የነበረው ለምንድን ነው? በአንድ ወቅት ኤልያስ ብቸኝነት፣ ፍርሃትና የዋጋ ቢስነት ስሜት ተሰምቶት ነበር። በመሆኑም “ይሖዋ ሆይ፣ . . . ሕይወቴን ውሰዳት” በማለት ለምኗል።—1 ነገሥት 19:4
● በዚህ ወቅት የረዳው ነገር ምን ነበር? ኤልያስ ስሜቱን ሁሉ አውጥቶ ለአምላክ ተናግሯል። አምላክስ ያበረታታው እንዴት ነው? አምላክ አሳቢነት ያሳየው ከመሆኑም ሌላ ኃይሉን የሚያሳዩ ድርጊቶችን በመፈጸም አበረታቶታል። ከዚህም በላይ አሁንም በእሱ ፊት ተፈላጊ እንደሆነ አረጋግጦለታል፤ በሥራው የሚያግዘው አሳቢና ብቃት ያለው ረዳትም ሰጥቶታል።
▸ ስለ ኤልያስ አንብብ፦ 1 ነገሥት 19:2-18
ኢዮብ
● ይህ ሰው ማን ነው? ኢዮብ ትልቅ ቤተሰብ ያለውና እውነተኛውን አምላክ በታማኝነት የሚያገለግል ሀብታም ሰው ነበር።
● ሞቱን ተመኝቶ የነበረው ለምንድን ነው? የኢዮብ ሕይወት በድንገት ምስቅልቅሉ ወጣ። ንብረቱን ሁሉ ያጣ ከመሆኑም ሌላ ሁሉም ልጆቹ በአደጋ ሞቱበት። በተጨማሪም የሚያሠቃይ ሕመም ያዘው። ይህ ሁሉ ሳያንሰው ሰዎች፣ ችግሮች እየደረሱበት ያለው በራሱ ጥፋት እንደሆነ በመግለጽ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በሐሰት ይወነጅሉት ጀመር። ኢዮብ “ሕይወቴን ተጸየፍኳት፤ በሕይወት መቀጠል አልፈልግም” ብሎ ነበር።—ኢዮብ 7:16
● በዚህ ወቅት የረዳው ነገር ምን ነበር? ኢዮብ ወደ አምላክ ይጸልይ እንዲሁም ስሜቱን ለሌሎች ይናገር ነበር። (ኢዮብ 10:1-3) ኤሊሁ የተባለ አሳቢ ወዳጁም ያበረታታው ሲሆን ለችግሩ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲይዝ ረድቶታል። ከምንም በላይ ግን ኢዮብን የረዳው አምላክ የሰጠውን ምክርና እርዳታ መቀበሉ ነበር።
▸ ስለ ኢዮብ አንብብ፦ ኢዮብ 1:1-3, 13-22፤ 2:7፤ 3:1-13፤ 36:1-7፤ 38:1-3፤ 42:1, 2, 10-13
ሙሴ
● ይህ ሰው ማን ነው? ሙሴ የጥንቱ የእስራኤል ብሔር መሪና ታማኝ ነቢይ ነበር።
● ሞቱን ተመኝቶ የነበረው ለምንድን ነው? ሙሴ ከባድ የሥራ ጫና ነበረበት፤ በተጨማሪም የማያባራ ትችት ይሰነዘርበት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ውስጡ ዝሎ ነበር። በመሆኑም “እባክህ አሁኑኑ ግደለኝ” በማለት ወደ አምላክ ጮዃል።—ዘኁልቁ 11:11, 15
● በዚህ ወቅት የረዳው ነገር ምን ነበር? ሙሴ የተሰማውን ስሜት ለአምላክ ተናግሯል። አምላክም ሙሴ ያለበትን የሥራ ጫና በመቀነስ ጭንቀቱን አቅልሎለታል።
▸ ስለ ሙሴ አንብብ፦ ዘኁልቁ 11:4-6, 10-17