በእምነታቸው ምሰሏቸው | ዮናታን
“የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ”
ውጊያው ተጠናቋል፤ በኤላህ ሸለቆም ጸጥታ ሰፍኗል። የከሰዓቱ ነፋስ ሠራዊቱ ያረፈባቸውን ድንኳኖች እያወዛወዛቸው ነው። ንጉሥ ሳኦል ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ስብሰባ ተቀምጧል። የመጀመሪያ ልጁ ዮናታን በስብሰባው ላይ የተገኘ ሲሆን አንድ ወጣት እረኛ ታሪኩን በሚያጓጓ መንገድ እየተናገረ ነው። ታሪኩን በቅንዓትና በግለት እየተናገረ ያለው ይህ ወጣት ዳዊት ነው። ሳኦል፣ ከታሪኩ ውስጥ አንድም ነገር እንዲያመልጠው ስላልፈለገ በጥሞና እያዳመጠ ነው። ዮናታንስ ምን ተሰምቶት ይሆን? ዮናታን በይሖዋ ሠራዊት ውስጥ ባገለገለባቸው በርካታ ዓመታት ብዙ ድሎችን ተቀዳጅቷል። በዚያን ዕለት ድል የተቀዳጀው ግን እሱ ሳይሆን ወጣቱ ዳዊት ነው። ዳዊት ግዙፍ የሆነውን ጎልያድን ገድሎታል! ታዲያ ዮናታን፣ ዳዊት ባገኘው ክብር ቀንቶ ይሆን?
ዮናታን በዚህ ወቅት ምን ስሜት እንዳደረበት ስታውቅ ትገረም ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ዳዊት ከሳኦል ጋር ተነጋግሮ እንደጨረሰ ዮናታንና ዳዊት የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ፤ ዮናታንም እንደ ራሱ ወደደው።” ዮናታን ለዳዊት ቀስቱን ጨምሮ የውጊያ ልብሶቹን ሰጠው። ይህ በጣም ልዩ ስጦታ ነው፤ ምክንያቱም ዮናታን የታወቀ ቀስተኛ ነበር። ከዚህም ባለፈ ዮናታንና ዳዊት ቃል ኪዳን ተጋቡ። በዚህ ቃል ኪዳን አማካኝነት ሁለቱ ሰዎች እርስ በርስ የሚደጋገፉ ጥብቅ ወዳጆች ለመሆን ስምምነት አደረጉ።—1 ሳሙኤል 18:1-5
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት በጣም የጠበቁ ወዳጅነቶች መካከል አንዱ የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር። ወዳጅነት፣ ለእምነት ሰዎች በጣም አስፈላጊ ነው። ፍቅር በጠፋባቸው በእነዚህ ጊዜያት ወዳጆቻችንን በጥበብ የምንመርጥ ከሆነ እንዲሁም ለሌሎች የድጋፍ ምንጭና ታማኝ ወዳጅ ለመሆን ጥረት የምናደርግ ከሆነ እምነታችንን ማጠናከር እንችላለን። (ምሳሌ 27:17) እንግዲያው ወዳጅነትን በተመለከተ ከዮናታን ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት።
ለወዳጅነት መሠረት የሚሆነው ነገር
ዮናታንና ዳዊት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ወዳጅነት ሊመሠርቱ የቻሉት እንዴት ነው? መልሱ ለወዳጅነታቸው መሠረት ከሆነው ነገር ጋር የተያያዘ ነው። እስቲ ታሪካቸውን መለስ ብለን ለመቃኘት እንሞክር። ዮናታን ይኖር የነበረው በአስቸጋሪ ወቅት ነው። አባቱ ንጉሥ ሳኦል ከጊዜ ወደ ጊዜ መጥፎ ሰው እየሆነ ሄዷል። በአንድ ወቅት ትሑት፣ ታዛዥና የእምነት ሰው የነበረው ሳኦል እብሪተኛና ዓመፀኛ ንጉሥ ሆኖ ነበር።—1 ሳሙኤል 15:17-19, 26
