በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዴረል ሻርፕ | የሕይወት ታሪክ

አምላክ ኃይል ስለሚሰጠን ወደኋላ አናፈገፍግም

አምላክ ኃይል ስለሚሰጠን ወደኋላ አናፈገፍግም

“አንድ ወር እንኳ አይቆይም!” በ1956 ረዳት አቅኚ ሆኜ ለማገልገል ሳመለክት በጉባኤያችን ያሉ አንዳንድ ወንድሞች እንዲህ ብለው ነበር። በወቅቱ 16 ዓመቴ ነበር። ከተጠመቅኩ አራት ዓመት ሆኖኛል። የተጠመቅኩት አንድ የምወደው ወንድም እንድጠመቅ ሐሳብ ስላቀረበልኝ ነው። በዚያን ጊዜ ሽማግሌዎች አንድ ሰው ለጥምቀት ብቁ መሆኑን የሚያጣሩበት ዝግጅት አልነበረም።

 ወንድሞች በአቅኚነት መቀጠሌን የተጠራጠሩበት በቂ ምክንያት ነበራቸው። መንፈሳዊ ሰው አልነበርኩም። አገልግሎት ስለማልወድ እሁድ እሁድ ዝናብ እንዲዘንብ እጸልይ ነበር፤ ምክንያቱም ዝናብ ከዘነበ አገልግሎት አልወጣም። አገልግሎት ከወጣሁም መጽሔት ብቻ አበረክታለሁ እንጂ መግቢያ ተጠቅሜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅስ አንብቤ አላውቅም። ጉባኤ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳነብ ውዷ እናቴ የሆነ ማባበያ ነገር ትሰጠኝ ነበር። ጎበዝ ተማሪ አልነበርኩም፤ መንፈሳዊ ግብም አልነበረኝም።

 በዚያ ዓመት የበጋ ወቅት በካርዲፍ፣ ዌልስ የአውራጃ ስብሰባ (በአሁኑ አጠራሩ የክልል ስብሰባ) ነበር። ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ነገር ያጋጠመኝ እዚህ ስብሰባ ላይ ነው። አንዱ ተናጋሪ አድማጮች ራሳቸውን መለስ ብለው እንዲገመግሙ የሚያደርጉ ጥያቄዎች አንስቶ ነበር። ከጥያቄዎቹ መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ የሚሉ ነበሩ፦ “ራሳችሁን ወስናችሁ ተጠምቃችኋል?” “አዎ” ብዬ ለራሴ መለስኩ። “በሙሉ ልባችሁ፣ ነፍሳችሁ፣ አእምሯችሁና ኃይላችሁ ይሖዋን ለማገልገል ቃል ገብታችኋል?” አሁንም “አዎ” አልኩ። “አቅኚ እንዳትሆኑ የሚያግዳችሁ የጤና ችግር ወይም የቤተሰብ ኃላፊነት አለባችሁ?” “አይ” ብዬ መለስኩ። “አቅኚ እንዳትሆኑ የሚከለክል የተለየ ምክንያት አላችሁ?” አሁንም “አይ” አልኩ። ከዚያም ተናጋሪው “ለመጨረሻው ጥያቄ የሰጣችሁት መልስ ‘አይ’ ከሆነ አቅኚ የማትሆኑት ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀ።

 በድንገት ዓይኔን የጋረደው ነገር የተገፈፈ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። እንዲህ ብዬ አሰብኩ፦ ‘ሕይወቴን እያባከንኩ ነው። ራሴን ስወስን የገባሁትን ቃል እየጠበቅኩ አይደለም። ይሖዋን በሙሉ ነፍሴ እያገለገልኩ አይደለም።’ ከዚያም ‘ይሖዋ ለእኔ የገባውን ቃል እንዲፈጽም የምጠብቅ ከሆነ እኔም ለእሱ የገባሁትን ቃል መፈጸም አለብኝ’ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ ጥቅምት 1956 ረዳት አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ።

