የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ሮም 15:13—“የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ”
“በእሱ በመታመናችሁ የተነሳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተስፋ እንዲትረፈረፍላችሁ ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።”—ሮም 15:13 አዲስ ዓለም ትርጉም
“በእርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስላችሁ ነው።”—ሮም 15:13 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የሮም 15:13 ትርጉም
ሐዋርያው ጳውሎስ በእነዚህ ቃላት አማካኝነት አምላክ የእምነት ባልንጀሮቹን ‘ደስታና ሰላም’ እንዲሞላባቸው ያለውን ምኞት ገልጿል። እነዚህ ግሩም ባሕርያት አምላክ ከሚሰጠው ተስፋና ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል ጋር የተያያዙ ናቸው።
አምላክ የሰጠውን ተስፋ በጽሑፍ ከሰፈረው ቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንማራለን። ሮም 15:4 እንደሚገልጸው “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ [በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ] ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።” መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ፣ ሕይወት በዛሬው ጊዜ ተስፋ ቢስ እንዲመስል ያደረጉትን ችግሮች ለማስወገድ ቃል እንደገባ ይናገራል፤ ከእነዚህ ችግሮች መካከል ድህነት፣ የፍትሕ መጓደል፣ በሽታ እና ሞት ይገኙበታል። (ራእይ 21:4) አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ተጠቅሞ ይህን ቃሉን ይፈጽማል፤ ወደፊት የተሻለ ሕይወት እንደምናገኝ ተስፋ የምናደርገው ለዚህ ነው።—ሮም 15:12
አምላክ የሰጠን ይህ ተስፋ ‘የሚትረፈረፍልን’ በእሱ ከተማመንን ብቻ ነው። ስለ አምላክ ይበልጥ በተማርን መጠን እሱ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት መሆኑን ይበልጥ እርግጠኞች እንሆናለን። (ኢሳይያስ 46:10፤ ቲቶ 1:2) አምላክ አስተማማኝ ተስፋ ስለሰጠን፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን እንኳ በደስታ እና በሰላም ልንሞላ እንችላለን።—ሮም 12:12
ሰላም፣ ደስታ እና ተስፋ ‘ከመንፈስ ቅዱስ’ ጋርም ተያይዘው ተጠቅሰዋል፤ መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል ነው። a አምላክ የገባውን ቃል ለመፈጸም ቅዱስ መንፈሱን ይጠቀማል፤ ይህ ደግሞ ተስፋ ሰጪ ነው። ይህ መንፈስ፣ ሰዎች እንደ ደስታ እና ሰላም ያሉ ግሩም ባሕርያትን እንዲያዳብሩም ያስችላል።—ገላትያ 5:22
የሮም 15:13 አውድ
የሮም መጽሐፍ በሮም ከተማ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የተጻፈ ደብዳቤ ነው። በዚያ ከነበሩት ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ አይሁዳውያን ነበሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ አይሁዳውያን አልነበሩም። ዘራቸውና ባሕላቸው የተለያየ ቢሆንም እንኳ ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች በአስተሳሰብም ሆነ በምግባር አንድነታቸውን ለመጠበቅ ጥረት እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል።—ሮም 15:6
ጳውሎስ፣ አምላክ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች እሱን በአንድነት እንደሚያወድሱት ከረጅም ጊዜ በፊት እንደተናገረ ለሮም ክርስቲያኖች አስታውሷቸዋል። ጳውሎስ ይህን ለማስረዳት ሲል ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት b አራት ጊዜ ጠቅሷል። (ሮም 15:6) ለማስተላለፍ የፈለገው ነጥብ ይህ ነበር፦ እንደ አይሁዳውያን ሁሉ፣ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ከክርስቶስ አገልግሎት መጠቀም ይችላሉ። አምላክ ለሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ስለዚህ በሮም ጉባኤ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ፣ አይሁዳውያን ሆኑም አልሆኑ ‘አንዳቸው ሌላውን መቀበል’ ወይም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።—ሮም 15:7
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b “የዕብራይስጥ ቅዱስን መጻሕፍት” አንዳንድ ጊዜ “ብሉይ ኪዳን” በመባልም ይጠራሉ።