ሰኔ 29, 2023
አርጀንቲና
በአርጀንቲና እና በኡራጓይ በሚገኙ ገለልተኛ ክልሎች ምሥራቹን መስበክ
የአርጀንቲና ቅርንጫፍ ቢሮ ከጥር እስከ ሚያዝያ 2023 በአርጀንቲና እና በኡራጓይ በሚገኙ ገለልተኛ ክልሎች ልዩ የስብከት ዘመቻ አዘጋጅቶ ነበር። በዘመቻው የተካፈሉት ከ9,500 የሚበልጡ አስፋፊዎች፣ 700 ገደማ በሚሆኑ ቡድኖች ተከፋፍለው ነበር። እነዚህ አስፋፊዎች በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ ባሉት በእነዚህ ገለልተኛ ክልሎች ውስጥ የሚገኙትን 146 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ረድተዋል።
በአርጀንቲና እና በኡራጓይ በሚገኙ ትናንሽ ሰፈሮች፣ የአገሬው ሰዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች እንዲሁም ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች አሉ። ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ እነዚህ ክልሎች ሄዶ መስበክ ለአስፋፊዎች ከባድ ነበር። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ራቅ ባሉት በእነዚህ ክልሎች መስበካቸውን መቀጠል በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል።
ወንድም አድሪያን ዶናዲዮ እና ባለቤቱ ካሪና በታርታጋል፣ አርጀንቲና ወደተሰጣቸው ክልል ለመድረስ 1,600 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዘዋል። አድሪያን እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎቹ መንፈሳዊ ጥማት እንዳላቸው ስላስተዋልን እረፍት የሚሰጠውን ምሥራች ለእነሱ ማድረስ በመቻላችን በጣም ተደስተን ነበር።”
ሁለት አስፋፊዎች አርጀንቲና ውስጥ በሚገኝ ባራንካስ የሚባል አካባቢ በ90ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አረጋውያን ባልና ሚስት አገኙ። ባልና ሚስቱ ከወረርሽኙ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረው ነበር። ሆኖም ቤታቸው የሚገኘው በጣም ርቆ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ የኢንተርኔት አገልግሎት አልነበራቸውም፤ በመሆኑም ለሦስት ዓመት ያህል ከጉባኤው ጋር መገናኘት አልቻሉም ነበር። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማዳቸውን የቀጠሉ ሲሆን አንድ ሰው በድጋሚ መጥቶ እንዲያነጋግራቸው ወደ ይሖዋ ይጸልዩ ነበር። ወንድሞች ለዘመቻ እነሱ ወዳሉበት አካባቢ ሲመጡ በጣም ተደሰቱ። ጸሎታቸውን ስለመለሰላቸው ይሖዋን አመሰገኑ፤ ጥናታቸውንም እንዲቀጥሉ ዝግጅት ተደረገ።
በሞንቴቪዴዮ፣ ኡራጓይ የዘወትር አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉት ወንድም ኤዱዋር ፌሬራ እና ባለቤቱ አሌሃንድራ፣ ርቆ በሚገኘው የአገሪቱ ክልል በሚደረገው ዘመቻ ለመካፈል 400 ኪሎ ሜትር ተጉዘዋል። የ17፣ የ15 እና የ11 ዓመት ልጆቻቸውም አብረዋቸው ወደ ዘመቻው ሄደው ነበር። ኤዱዋር እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችን በደስታ ተሞልተው ሲሰብኩ ማየት በጣም ያስደስታል። ቤተሰባችን ለቀጣዩ ዘመቻ ዝግጁ ነው!”
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ርቀው በሚገኙት በእነዚህ ክልሎች ‘በተሟላ ሁኔታ ለመመሥከር’ ያደረጉትን ጥረት ይሖዋ እንደባረከው በማየታችን በጣም ተደስተናል።—የሐዋርያት ሥራ 10:42