በ1959 በአበርዲን ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ

 በቀጣዩ ዓመት የዘወትር አቅኚ ሆኜ 19 አስፋፊዎች ወዳሉበት ጉባኤ ተዛወርኩ። እዚያ ጉባኤ ከተዛወርኩበት ጊዜ አንስቶ በየሳምንቱ ንግግር አቀርብ ነበር። ታጋሽ የሆኑ ወንድሞች ባደረጉልኝ እርዳታ የንግግሬ ይዘትም ሆነ አቀራረቤ እየተሻሻለ ሄደ። ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ1959 ልዩ አቅኚ ሆኜ ተሾምኩ። ከዚያም በስኮትላንድ ሰሜናዊ ጫፍ በሚገኝ አበርዲን የተባለ ቦታ እንዳገለግል ተመደብኩ። ከጥቂት ወራት በኋላ በለንደን ቤቴል እንዳገለግል ተጠራሁ። እዚያ በቆየሁባቸው ሰባት ዓመታት በሕትመት ክፍል ውስጥ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።

 በቤቴል የነበረኝን ሕይወት እወደው ነበር፤ ግን በመስኩ ላይ የማገልገል ፍላጎት አደረብኝ። ወጣትና ጤናማ እንደመሆኔ መጠን ይሖዋ የትኛውም ቦታ ላይ እንዲጠቀምብኝ ፈቃደኛ ነበርኩ። ስለዚህ ሚያዝያ 1965 ጊልያድ ትምህርት ቤት ገብቼ የሚስዮናዊነት ሥልጠና ለማግኘት አመለከትኩ።

 በዚያ ዓመት እኔና የክፍል ጓደኛዬ በትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንዲሁም ከጥቂት ዓመታት በፊት የተገነባውን የበርሊን ግንብ ለማየት ወደ በርሊን፣ ጀርመን ሄድን።

 ስብሰባው ከሚካሄድባቸው ቀናት በአንዱ ላይ በአገልግሎት የመካፈል አጋጣሚ ተከፍቶልን ነበር። እኔ ከሱዛን ባንድሮክ ጋር እንዳገለግል ተመደብኩ። በ1966 ከሱዛን ጋር የተጋባን ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ በ47ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንማር ተጋበዝን። ይህ እንዴት ያለ ትልቅ በረከት ነው! ምንም ሳይታወቀን የአምስት ወሩ ሥልጠና አበቃ። የተሰጠን ምድብ በአሁኑ ጊዜ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ተብሎ የሚጠራው ዛየር ነው። ይህን ስናውቅ በጣም ደነገጥን! ስለዚህ አገር ምንም የምናውቀው ነገር የለም ማለት ይቻላል። ስጋት ቢያድርብንም ምድቡን ለመቀበልና ራሳችንን ለይሖዋ አደራ ለመስጠት ወሰንን።

በ1969 እኔና ሱዛን ከጊልያድ ትምህርት ቤት ተመረቅን

 በአየር ማረፊያዎች ውስጥና በአውሮፕላኖች ላይ ብዙ ሰዓታትን ካሳለፍን በኋላ በመጨረሻ ኮልዌዚ ወደተባለች ማዕድን የሚወጣባት ከተማ ደረስን። ሊቀበለን የመጣ ሰው ባለመኖሩ ግራ ተጋባን። በኋላ እንደተረዳነው ግን ወንድሞች እኛ እንደምንመጣ የሚገልጸው ቴሌግራም የደረሳቸው እኛ ከመጣን ከሁለት ቀን በኋላ ነበር። አንድ የአየር መንገዱ የጸጥታ አስከባሪ ወደ እኛ መጥቶ በፈረንሳይኛ የሆነ ነገር አለን። በወቅቱ ፈረንሳይኛ አንችልም ነበር። ከፊታችን ያለች አንዲት ሴት ወደ እኛ ዞራ “በቁጥጥር ሥር ውላችኋል እያላችሁ ነው” አለችን።

 እኛን ያሰረን የጸጥታ አስከባሪ አንድ መኪና አስቁሞ የመኪናውን ባለቤት እንዲወስደን አዘዘው። መኪናዋ አሮጌ፣ ሞተሯ ከኋላ በኩል ያለና ሁለት ሰው ብቻ የምታስቀምጥ ነበረች። እኔ፣ ሱዛን፣ የጸጥታ አስከባሪውና የመኪናዋ ባለቤት እንደ ምንም ተጨናንቀን መኪናዋ ውስጥ ገባን። በዚያች መኪና ውስጥ ተጭነን ጉድጓዶች በሞሉበት መንገድ ላይ እየተንገጫገጭን ስንሄድ የኮሜዲ ፊልም የምንሠራ ነበር የምንመስለው። ሙሉ በሙሉ ባልገባው ሻንጣችን ምክንያት ገርበብ ብሎ የተዘጋው ኮፈን ወደ ላይ ወደ ታች ሲል መኪናዋ ምግብ በአፉ የያዘ ዓሣ ትመስል ነበር።

