ሞትን ከመፍራት ነፃ መውጣት የምትችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ሞትን እንደ ጠላታችን በመመልከት ተገቢ በሆነ መንገድ የምንፈራው ከሆነ ሕይወታችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ አንዳንድ እርምጃዎችን እንወስዳለን። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ያም ቢሆን በሐሰት ትምህርቶችና በአጉል እምነት ምክንያት የሚመጣ መሠረተ ቢስ የሞት ፍርሃት ሰዎች “በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ ለባርነት [እንዲዳረጉ]” ምክንያት ሆኗል። (ዕብራውያን 2:15) ሞትን መፍራት በሕይወትህ ደስታ እንዳታገኝ እንቅፋት ይሆንብሃል፤ እውነትን ማወቅ ግን ለሞት ከልክ ያለፈ ፍርሃት እንዳያድርብህ በመከላከል ነፃ ያወጣሃል።—ዮሐንስ 8:32
ስለ ሞት እውነታው ምንድን ነው?
የሞቱ ሰዎች ከሕልውና ውጪ ናቸው። (መዝሙር 146:4) መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር ስለሚያመሳስለው ከሞትኩ በኋላ ልሠቃይ አችላለሁ ብለህ ልትፈራ አይገባም።—መዝሙር 13:3፤ ዮሐንስ 11:11-14
ሙታን ጉዳት ሊያደርሱብን አይችሉም። ቀደም ሲል ጉዳት ያደርሱብን የነበሩ ጠላቶቻችን እንኳ ከሞቱ በኋላ “መንፈሳቸው ተነሥቶ አይመጣም።” (ኢሳይያስ 26:14) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጥላቻቸውና ቅናታቸው ከጠፋ ቆይቷል’ ይላል።—መክብብ 9:6
እርግጥ ስንሞት ሕልውናችን እስከ መጨረሻው ያከትማል ማለት አይደለም። አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት የሞቱ ሰዎችን መልሶ ሕያው ያደርጋቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15
አምላክ ‘ሞት የማይኖርበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:4) መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ጊዜ አስመልክቶ ሲናገር “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። በዚህ ወቅት የሚኖሩ ሰዎች ከማንኛውም ዓይነት የሞት ፍርሃት ሙሉ በሙሉ ነፃ ይወጣሉ።—መዝሙር 37:29