ክርስቲያናዊ ሕይወት
ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?
ፈተናዎች ሲደርሱብህ ልክ እንደ ዳንኤል ፈተናዎቹን በታማኝነት መወጣት ትፈልጋለህ? ዳንኤል ጥልቅ የሆኑ ትንቢቶችን ጨምሮ የአምላክን ቃል በትጋት ያጠና ነበር። (ዳን 9:2) መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናትህ ምንጊዜም ታማኝ እንድትሆን ይረዳሃል። እንዴት? ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች እንደሚፈጸሙ ያለህን እምነት ያጠናክርልሃል። (ኢያሱ 23:14) በተጨማሪም ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ለማሳደግ ይረዳሃል፤ ይህም ትክክል የሆነውን ነገር እንድታደርግ ያነሳሳሃል። (መዝ 97:10) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት የማጥናት ልማድ ለማዳበር ከየት መጀመር ትችላለህ? እስቲ የሚከተሉትን ጠቃሚ ሐሳቦች ተመልከት።
-
ምን ማጥናት እችላለሁ? ጥሩ የጥናት ልማድ፣ ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀትን ይጨምራል። ሳምንታዊውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ስታነብ ግልጽ ባልሆኑልህ ነጥቦች ላይ ምርምር ለማድረግ ጊዜ የምትመድብ ከሆነ ከንባቡ ይበልጥ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ። በተጨማሪም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች፣ ስለ አምላክ መንፈስ ፍሬ የተለያዩ ገጽታዎች፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ስላደረጋቸው ሚስዮናዊ ጉዞዎች ሌላው ቀርቶ ይሖዋ ስለፈጠራቸው ግዑዛን ፍጥረታት ይበልጥ ለማወቅ ምርምር ማድረግ ይቻላል። ከዚህም ሌላ በቀኑ ውስጥ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ ወደ አእምሮህ ከመጣ ጥያቄውን በማስታወሻ ላይ በመጻፍ በቀጣዩ የጥናት ፕሮግራምህ ላይ ምርምር ልታደርግበት ትችላለህ።
-
ምርምር ለማድረግ የትኞቹን መሣሪያዎች መጠቀም እችላለሁ? አንዳንድ አማራጮችን ለማግኘት መንፈሳዊ ዕንቁዎችን ለማግኘት የሚረዱ የምርምር መሣሪያዎች የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት። ለልምምድ ያህል፣ በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ የተጠቀሱት አውሬዎች የትኞቹን የዓለም ኃይሎች እንደሚወክሉ በምርምር ለማግኘት ሞክር።
-
ለጥናት ምን ያህል ጊዜ መመደብ ይኖርብኛል? ቋሚ የጥናት ፕሮግራም በመንፈሳዊ ጤናማ ለመሆን ወሳኝ ነገር ነው። አጠር አጠር ባሉ የጥናት ፕሮግራሞች መጀመርና በጥናት የምታሳልፈውን ጊዜ ቀስ በቀስ እየጨመርክ መሄድ ትችላለህ። የአምላክን ቃል ማጥናት የተሸሸጉ ሀብቶችን ለማግኘት ከመቆፈር ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ የተሸሸጉ ሀብቶችን ባገኘህ ቁጥር ይበልጥ ለመቆፈር ትነሳሳለህ! (ምሳሌ 2:3-6) በተመሳሳይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን የተሸሸጉ ሀብቶች ባገኘህ ቁጥር ለአምላክ ቃል ያለህ ጉጉት እየጨመረ ስለሚሄድ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ቋሚ የሕይወትህ ክፍል ይሆናል።—1ጴጥ 2:2