የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
የእርዳታ ሥራ በ2022—የወንድማማች ፍቅር በተግባር ሲገለጽ
ጥር 1, 2023
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የምንኖርበት ዘመን በጦርነቶች፣ በምድር ነውጦች፣ በቸነፈርና በሌሎች “የሚያስፈሩ ነገሮች” ተለይቶ እንደሚታወቅ አስቀድሞ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:10, 11) ይህ ትንቢት በ2022 የአገልግሎት ዓመትም ፍጻሜውን ማግኘቱን ቀጥሎ ነበር። ለምሳሌ በዩክሬን የተከሰተው ጦርነት አሁንም አላባራም፤ ጦርነቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ይህ ነው የማይባል ጉዳት አድርሷል። አብዛኛው የዓለማችን ክፍል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካስከተለው ጉዳት ገና አላገገመም። በተጨማሪም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በተፈጥሮ አደጋዎች ተጠቅተዋል፤ ለምሳሌ በሄይቲ የምድር ነውጥ ተከስቶ ነበር፤ በማዕከላዊ አሜሪካ፣ በፊሊፒንስና በደቡብ ምሥራቃዊ አፍሪካ ደግሞ አውዳሚ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከስቶ ነበር። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ አደጋዎች የተጎዱ ሰዎችን የረዱት እንዴት ነው?
በ2022 የአገልግሎት ዓመት ድርጅታችን 200 ገደማ በሚሆኑ አደጋዎች ለተጎዱ የእምነት አጋሮቻችን እርዳታ አድርሶ ነበር! ለእርዳታ ሥራው በድምሩ 12 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ አውጥተናል። a በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ በሁለት አደጋዎች የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት የዋለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
በሄይቲ የተከሰተ የምድር ነውጥ
ነሐሴ 14, 2021 ደቡባዊ ሄይቲ በመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ 7.2 በተመዘገበ የምድር ነውጥ ተመታች። የሚያሳዝነው ሁለት እህቶችና አንድ ወንድም ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከአደጋው የተረፉት ደግሞ የምድር ነውጡ ካስከተለው አካላዊና ስሜታዊ ጉዳት ጋር መታገል አስፈልጓቸዋል። ስቴፋን የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በከተማዋ ውስጥ ብዙ ሰው ከማለቁ የተነሳ ለሁለት ወር ያህል በየሳምንቱ ብዙ ለቅሶ ቤቶች ነበሩ።” ኤሊዔዘር የተባለ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች መጠለያ፣ ልብስ፣ ጫማ ወይም ሌሎች መሠረታዊ ቁሳቁሶች አልነበሯቸውም። ከዋናው ነውጥ በኋላ ለተከታታይ ወራት ትናንሽ ነውጦች ይከሰቱ ስለነበር ብዙዎች ኑሯቸው ስጋት የሞላበት ነበር።”
ድርጅታችን ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደ። የሄይቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ከ53 ቶን በላይ ምግብ እንዲሁም ድንኳን፣ ሸራ፣ ፍራሽና በፀሐይ የሚሠራ የስልክ ቻርጀር አከፋፈለ። ከዚህም ሌላ በ2022 የአገልግሎት ዓመት ከ100 በላይ ቤቶች እንደገና ተገንብተዋል ወይም ታድሰዋል። ለእርዳታ ሥራው ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥተናል።
