ነሐሴ 20, 2020
ሩሲያ
ወንድም ብሪትቪን እና ወንድም ሌቭቹክ ሩሲያ ውስጥ የስድስት ዓመት ተኩል እስር ሊፈረድባቸው ይችላል
የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን
መስከረም 2, 2020፣ a በኬሜሮቮ ግዛት የሚገኘው የቤሬዞቭስኪ ከተማ ፍርድ ቤት
አቃቤ ሕጉ የጠየቀው ፍርድ
የስድስት ዓመት ተኩል እስር
አጭር መግለጫ
ሰርጌ ብሪትቪን
የትውልድ ዘመን፦ 1965 (ኬሜሮቮ ግዛት)
ግለ ታሪክ፦ ለአሥርተ ዓመታት ያህል የዕቃ ማንሻ ክሬን አንቀሳቃሽና የከባድ መኪና ሾፌር ሆኖ ሠርቷል። በጤና ችግር ምክንያት በጊዜ ጡረታ ወጥቷል። ስፖርት መሥራት ይወዳል
በ1992 ናታሊያ ከተባለች ሴት ጋር ትዳር መሠረተ። አምላክ ስለሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ሲያውቅ በ1995 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ናታሊያም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። የሰርጌን እምነትና በእምነቱ ምክንያት ያደረጋቸውን ለውጦች መመልከቷ ይህን እርምጃ እንድትወስድ አነሳስቷታል
ቫዲም ሌቭቹክ
የትውልድ ዘመን፦ 1972 (ኬሜሮቮ ግዛት)
ግለ ታሪክ፦ ያደገው ሃይማኖት የለሽ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ለ14 ዓመታት በማዕድን ማውጫ ውስጥ ሠርቷል
በ1992 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ1997 ታቲያና የተባለች ሴት አገባ። ሁለት ወንዶች ልጆች አሉት። ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ስፖርት መሥራትና ከቤት ውጭ በሚደረጉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መካፈል ያስደስታቸዋል
የክሱ ሂደት
ሐምሌ 22, 2018 የፌዴራል ደህንነት አባላት በቤሬዞቭስኪ ከተማ የሚገኙ የስምንት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈትሸው ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ወንድም ብሪትቪንና ወንድም ሌቭቹክ ተይዘው ለምርመራ ቀረቡ። በኋላም የኬሜሮቮ ማዕከላዊ አውራጃ ፍርድ ቤት ሁለቱም ወንድሞች እስር ቤት ሆነው ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ አዘዘ። አንድ ዓመት ተኩል ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ቆዩ። ታኅሣሥ 25, 2019 ወንድሞች የቁም እስረኛ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን ከዚያ ጊዜ አንስቶ በዚህ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
ወንድም ብሪትቪን እና ወንድም ሌቭቹክ በእምነታቸው ምክንያት ፍርድ እየተጠባበቁ ካሉ በኬሜሮቮ ግዛት የሚኖሩ አምስት ወንድሞች ሁለቱ ናቸው። በሩሲያ በእስር የሚገኙትን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ሁሌም እናስባቸዋለን፤ ደግሞም ስለ እነሱ መጸለያችንን አናቋርጥም። በዕብራውያን 13:3 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን፦ “በእስር ላይ ያሉትን ከእነሱ ጋር ታስራችሁ እንዳላችሁ አድርጋችሁ በማሰብ ሁልጊዜ አስታውሷቸው፤ እናንተም ራሳችሁ ገና በሥጋ ያላችሁ በመሆናችሁ እንግልት እየደረሰባቸው ያሉትን አስቡ።”
a ቀኑ ሊለወጥ ይችላል