ዮናታን ከአባቱ ጋር ይቀራረብ ስለነበር የሳኦል ባሕርይ መለወጡ በእጅጉ አሳስቦት መሆን አለበት። (1 ሳሙኤል 20:2) ምናልባትም በሳኦል ምክንያት ይሖዋ በመረጠው ብሔር ላይ የሚመጣው ጉዳት ሳያስጨንቀው አልቀረም። የንጉሡ አለመታዘዝ፣ ሕዝቡ እንዲያምፅና የይሖዋን ሞገስ እንዲያጣ ያደርገው ይሆን? ይህ ወቅት እንደ ዮናታን ላለ የእምነት ሰው በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
ይህን ማወቃችን ዮናታን ዳዊትን የወደደበትን ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል። ዮናታን፣ ዳዊት ጠንካራ እምነት እንዳለው ማስተዋል ችሏል። በሳኦል ሠራዊት ውስጥ የሚያገለግሉት ተዋጊዎች ግዙፉን ጎልያድን መግጠም ፈርተው የነበረ ቢሆንም ዳዊት ግን ፈጽሞ አልተሸበረም። የይሖዋን ስም ተሸክሞ መዋጋቱ ብቻ ከጎልያድና እሱ ከታጠቃቸው የጦር መሣሪያዎች የበለጠ ኃያል እንደሚያደርገው ተማምኖ ነበር።—1 ሳሙኤል 17:45-47
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ዮናታንም እንዲህ ያለ እምነት እንዳለው አሳይቷል። እሱና ጋሻ ጃግሬው ብቻቸውን፣ የታጠቁ ወታደሮች ያሉበትን የጦር ሰፈር መምታትና ድል ማድረግ እንደሚችሉ ተማምኖ ነበር። ለምን? ዮናታን ‘ይሖዋን ከማዳን የሚያግደው ነገር የለም’ ሲል ተናግሯል። (1 ሳሙኤል 14:6) በመሆኑም ዮናታንና ዳዊት ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገር ነበር፤ ሁለቱም በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው። በሁለቱ ሰዎች መካከል ለነበረው ወዳጅነት ከሁሉ የላቀው ጠንካራ መሠረት ይህ ነበር። ዮናታን ወደ 50 ዓመት የሚጠጋው ኃያል መስፍን ሲሆን ዳዊት ደግሞ ገና 20 ዓመት ያልሞላው ተራ እረኛ ነበር፤ ሆኖም እነዚህ ልዩነቶች ሁለቱ ሰዎች የጠበቀ ወዳጅነት እንዳይመሠርቱ እንቅፋት አልሆኑባቸውም። a
ዮናታንና ዳዊት የገቡት ቃል ኪዳን ወዳጅነታቸውን ለመጠበቅ በእጅጉ ረድቷቸዋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ዳዊት፣ ይሖዋ ለእሱ ምን እንዳሰበለት ያውቃል፤ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው እሱ ነው! ታዲያ ዳዊት ይህን ጉዳይ ከዮናታን ሚስጥር አድርጎ ይዞት ይሆን? በፍጹም! በዳዊትና በዮናታን መካከል እንደነበረው ያለ ጥሩ ወዳጅነት ጠንካራ ሆኖ የሚቀጥለው በግልጽ በመነጋገር እንጂ በሚስጥር እና በውሸት አይደለም። ታዲያ ዮናታን፣ ዳዊት ንጉሥ ሆኖ እንደተሾመ በማወቁ ምን ተሰማው? ዮናታን ‘ወደፊት ንጉሥ ሆኜ ስሾም አባቴ የሠራቸውን ስህተቶች አስተካክላለሁ’ የሚል ተስፋ ኖሮት ቢሆንስ? መጽሐፍ ቅዱስ ዮናታን በውስጡ ካደረበት አሉታዊ ስሜት ጋር ትግል እንዳደረገ የሚገልጽ ሐሳብ አልያዘም፤ ከዚህ ይልቅ የሚናገረው ትልቅ ቦታ ስለሚሰጠው ጉዳይ ይኸውም ዮናታን ስላሳየው ታማኝነትና እምነት ነው። ዮናታን የይሖዋ መንፈስ ከዳዊት ጋር እንደሆነ ማስተዋል ችሎ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:1, 11-13) በመሆኑም የገባውን ቃል ኪዳን ያከበረ ከመሆኑም ሌላ ዳዊትን እንደ ተቀናቃኙ ሳይሆን እንደ ወዳጁ አድርጎ መመልከቱን ቀጥሏል። ዮናታን የይሖዋ ፈቃድ ሲፈጸም ማየት ይፈልግ ነበር።
