በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 29, 2019
ብራዚል

በብራዚል በተካሄደ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች መስማትና ማየት ለተሳናቸው ሰዎች JW.ORGን አስተዋወቁ

በብራዚል በተካሄደ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች መስማትና ማየት ለተሳናቸው ሰዎች JW.ORGን አስተዋወቁ

የይሖዋ ምሥክሮች ከነሐሴ 30 እስከ መስከረም 8, 2019 በሪዮሴንትሮ የስብሰባና የኤግዚቢሽን ማዕከል በተካሄደው 19ኛው የሪዮ ዴ ጄኒሮ ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ ተሳትፈው ነበር። የብራዚል ትልቁ ባሕላዊ ኤግዚቢሽን በሆነው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ 520 ድርጅቶች ዝግጅት ያቀረቡ ሲሆን 600,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች አውደ ርዕዩን ጎብኝተዋል። ወንድሞቻችን ድረ ገጻችንን የሚያስተዋውቅ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለማዳረስ የምናደርገውን ጥረት የሚያሳይ ኤግዚቢሽን አቅርበው ነበር። ለአሥር ቀናት በተካሄደው የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ የተካፈሉት 258 ወንድሞችና እህቶች 3,737 ጽሑፎችን አበርክተዋል።

ወንድሞቻችን ባዘጋጁት ኤግዚቢሽን ላይ የመስማት ችግር ላለባቸው፣ መስማት ለተሳናቸው ወይም ማየት ለተሳናቸው ሰዎች ታስቦ የተዘጋጀ ልዩ ክፍል ነበር። ወንድሞች በብራዚል ምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን ያሳዩ ሲሆን ምልክት ቋንቋ የሚችሉ አስፋፊዎች ጎብኚዎቹን እንዲያግዙ ተመድበው ነበር። በኤግዚቢሽኑ ከተሳተፉት ወንድሞች አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ጎብኚዎቹ ወደ ኤግዚቢሽናችን ሲመጡ ምንም ሳይሳቀቁ ያነጋግሩን ነበር። ምክንያቱም ስለ jw.org አጠቃቀም እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው እንዴት እንደሆነ ለማብራራት የተዘጋጁ ወንድሞች ምንጊዜም በቦታው ይገኙ ነበር።”

የአሥር ዓመት ልጅ የሆነ ማየት የተሳነው አስፋፊ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁት የብሬይል ጽሑፎች እንዴት እንደረዱት ለአንዲት ጋዜጠኛ ሲናገር

አንዲት አስተማሪ መስማት የተሳናቸውን ሰባት ተማሪዎቿን ይዛ ወደ ኤግዚቢሽኑ መጥታ ነበር። በ​jw.org ላይ ለወጣቶች የተዘጋጁትን የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎች ስታይ በጣም ተገረመች። አስተማሪዋ በርካታ ወላጆች መስማት የተሳናቸው ልጆቻቸውን ከባድ ስለሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ለማነጋገር እንድትረዳቸው እንደሚጠይቋት የተናገረች ሲሆን ከዚህ በኋላ ወላጆች ድረ ገጻችንን እንዲጎበኙ እንደምትነግራቸው ገልጻለች።

አንዲት እህት ለአንድ ጎብኚ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ስታሳይ

በተጨማሪም ኤግዚቢሽኑ እንደ ግዋራኒ፣ ቲኩና እና ዛቫንቴ ባሉት አገር በቀል ቋንቋዎች jw.org​ን አስተዋውቋል። የብራዚል የይሖዋ ምሥክሮች ቃል አቀባይ የሆነው ሪካርዶ ካርኔሮ “ዓላማችን የአገሬው ጎሳዎች መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩ መርዳት ነው” ብሏል።

የሪዮ ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ የሚዘጋጀው በብራዚል የሚኖሩ ሰዎች የንባብ ልማዳቸውን በማሳደግ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ለመርዳት ታስቦ ነው። የ​jw.org​ን ማስተዋወቂያ ኤግዚቢሽን የተመለከቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች፣ ለበርካታ መቶ ዓመታት ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ሲረዳ የቆየውን መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ የሚችሉበት አጋጣሚ አግኝተዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17