 በዚህ መንገድ ሚስዮናውያን ወደሚኖሩበት ቤት ሄድን። እኛ ቤቱ የት እንዳለ ባናውቅም የጸጥታ አስከባሪው አውቆት ነበር። ስንደርስ ቤት ማንም አልነበረም፤ በሮቹም ተቆልፈዋል። ሁሉም ሚስዮናውያን ለዓለም አቀፍ ስብሰባና ለእረፍት ሄደዋል። ጠራራ ፀሐይ ላይ ቆመን ምን እንደምናደርግ ማሰብ ጀመርን። በኋላም በአካባቢው ያለ አንድ ወንድም መጣ። ልክ እንዳየን ፊቱ በፈገግታ ተሞላ። እኛም ተረጋጋን። ወንድም የጸጥታ አስከባሪውን ያውቀው ነበር። በኋላ እንደተረዳነው የጸጥታ አስከባሪው ገንዘብ እንድንሰጠው ፈልጎ ነበር። ወንድም ካነጋገረውና ሁኔታውን ካስረዳው በኋላ ግን የጸጥታ አስከባሪው ሄደ፤ እኛም ወደ ቤታችን ገባን።

በ1971 ናታን ኖር ዛየርን ሊጎበኝ በመጣበት ጊዜ የሚስዮናውያን ቤት ደጅ ላይ ቆመን

ወደኋላ የምናፈገፍግበት ጊዜ አልነበረም

 ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን የተቋቋሙ ደስተኛና አፍቃሪ ሰዎች ጋር እንደተቀላቀልን ለማወቅ ጊዜ አልፈጀብንም። የሚያሳዝነው ግን ላለፉት አሥር ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ግጭትና ብጥብጥ አገሪቱ በዓመፅ እንድትሞላ አድርጎ ነበር። ከዚያ ደግሞ በ1971 የይሖዋ ምሥክሮች ከዚያ በፊት የነበራቸውን ሕጋዊ እውቅና አጡ። ሁኔታውን እንዴት እንደምንወጣው አሳስቦን ነበር።

 ጊዜው በፍርሃት ወደኋላ የምናፈገፍግበት አልነበረም። ወንድሞችና እህቶች ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን የሚፈትን ከባድ ጫና ቢደርስባቸውም በፈተናው የተሸነፉት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። በወቅቱ ሁሉም ሰው የፖለቲካ ፓርቲ ካርድ እንዲይዝና የፓርቲ ባጅ እንዲያደርግ ይጠበቅበት ነበር። ባጁን ያላደረገ ሰው የመንግሥት አገልግሎቶችን ማግኘት የማይችል ከመሆኑም ሌላ ከወታደሮችና ከፖሊሶች እንግልት ይደርስበት ነበር። ወንድሞች ሥራቸውን አጥተዋል፤ ልጆችም ከትምህርት ቤት ተባረዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞች ለእስር ተዳርገዋል። በጣም ከባድ ጊዜ ነበር። ያም ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በድፍረት መስበካቸውን አላቆሙም።

መጽናት አስፈልጎናል

 በእነዚያ ዓመታት እኔና ሱዛን አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው በወረዳና በአውራጃ ሥራ ምክንያት ወደ ገጠራማ አካባቢዎች በመጓዝ ነበር። የገጠር ሕይወት ለየት ያሉ፣ አንዳንዴም ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ይጠይቃል። እናርፍባቸው የነበሩት ደሳሳ የሣር ጎጆዎች ለመተኛ እንኳ በቂ ቦታ አልነበራቸውም። የጎጆዎቹ በሮች አጫጭር ስለነበሩ ወደ ውስጥ ለመግባት ስሞክር ብዙ ጊዜ ጭንቅላቴን ተመትቻለሁ። ገላችንን የምንታጠበው ከጅረቶችና ከወንዞች በተቀዳ ውኃ ነበር። ማታ ላይ የምናነበው በሻማ ነው። ምግባችንን የምናበስለው ደግሞ በከሰል ነው። ግን ትክክለኛ የሚስዮናዊ ሕይወት ብለን የምናስበው ይህን ነበር፤ የመጣነው ለዚህ ነው። በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ ግንባር ላይ እንደተሰለፍን አድርገን ስለቆጠርነው ደስተኞች ነበርን።