ዮናታንና ዳዊት በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው
ይህ ወዳጅነት ለሁለቱም ትልቅ በረከት አስገኝቶላቸዋል። ታዲያ ዮናታን ካሳየው እምነት ምን እንማራለን? የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ ወዳጅነት ያለውን ዋጋ መገንዘባቸው አስፈላጊ ነው። ወዳጆች አድርገን የምንመርጣቸው ሰዎች የግድ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ዕድሜ ወይም አስተዳደግ ያላቸው መሆን አያስፈልጋቸውም፤ እውነተኛ እምነት እስካላቸው ድረስ ጥሩ ወዳጆች ሊሆኑን ይችላሉ። ዮናታንና ዳዊት በተደጋጋሚ አንዳቸው ሌላውን ማበረታታትና ማጠናከር ችለው ነበር። ደግሞም ሁለቱም እንዲህ ያለ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር፤ ምክንያቱም ብዙም ሳይቆይ ወዳጅነታቸውን የሚፈትን ከባድ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል።
ተገቢ ለሆነው አካል ታማኝነት ማሳየት
መጀመሪያ ላይ፣ ሳኦል ዳዊትን በጣም ይወደው የነበረ ሲሆን በሠራዊቱ ላይ ሾሞት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ጠላት በሆነው ቅናት ተሸነፈ። ዮናታን ይህን ጠላት ያሸነፈው ቢሆንም ሳኦል ግን ይህን ጠላት ማሸነፍ አልቻለም። ዳዊት የእስራኤላውያን ጠላት በሆኑት በፍልስጤማውያን ላይ በተደጋጋሚ ድል ተቀዳጀ። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ውዳሴና አድናቆት አተረፈ። እንዲያውም አንዳንድ የእስራኤል ሴቶች “ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ” በማለት ዘፍነው ነበር። ሳኦል ግን በዚህ አልተደሰተም። መጽሐፍ ቅዱስ “ከዚያች ዕለት አንስቶ ሳኦል ዳዊትን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከተው ጀመር” በማለት ይናገራል። (1 ሳሙኤል 18:7, 9) ሳኦል፣ ዳዊት ንግሥናውን እንዳይቀማው ፈርቶ ነበር። ሆኖም ይህ ሞኝነት የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ነው። እርግጥ ነው፣ ዳዊት ከሳኦል ቀጥሎ እንደሚነግሥ ያውቅ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ የቀባውን ንጉሥ ከሥልጣኑ አውርዶ ለመንገሥ በጭራሽ አስቦ አያውቅም!
ሳኦል፣ ዳዊት በጦርነት ላይ እያለ እንዲገደል አሴረ፤ ሆኖም አልተሳካለትም። ዳዊት ድል መቀዳጀቱንና በሕዝቡ ዘንድ አክብሮት ማትረፉን ቀጠለ። በመሆኑም ሳኦል ቤተሰቡን ማለትም አገልጋዮቹንና የበኩር ልጁን በማስተባበር ዳዊትን ለመግደል ሌላ እቅድ አወጣ። ዮናታን ይህን ሲያይ ምን ያህል አዝኖ ሊሆን እንደሚችል አስበው! (1 ሳሙኤል 18:25-30፤ 19:1) ዮናታን ለአባቱ ታማኝ ልጅ ቢሆንም ለዳዊትም ታማኝ ወዳጅ ነበር። ታዲያ በዚህ ወቅት ለየትኛው ወገን ታማኝ ለመሆን ይመርጥ ይሆን?
