በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስከረም 15, 2023
ምያንማር

የማቴዎስ መጽሐፍ በቺን (ሃካ) እና በሚዞ ቋንቋዎች ወጣ

የማቴዎስ መጽሐፍ በቺን (ሃካ) እና በሚዞ ቋንቋዎች ወጣ

የምያንማር ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት በተከታታይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በሁለት ቋንቋዎች መውጣቱን አብስረዋል። መስከረም 3, 2023 ወንድም ሳይ ኅሉዋ በቺን (ሃካ) ቋንቋ፣ ከዚያም መስከረም 10 ወንድም ክሊፍተን ሉድሎው በሚዞ ቋንቋ መውጣቱን አሳውቀዋል።

ቺን (ሃካ)

አስቀድሞ በተቀዳና በ​JW Box በተላከ ልዩ ፕሮግራም አማካኝነት በምያንማር የሚገኙት በቺን (ሃካ) ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች መጽሐፉ መውጣቱን ተበስረዋል። በመላዋ ምያንማር በሚገኙ የተለያዩ የስብሰባ አዳራሾች የታደሙ 397 ሰዎች ፕሮግራሙን ተመልክተዋል። ከፕሮግራሙ በኋላ የታተሙ ቅጂዎች ለታዳሚዎቹ ተሰራጭተዋል። የመጽሐፉ ኤሌክትሮኒክና የድምፅ ቅጂዎችም ለተጠቃሚዎች ተለቅቀዋል።

ቺን (ሃካ) ቋንቋ በዋነኝነት የሚነገረው በሰሜን ምዕራብ ምያንማር በሚገኙት የቺን ኮረብታዎች ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ200,000 የሚበልጡ ተናጋሪዎች አሉት። በምያንማር በቺን (ሃካ) ቋንቋ በሚመሩ አምስት ጉባኤዎችና አንድ ቡድን ውስጥ የሚያገለግሉ ከ220 በላይ አስፋፊዎች አሉ። በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ አንድ ጉባኤና አንድ ቡድን ይገኛሉ።

አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አዲሱን የማቴዎስ መጽሐፍ ትርጉም በአገልግሎት ላይ ለመጠቀም ጓጉቻለሁ። ምክንያቱም ቺን (ሃካ) ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ሁሉ በቀላሉ ሊረዱት ይችላሉ።”

ሚዞ

የመጽሐፉ መውጣት የተበሰረው አስቀድሞ በተቀዳ ፕሮግራም አማካኝነት ነው፤ ፕሮግራሙ በምያንማር በሚገኙ ሁለት የስብሰባ አዳራሾች ተላልፏል። ከንግግሩ በኋላ በቦታው ለተገኙት 173 ተሰብሳቢዎች የመጽሐፉ የታተሙ ቅጂዎች ተሰራጭተዋል፤ የመጽሐፉ ኤሌክትሮኒክና የድምጽ ቅጂዎችም ለተጠቃሚዎች ተለቅቀዋል።

ሚዞ ቋንቋ ቀድሞ የሚታወቀው ሉሼይ በሚል ስም ሲሆን በዋነኝነት የሚነገረው በባንግላዴሽ፣ በምያንማር እና የሕንድ ክፍል በሆነችው በሚዞራም ነው። በዓለም ዙሪያ 1.3 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ይህን ቋንቋ ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት በሕንድና በምያንማር በሚዞ ቋንቋ በሚመሩ አምስት ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 250 ገደማ አስፋፊዎች አሉ።

የቺን (ሃካ) እና የሚዞ የትርጉም ቡድኖች የሚሠሩት በቺን ኮረብታዎች ግርጌ በሚገኝ የርቀት የትርጉም ቢሮ ሆነው ነበር። በአካባቢው በተነሳው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ሚያዝያ 2021 የቡድኖቹ አባላት አካባቢውን ለቅቀው ለመውጣት ተገደዋል። አሁን ተርጓሚዎቹ እየሠሩ ያሉት በያንጎን አዲስ በተቋቋመው የርቀት የትርጉም ቢሮ ነው፤ ይህ ቢሮ ከምያንማር ቅርንጫፍ ቢሮ 4.5 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ይገኛል።

የቺን (ሃካ) እና የሚዞ ተናጋሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ ‘ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውንና ክብራማ የሆነውን ምሥራች’ ለማንበብ አጋጣሚ በማግኘታቸው ተደስተናል።—2 ቆሮንቶስ 4:4