በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 19, 2019
ስፔን

ታሪካዊ ቀን፦ የይሖዋ ምሥክሮች የተሻሻለውን አዲስ ዓለም ትርጉም በስፓንኛ አወጡ

ታሪካዊ ቀን፦ የይሖዋ ምሥክሮች የተሻሻለውን አዲስ ዓለም ትርጉም በስፓንኛ አወጡ

ዓርብ፣ ሐምሌ 19, 2019 “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል”! በተባለው በማድሪድ፣ ስፔን በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ላይ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የተሻሻለው የስፓንኛ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱ ተገለጸ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ከ2.5 ሚሊዮን የሚበልጡ ስፓንኛ ተናጋሪ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሱን jw.org® ላይ ማንበብ እና ማውረድ ይችላሉ፤ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል በተናጋሪዎች ብዛት አንደኛ የሆነው ቋንቋ ስፓንኛ ነው። a

መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱ የተነገረው በማድሪድ በሚገኘው ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ውስጥ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ሲሆን የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ ከስብሰባው ቀደም ብሎ በተቀረጸው ቪዲዮ ላይ የዚህን መጽሐፍ ቅዱስ መውጣት ገልጿል። ቪዲዮው ስፔን ውስጥ ወደ ሌሎች 11 ቦታዎችም ተላልፎ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱ ከተገለጸ ብዙም ሳይቆይ ይህ ቪዲዮ JW Broadcasting® ላይ ወጥቷል።

የተሻሻለው ስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሲወጣ ተሰብሳቢዎቹ ደስታቸውን ሲገልጹ

በብሔራት አቀፉ ስብሰባ ላይ የተገኙት በሙሉ መጽሐፍ ቅዱሱን ከ​jw.org ላይ በ​EPUB፣ በ​JWPUB ወይም በ​PDF ፎርማቶች እንዲያወርዱ ልዩ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ስፔን ውስጥ በሌሎቹ 11 ቦታዎች በተካሄዱት ስብሰባዎች ላይ የተገኙ ሰዎችም ስልካቸውን ወይም ታብሌታቸውን JW Box ከተባለ ለስብሰባው ተብሎ የተዘጋጀ የዋይፋይ ሆትስፖት ጋር በማገናኘት መጽሐፍ ቅዱሱን ማውረድ ችለዋል። በብሔራት አቀፍ ስብሰባውና በሌሎቹ የስብሰባ ቦታዎች ላይ አድማጮች መጽሐፍ ቅዱሱን ማውረድ እንዲችሉ ለመርዳት የተመደቡ ከ1,200 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ነበሩ።

ወንድሞችና እህቶች በስፓንኛ የወጣውን አዲስ ዓለም ትርጉም ስልካቸው ላይ ሲያወርዱ

መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ስፓንኛ መተርጎም ተፈታታኝ ሥራ ነበር፤ ምክንያቱም በዓለም ዙሪያ ስፓንኛ የሚናገሩ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። የስፔን ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፔድሮ ጊል እንዲህ ብሏል፦ “በዓለም ዙሪያ 577 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ስፓንኛ ተናጋሪዎች አሉ፤ አንዳንድ ቃላትና አገላለጾች ያላቸው ትርጉም ከአገር አገር ይለያያል። ከዚህም ሌላ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ስፓንኛ ቋንቋ በጣም ተቀይሯል።”

አንዲት ወጣት ፈቃደኛ ሠራተኛ የመጽሐፍ ቅዱሱን የኤሌክትሮኒክ ቅጂ እንድታወርድ አንዲትን እህት ስትረዳ

የትርጉም ቡድኑ ትክክለኛና ቀላል የሆነ ትርጉም ለማዘጋጀት ሲል በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ 100 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶችን አማክሯል። አጠቃላዩ ሥራ አራት ዓመት ተኩል ወስዷል።

ወንድም ጊል እንዲህ ብሏል፦ “የተሻሻለው ስፓንኛ አዲስ ዓለም ትርጉም የሚጠቀመው ማንኛውም ሰው ሊረዳው የሚችል ቀላል ቋንቋ ነው። ይህም አስፋፊዎች መጽሐፍ ቅዱስን በአገልግሎትም ሆነ በጉባኤ ለመጠቀም ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ስፓንኛ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ እንደሚረዳቸው ማወቃችን ያስደስተናል።”

ይሖዋ ስሙን የሚያስከብር አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ስለሰጠን እናመሰግነዋለን። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ምሥክሮች “እስከ ምድር ዳር ድረስ” መስበካቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—የሐዋርያት ሥራ 1:8

a የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ በስብሰባው ላይ አልተሰራጨም፤ ምክንያቱም እንዲህ ለማድረግ በጣም ብዙ መጽሐፍ ቅዱስ ማተም ያስፈልጋል። ሆኖም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በስፓንኛ የሚመሩ ጉባኤዎች መጽሐፍ ቅዱሱ እንደታተመ ይደርሳቸዋል። በተጨማሪም ከሰኞ ሐምሌ 22 አንስቶ፣ የተሻሻለውን ስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ JW Library® ላይ ማግኘት ይቻላል።