ዮናታን እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ንጉሡ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ኃጢአት አይሥራ፤ ምክንያቱም እሱ በአንተ ላይ የሠራው ኃጢአት የለም፤ ያደረገልህም ነገር ቢሆን ለአንተ የሚበጅ ነው። ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ፍልስጤማዊውን መታ፤ ይሖዋም ለመላው እስራኤል ታላቅ ድል አጎናጸፈ። አንተም ይህን አይተህ በጣም ተደስተህ ነበር። ታዲያ ያለምንም ምክንያት ዳዊትን በመግደል በንጹሕ ሰው ደም ላይ ለምን ኃጢአት ትሠራለህ?” ሳኦል ባልተጠበቀ መልኩ ምክንያታዊነት በማሳየት የዮናታንን ምክር ሰማ፤ አልፎ ተርፎም በዳዊት ላይ ጉዳት ላለማድረስ ማለ። ሆኖም ሳኦል ቃሉን አልጠበቀም። ዳዊት ተጨማሪ ድሎችን ሲቀዳጅ ሳኦል በቅናትና በንዴት ከመዋጡ የተነሳ ጦር ወርውሮ ዳዊትን ሊገድለው ሞከረ! (1 ሳሙኤል 19:4-6, 9, 10) ሆኖም ዳዊት ካመለጠ በኋላ ከሳኦል ቤተ መንግሥት ሸሽቶ ሄደ።
አንተስ ታማኝ መሆን ያለብህ ለማን እንደሆነ ግራ ገብቶህ ያውቃል? እንዲህ ያለው ሁኔታ ስሜትህን ሊጎዳው እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም። አንዳንዶች፣ እንዲህ ባለ ሁኔታ ሥር ምንጊዜም ለቤተሰብ ቅድሚያ መስጠት እንዳለብህ ሊመክሩህ ይችላሉ። ሆኖም ዮናታን ይህ ትክክል እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። ዮናታን፣ ዳዊት ታማኝና ታዛዥ የይሖዋ አገልጋይ እንደሆነ እያወቀ ከአባቱ ጋር እንዴት ሊተባበር ይችላል? በመሆኑም ለይሖዋ ባለው ታማኝነት ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ አድርጓል። ለዳዊት ጥብቅና የቆመው በዚህ ምክንያት ነው። እርግጥ ዮናታን ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት ቢያስቀድምም ለአባቱም ታማኝ እንደሆነ አሳይቷል፤ መስማት የሚፈልገውን ነገር ከመንገር ይልቅ በሐቀኝነት ምክር ሰጥቶታል። ዮናታን የተወውን የታማኝነት ምሳሌ መከተላችን ሁላችንንም ይጠቅመናል።
ታማኝነት የሚያስከፍለው ዋጋ
ዮናታን፣ ሳኦልና ዳዊትን ለማስታረቅ በድጋሚ ጥረት አደረገ፤ ሆኖም ሳኦል ሊሰማው እንኳ ፈቃደኛ አልሆነም። ዳዊት በድብቅ ወደ ዮናታን በመሄድ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደወደቀ ገለጸለት። በተጨማሪም በዕድሜ ለሚበልጠው ወዳጁ “በእኔና በሞት መካከል ያለው አንድ እርምጃ ብቻ ነው!” ሲል ነገረው። ዮናታን፣ አባቱ ያለውን አመለካከት ካጣራ በኋላ ውጤቱን እንደሚያሳውቀው ለዳዊት ነገረው። ዳዊት ተደብቆ ባለበት፣ ዮናታን ፍላጻ ተጠቅሞ ምልክት እንደሚሰጠው ገለጸለት። ዮናታን ዳዊትን አንድ ነገር ብቻ ቃል እንዲገባለት ጠየቀው፤ “ይሖዋ የዳዊትን ጠላቶች በሙሉ ከምድር ገጽ ጠራርጎ በሚያጠፋበት ጊዜም ለቤተሰቤ ታማኝ ፍቅርህን ከማሳየት ፈጽሞ ወደኋላ አትበል” አለው። ዳዊትም ምንጊዜም የዮናታንን ቤተሰብ እንደሚንከባከብ ቃል ገባ።—1 ሳሙኤል 20:3, 13-27