 በአካባቢው ካሉ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች ጋር ስንኖር እኛ እንደ ተራ ነገር አድርገን የምንቆጥራቸው እንደ ምግብ፣ ውኃ፣ ልብስና መጠለያ ያሉ ነገሮች ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ተምረናል። ከእነዚህ ውጭ ያለው ነገር ሁሉ ትርፍ ነው። ይህ እውነታ አሁንም ድረስ በውስጣችን ተቀርጾ ቀርቷል።

 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳጋጠሙት ያሉ ፈተናዎች አጋጥመውን ባያውቁም አንዳንድ የምናደርጋቸው ጉዞዎች እምነታችንንና ውስጣዊ ዝንባሌያችንን የሚፈትኑ ነበሩ። በጣም በተበላሹ መንገዶች ላይ ወይም ጭራሽ መንገድ እንኳ ባልተሠራባቸው አካባቢዎች መጓዝ አስፈልጎናል። ድንጋያማ በሆኑ መንገዶች ላይ ስንጓዝ መኪናችን በጣም ይንገጫገጭ ነበር። አንዳንዴ ደግሞ አሸዋ ውስጥ ገብቶ ይቀረቀራል። ዝናባማ በሆኑ ወቅቶች መኪናችን እንደ ሙጫ በሚያጣብቅ ጭቃ ውስጥ ገብቶ አልንቀሳቀስ ይላል። በአንድ ወቅት ሙሉ ቀን ብንጓዝም የነዳነው 70 ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር፤ አሥራ ሁለት ጊዜ መኪናችንን ከተቀረቀረበት ማውጣት ነበረብን።

በምድባችን ስናገለግል ብዙ ጊዜ መንገድ ላይ ችግር ያጋጥመን ነበር

 ሆኖም ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ስናገለግል የነበረበትን ጊዜ ያህል ወደ ይሖዋ እንደቀረብን ተሰምቶን አያውቅም። አንድን ከባድ ሁኔታ መለወጥ በማንችልበት ጊዜም እንኳ በይሖዋ እርዳታ በደስታ መጽናት እንደምንችል ተምረናል። ሱዛን በተፈጥሮዋ ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝና አዳዲስ ነገሮችን መሞከር የምትወድ ዓይነት ሰው አይደለችም። ግን በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት አንዴም አጉረምርማ አታውቅም። እነዚያ ጊዜያት አስደሳች፣ አርኪና ብዙ ትምህርት ያገኘንባቸው ናቸው።

 ዛየር ውስጥ በቆየንባቸው ዓመታት በተደጋጋሚ ታስሬያለሁ። በአንድ ወቅት ሕገ ወጥ በሆነ የአልማዝ ንግድ ተሰማርተሃል በሚል ተከስሼ ነበር። እውነት ለመናገር ሁኔታው አስጨንቆን ነበር። ግን ‘ይሖዋ የተመደብንበትን አገልግሎት እንድናከናውን የሚፈልግ ከሆነ ያለጥርጥር ይረዳናል’ ብለን አሰብን። ደግሞም ረድቶናል!

በይሖዋ አገልግሎት ወደፊት መግፋት

 በ1981 በኪንሻሳ ባለው ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል ተጠራን። ከአንድ ዓመት በፊት ሥራችን በድጋሚ ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ ነበር። በዚህም የተነሳ ወንድሞች ተለቅ ያለ ቅርንጫፍ ቢሮ ለመገንባት መሬት ገዝተው ነበር። ከዚያ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ መጋቢት 1986 የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እንዲታገድ በሚያዝዝ ሰነድ ላይ ፈረመ። የግንባታ ሥራው ቆመ፤ ብዙም ሳይቆይ አብዛኞቹ ሚስዮናውያን አገሪቱን ለቀው ወጡ።

