ሚያዝያ 29, 2024
ፊሊፒንስ
የማቴዎስ መጽሐፍ በፊሊፒኖ ምልክት ቋንቋ ወጣ
ሚያዝያ 21, 2024 በኬሶን ከተማ በሚገኘው የፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ የፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዲን ያሴክ የማቴዎስ መጽሐፍ በፊሊፒኖ ምልክት ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። በፕሮግራሙ ላይ 413 ወንድሞችና እህቶች በአካል ተገኝተዋል። በመላው አገሪቱ የሚገኙ ሌሎች 3,998 ሰዎች ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታትለዋል። መጽሐፉ jw.org እና JW Library Sign Language አፕሊኬሽን ላይ ወዲያውኑ ለተጠቃሚዎች ተለቅቋል።
የፊሊፒኖ ምልክት ቋንቋን የሚጠቀሙ ሰዎች ብዛት ከ500,000 እንደማያንስ ይገመታል። በ1999 ኬሶን ከተማ ውስጥ የመጀመሪያው የፊሊፒኖ ምልክት ቋንቋ ጉባኤ ተቋቋመ፤ በ2011 ደግሞ በቋንቋው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች መተርጎም ጀመሩ። በአሁኑ ወቅት በመላው ፊሊፒንስ በ72 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ3,000 በላይ ወንድሞችና እህቶች አሉ።
ይህ በፊሊፒኖ ምልክት ቋንቋ ሙሉ በሙሉ የተተረጎመው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ነው። መስማት የተሳነው አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መጽሐፍ ከመውጣቱ በፊት ከማቴዎስ መጽሐፍ ላይ በቋንቋችን ማግኘት የምንችለው የተወሰኑ ጥቅሶችን ብቻ ነበር። የአንድን ትልቅ ተገጣጣሚ ሥዕል የተወሰኑ ቁርጥራጮች ብቻ እንደ ማግኘት ነው። አሁን ግን ሙሉው ምስል አለን!” በፊሊፒኖ ምልክት ቋንቋ ጉባኤ የሚያገለግል አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “የማቴዎስ መጽሐፍ እረኝነት ለማድረግም ሆነ ጉባኤውን ለማነጽ የሚረዱ ብዙ ትምህርቶች ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ ማቴዎስ 5:23, 24 ከወንድሞቻችን ጋር አለመግባባት ሲያጋጥመን ሰላም እንድንፈጥር ያሳስበናል። እነዚህ አስፈላጊ ትምህርቶች በቋንቋችን እንዲተረጎሙ በማድረጉ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።”
የማቴዎስ መጽሐፍ በፊሊፒኖ ምልክት ቋንቋ በመውጣቱ ተደስተናል፤ ሌሎች በርካታ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከአምላክ ቃል እንዲጠቀሙ ይረዳል የሚል እምነት አለን።—ማቴዎስ 7:24, 25