ዮናታን ለሳኦል ስለ ዳዊት መልካም ነገሮችን ነገረው፤ ንጉሡ ግን እጅግ ተቆጣ። ዮናታንን “የዚያች ዓመፀኛ ሴት ልጅ” ብሎ የጠራው ከመሆኑም ሌላ ለዳዊት ታማኝ መሆኑ በቤተሰቡ ላይ ውርደት እንዳመጣ በመግለጽ ሰደበው። ከዚያም “የእሴይ ልጅ በምድር ላይ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተም ሆንክ መንግሥትህ አትጸኑም” በማለት ዮናታንን ስለ ራሱ ጥቅም እንዲያስብ ለማድረግ ሞከረ። በዚህ ያልተበገረው ዮናታን “ለምን ይገደላል? ጥፋቱስ ምንድን ነው?” በማለት አባቱን ለማግባባት ጥረት ማድረጉን ቀጠለ። በዚህ ጊዜ ሳኦል በቁጣ ገነፈለ! ሳኦል ዕድሜው ይግፋ እንጂ ኃያል ተዋጊ ነው። በመሆኑም በልጁ ላይ ጦር ወረወረበት! ሳኦል የተዋጣለት ጦረኛ ቢሆንም ዮናታንን ሳተው። አባቱ ባደረሰበት ውርደት የተከፋውና በጣም ያዘነው ዮናታን በቁጣ ስፍራውን ለቆ ሄደ።—1 ሳሙኤል 20:24-34
ዮናታን የራሱን ጥቅም እንዲያስቀድም በቀረበለት ፈተና አልተሸነፈም
ዮናታን በቀጣዩ ቀን ማለዳ ላይ ተነስቶ፣ ዳዊት ተደብቆ ካለበት ቦታ አቅራቢያ ወደሚገኝ ሜዳ አቀና። በተነጋገሩት መሠረት ፍላጻዎቹን በመወርወር ሳኦል አሁንም ሊገድለው እንደሚፈልግ ለዳዊት ምልክት ሰጠው። ከዚያም ዮናታን አገልጋዩን ወደ ከተማ እንዲመለስ ነገረው። አሁን በስፍራው ያሉት እሱና ዳዊት ብቻ ስለሆኑ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ለብቻቸው የሚነጋገሩበት ጊዜ አገኙ። ሁለቱም ተላቀሱ፤ በዚህ መልኩ ዮናታን የስደት ሕይወት የሚጠብቀውን ወዳጁን ዳዊትን በሐዘን ተሰናበተው።—1 ሳሙኤል 20:35-42
ዮናታን ለራሱ ፍላጎት ቅድሚያ እንዲሰጥ የቀረበለትን ፈተና በታማኝነት አልፏል። ታማኝ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ጠላት የሆነው ሰይጣን፣ ዮናታን የሳኦልን ፈለግ በመከተል ለራሱ ሥልጣንና ክብር ቢፈልግ ደስ ይለው ነበር። ሰይጣን የራስ ወዳድነት ዝንባሌን ተጠቅሞ ሰዎችን ማጥመድ እንደሚፈልግ አትዘንጋ። የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ማለትም አዳምንና ሔዋንን በማጥመድ ረገድ ተሳክቶለታል። (ዘፍጥረት 3:1-6) ከዮናታን ጋር በተያያዘ ግን አልተሳካለትም። ሰይጣን ምንኛ ተበሳጭቶ ይሆን! አንተስ እንዲህ ያሉ ፈተናዎችን ትቋቋማለህ? የምንኖረው ራስ ወዳድነት እንደ ወረርሽኝ በተዛመተበት ዓለም ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ታዲያ ዮናታን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ስሜትና ታማኝነት በማሳየት ረገድ ከተወው ምሳሌ የምንማረው ነገር ይኖር ይሆን?