ለጥቂት ዓመታት፣ በዛየር ቅርንጫፍ ቢሮ አገልግለናል

 እኛ ግን የተወሰነ ጊዜ ያህል መቆየት ችለን ነበር። ጥብቅ ክትትል እየተደረገብን እንዳለ ብናውቅም መስበካችንን ለመቀጠል የቻልነውን ሁሉ አደረግን። የምንሰብከው በከፍተኛ ጥንቃቄ ቢሆንም አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠናሁ ሳለ ታሰርኩ። በእስረኞች የተጨናነቀ ጨለማ ክፍል ውስጥ አስገቡኝ። ክፍሉ በጣም የሚሞቅ፣ የሚሸትና የታፈነ ነበር፤ ብርሃንና አየር የሚገባው በአንዱ ግድግዳ ላይ ባለች ትንሽ ቀዳዳ ብቻ ነበር። አንዳንድ እስረኞች ያዙኝና ራሳቸው በሾሙት አለቃቸው ፊት አቀረቡኝ። አለቃቸው “ብሔራዊ መዝሙራችንን ዘምር!” ብሎ አዘዘኝ። እኔም “አላውቀውም” ብዬ መለስኩለት። ከዚያም “እሺ፣ የአገርህን ብሔራዊ መዝሙር ዘምር!” አሉኝ። እኔም “እሱንም አላውቀውም” አልኳቸው። በዚህ የተነሳ አለቃው ለ45 ደቂቃ ያህል ወደ ግድግዳ ዞሬ እንድቆም አደረገኝ። ከጊዜ በኋላ በአካባቢው ያሉ ወንድሞች ተደራድረው አስፈቱኝ።

በ1987 ዛምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ከደረስን ከጥቂት ጊዜ በኋላ

 በአገሪቱ ያለው ሁኔታ የመሻሻል አዝማሚያ እንደሌለው ያስታውቅ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ዛምቢያ እንድናገለግል ተመደብን። ድንበሩን ተሻግረን ስንወጣ የተደበላለቀ ስሜት ተሰማን። በአንድ በኩል ብናዝንም በሌላ በኩል ግን እፎይታ ተሰማን። ታማኝ ከሆኑ ሚስዮናውያን እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር አብረን በአገልግሎት ስላሳለፍናቸው 18 ዓመታት መለስ ብለን አሰብን። አንዳንዴ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም የይሖዋን በረከት በግልጽ አይተናል። ይሖዋ ምንጊዜም ከእኛ እንዳልተለየ ተመልክተናል። ስዋሂሊና ፈረንሳይኛ ተምረናል፤ ሱዛን ደግሞ የተወሰነ ሊንጋላ ተምራለች። በአገልግሎታችን አስደሳች ውጤት አግኝተናል። ከ130 የሚበልጡ ሰዎች እንዲጠመቁ ረድተናል። ወደፊት ለሚኖረው እድገት መሠረት በመጣል ረገድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንዳደረግን ስለምናውቅ ውስጣዊ እርካታ ይሰማናል። ደግሞም በአገሪቱ አስደናቂ እድገት ተገኝቷል! በ1993 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በ1986 የተጣለውን እገዳ አነሳ። በአሁኑ ጊዜ በኮንጎ ከ240,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች አሉ።

 ዛምቢያ በነበርንበት ጊዜ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ሲገነባ፣ ከዚያም ሌሎች የማስፋፊያ ሥራዎች ሲሠሩ ተመልክተናል። አሁን በዚያ ያሉት አስፋፊዎች ቁጥር እኛ በ1987 ስንመጣ ከነበረው የአስፋፊዎች ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ ሆኗል።

የዛምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ከላይ ሲታይ

 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አንድ ወር እንኳ አይቆይም የተባለው ያ ወጣት ወንድም አሁን የት ደረሰ? በይሖዋ በረከትና በውዷ ባለቤቴ በሱዛን ድጋፍ ይኸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አስደሳች የሆኑ 65 ዓመታትን አሳልፌያለሁ። ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሼ ማየት ችያለሁ!—መዝሙር 34:8

 እኛ የተለየን ሰዎች አይደለንም፤ ብቻ ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ቃል ለመፈጸም የቻልነውን ሁሉ አድርገናል። ይሖዋ ፈጽሞ ወደኋላ ‘እንዳናፈገፍግ’ ከዚህ ይልቅ “በሕይወት የሚያኖር እምነት” ማዳበራችንን እንድንቀጥል እንደሚረዳን እርግጠኞች ነን።—ዕብራውያን 10:39

እኔና ሱዛን አሁንም በዛምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ እያገለገልን ነው

 ዴረል እና ሱዛን ሻርፕ፦ ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ለማገልገል ቃል ገብተናል የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።