“አንተ በእኔ ዘንድ እጅግ የተወደድክ ነበርክ”
ሳኦል ለዳዊት ያለው ጥላቻ እያደገ ሄዶ አስተሳሰቡንና ስሜቱን ሁሉ ተቆጣጠረው። በመሆኑም ልክ እንደ አበደ ሰው መሆንና አንድን ንጹሕ ሰው ለመግደል ሲል ሠራዊቱን አሰባስቦ መላ አገሪቱን ማሰስ ጀመረ። ዮናታን ይህን ሁሉ ሲያይ በጣም አዝኖ መሆን አለበት። (1 ሳሙኤል 24:1, 2, 12-15፤ 26:20) ለመሆኑ ዮናታን በዚህ ዘመቻ ተካፍሎ ይሆን? ቅዱሳን መጻሕፍት ዮናታን ከእነዚህ ዘመቻዎች ውስጥ በአንዱም ላይ እንደተካፈለ አይገልጹም። ዮናታን ለይሖዋ፣ ለዳዊት እንዲሁም ለገባው የወዳጅነት ቃል ኪዳን ታማኝ ስለሆነ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር ሊያደርግ አይችልም።
ዮናታን ወጣት ለሆነው ወዳጁ ያለው ፍቅር ፈጽሞ አልተለወጠም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሆሬሽ (“ጫካ” የሚል ትርጉም አለው) ሄዶ ዳዊትን አገኘው። ሆሬሽ ያለው ከኬብሮን በስተ ደቡብ ምሥራቅ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ እንደሚገኝ በሚገመት ተራራማና ሰው የማይኖርበት አካባቢ ነው። ዮናታን፣ በስደት ላይ ያለውን ዳዊትን ለማግኘት ይህን ያህል መሥዋዕትነት የከፈለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ዮናታን እንዲህ ለማድረግ የተነሳሳው “በይሖዋ ላይ ያለው ትምክህት እንዲጠናከር” ዳዊትን ሊረዳው ስለፈለገ እንደሆነ ይገልጻል። (1 ሳሙኤል 23:16) ለመሆኑ ዮናታን ዳዊትን ያበረታታው እንዴት ነው?
ዮናታን ወጣቱን ዳዊትን “አትፍራ” አለው። በተጨማሪም “አባቴ ሳኦል [አያገኝህም]” የሚል ማረጋገጫ ሰጠው። ዮናታን እንዲህ ብሎ በእርግጠኝነት ሊናገር የቻለው እንዴት ነው? የይሖዋ ዓላማ መሳካቱ እንደማይቀር ጠንካራ እምነት ስለነበረው ነው። ከዚህም በላይ ዮናታን ዳዊትን “አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ” አለው። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ ከይሖዋ ተልእኮ ተቀብሎ የመጣው ነቢዩ ሳሙኤል ለዳዊት ተመሳሳይ ነገር ነግሮት ነበር፤ አሁን ደግሞ ዮናታን የይሖዋ ቃል ምንጊዜም እምነት የሚጣልበት እንደሆነ አስታወሰው። ይሁንና ዮናታን ስለ ራሱስ ምን በማለት ተናገረ? “ከአንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ” አለ። እንዴት ያለ አስደናቂ ትሕትና ነው! ዮናታን የ30 ዓመት ታናሹ በሆነው በዳዊት አመራር ሥር በመሆን ለእሱ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። ሐሳቡን ሲደመድም “አባቴ ሳኦልም ቢሆን ይህን ያውቃል!” በማለት ተናገረ። (1 ሳሙኤል 23:17, 18) ሳኦል፣ ይሖዋ ቀጣዩ ንጉሥ እንዲሆን ከመረጠው ሰው ተዋግቶ ፈጽሞ ሊያሸንፍ እንደማይችል በልቡ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር።
ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ሁሉ፣ ዳዊት ከዮናታን ጋር ያደረገውን ውይይት ወደ ኋላ መለስ ብሎ በማሰብ ልቡ በደስታ ይሞላ እንደነበር እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህ አጋጣሚ ከዮናታን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙበት ወቅት ነው። የሚያሳዝነው ነገር፣ ዮናታን ከዳዊት ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው ለመሆን የነበረው ምኞት ዳር ሳይደርስ ቀርቷል።
ዮናታን፣ የእስራኤላውያን ጠላቶች እንደሆኑ በግልጽ ከሚናገሩት ፍልስጤማውያን ጋር በተደረገው ውጊያ ላይ ከአባቱ ጎን ተሰለፈ። ዮናታን በንጹሕ ሕሊና እንዲህ ማድረግ ይችል ነበር፤ ምክንያቱም አባቱ የሠራቸው ስህተቶች ለይሖዋ የሚያቀርበውን አምልኮ እንዲነኩበት አልፈቀደም። ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው በድፍረትና በታማኝነት የተዋጋ ቢሆንም እስራኤላውያን በውጊያው ድል አልቀናቸውም። ሳኦል በክፋት ጎዳናው እየገፋ ሄዶ በሕጉ መሠረት በሞት የሚያስቀጣ ከባድ ኃጢአት ማለትም መናፍስታዊ ድርጊት እስከመፈጸም ደርሶ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ሳኦልን መባረኩን አቆመ። ዮናታንን ጨምሮ የሳኦል ሦስት ወንዶች ልጆች በውጊያው ተገደሉ። ክፉኛ የቆሰለው ሳኦልም በገዛ እጁ ሕይወቱን አጠፋ።—1 ሳሙኤል 28:6-14፤ 31:2-6
ዮናታን “አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፤ እኔ ደግሞ ከአንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ” በማለት ተናግሯል።—1 ሳሙኤል 23:17
ዳዊት ከባድ ሐዘን ላይ ወደቀ። ደግና ይቅር ባይ የሆነው ዳዊት፣ ብዙ መከራና ችግር ባደረሰበት በሳኦል ሞት እንኳ በጣም አዘነ! እንዲያውም ለሳኦልና ለዮናታን የሐዘን እንጉርጉሮ ጻፈ። ከእንጉርጉሮው ውስጥ ከሁሉ በላይ ልብ የሚነካው፣ ውድ አማካሪውና ወዳጁ ስለሆነው ስለ ዮናታን የጻፈው ሐሳብ ሳይሆን አይቀርም፤ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሜ ዮናታን፣ በአንተ የተነሳ ተጨንቄአለሁ፤ አንተ በእኔ ዘንድ እጅግ የተወደድክ ነበርክ። የአንተ ፍቅር ለእኔ ከሴት ፍቅር ይበልጥ ነበር።”—2 ሳሙኤል 1:26
ዳዊት ለዮናታን የገባውን ቃል ፈጽሞ አልረሳም። የአካል ጉዳተኛ የሆነውን የዮናታንን ልጅ ሜፊቦስቴን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አፈላልጎ በማግኘት እንክብካቤ አድርጎለታል። (2 ሳሙኤል 9:1-13) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ዳዊት ከዮናታን ብዙ ነገር ተምሯል። ዮናታን ለወዳጁ ታማኝነትና አክብሮት አሳይቷል፤ እንዲሁም በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ ከጎኑ ለመቆም ፈቃደኛ ሆኗል። እኛስ ዮናታን ከተወው ምሳሌ ለመማር ፈቃደኞች ነን? እንደ ዮናታን ወዳጆችን ለማፍራት ጥረት እናደርጋለን? እኛ ራሳችንስ ለሌሎች ጥሩ ወዳጅ ለመሆን እንሞክራለን? ወዳጆቻችን በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲገነቡና እንዲያጠናክሩ የምንረዳቸው ከሆነ፣ ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ከምንም ነገር በላይ የምናስቀድም ከሆነ እንዲሁም በራሳችን ፍላጎት ላይ ከማተኮር ይልቅ ለወዳጆቻችን ታማኝ ለመሆን ጥረት የምናደርግ ከሆነ እንደ ዮናታን ዓይነት ወዳጅ መሆን እንችላለን። በተጨማሪም እምነት በማሳየት ረገድ ዮናታን የተወውን ምሳሌ እንደምንከተል እናሳያለን።
a ዮናታን ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ሳኦል መግዛት በጀመረበት ወቅት ነው፤ ዮናታን በወቅቱ የጦር አዛዥ ስለነበር ዕድሜው ቢያንስ 20 ዓመት መሆን ይኖርበታል። (ዘኁልቁ 1:3፤ 1 ሳሙኤል 13:2) ሳኦል ለ40 ዓመታት ገዝቷል። በመሆኑም ሳኦል ሲሞት ዮናታን 60 ዓመት ገደማ፣ ዳዊት ደግሞ 30 ዓመቱ ነበር። (1 ሳሙኤል 31:2፤ 2 ሳሙኤል 5:4) በመሆኑም ዮናታን ዳዊትን በ30 ዓመት ገደማ ሳይበልጠው አይቀርም።