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለተደረገላቸው እርዳታ በጣም አመስግነዋል። ሎሬት እንዲህ ብላለች፦ “የምድር ነውጡ ቤታችንንና ንግዳችንን ሙሉ በሙሉ አውድሞብናል። የምንበላው ነገር እንኳ አልነበረንም። ሆኖም የይሖዋ ድርጅት ከጎናችን ሆኖ የሚያስፈልገንን ነገር በሙሉ አቅርቦልናል።” ሚሸሊን ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “የምድር ነውጡ እኔና ሁለት ልጆቼ የምንኖርበትን ቤት አፈረሰብን። እርዳታ ለማግኘት ከመጸለይ በቀር ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገብቶኝ ነበር፤ ይሖዋ ግን በድርጅቱ አማካኝነት ጸሎታችንን መልሶልናል። አሁን ምቹ ቤት አግኝተናል። ለይሖዋ ያለኝን አመስጋኝነት ለማሳየት አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጫለሁ።”
የእርዳታ ሥራችን ከባለሥልጣናቱ ዓይን አልተሰወረም። የላዚል ከተማ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ እንዲህ ብለዋል፦ “ፈጥኖ ደራሽ በመሆናችሁ ልትመሰገኑ ይገባል። ለባለሥልጣናት የምታሳዩት ታላቅ አክብሮት የሚደነቅ ነው። እናንተ የምትፈልጉት ሰዎችን መርዳት እንጂ ገንዘብ መሰብሰብ አለመሆኑ አስደስቶኛል። እርምጃ ለመውሰድ የሚያነሳሳችሁ ፍቅር ነው።”
ማላዊ እና ሞዛምቢክ አና በተባለችው አውሎ ነፋስ ተመቱ
ጥር 24, 2022 አና የተባለችው አውሎ ነፋስ መጀመሪያ ሞዛምቢክን ከዚያም በስተ ምዕራብ የምትገኘውን ማላዊን መታች። በዚህም የተነሳ ከባድ ዝናብና እስከ 100 ኪሎ ሜትር በሰዓት የሚጓዝ ኃይለኛ ነፋስ ተከስቷል። ይህም የኃይል መቋረጥ አስከትሏል፤ ድልድዮችን አፍርሷል እንዲሁም መጠነ ሰፊ የጎርፍ መጥለቅለቅ አስከትሏል።
አውሎ ነፋሱ በማላዊና በሞዛምቢክ በሚኖሩ ከ30,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጉዳት አድርሷል። በእርዳታ ሥራው የተካፈለ ቻርልስ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች የደረሰባቸውን መከራና ያጡትን ነገር ስመለከት ልቤ ተሰበረ፤ አቅመ ቢስ እንደሆንኩ ተሰማኝ።” በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ የነበራቸው ጥቂት ምግብና ሰብላቸው በጎርፉ ተወሰደ። ብዙዎች ቤታቸውን አጥተዋል። የሚያሳዝነው የአንድ ወንድም ቤተሰቦች ሕይወት አድን ጀልባቸው በመገልበጡ የተነሳ ወንድማችን ባለቤቱንና ሁለት ትናንሽ ልጆቹን በሞት ተነጥቋል።
አውሎ ነፋሱ እጅግ አስፈሪ ነበር። በንቻሎ፣ ማላዊ የሚኖሩት የወንድም ሴንጌሬዶ ቤተሰቦች ከሌሊቱ 7:00 ላይ አስፈሪ የሆነውን የጎርፍ ድምፅ ሰሙ። ሁለት ወንዞች ተጥለቅልቀው ነበር! ወንድም ሴንጌሬዶና ቤተሰቡ ቤታቸውን ለቀው ለመሄድ ወሰኑ። ይህ የጥበብ እርምጃ ነበር፤ ምክንያቱም ብዙም ሳይቆይ ጎርፉ ቤታቸውን አፈረሰው። ንብረቶቻቸው በሙሉ ወይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይ በጎርፍ ተወስደዋል። ቤተሰቡ በስብሰባ አዳራሹ ለመጠለል ወሰኑ። ሌላ ጊዜ ቢሆን መንገዱ የሚፈጅባቸው 30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ብቻ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ግን ሁለት ሰዓት ፈጀባቸው። በዝናብ በስብሰውና ደክሟቸው ቢሆንም በሰላም መድረስ ችለዋል።
የማላዊና የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ወዲያውኑ የእርዳታ እንቅስቃሴ ጀመሩ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች በአደጋው የተጠቁት ወንድሞች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንዲገመግሙ እንዲሁም መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ እንዲሰጡ ከቅርንጫፍ ቢሮዎቹ መመሪያ ተሰጣቸው። የእርዳታ ሥራውን የሚያስተባብሩ በርካታ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ፤ እነዚህ ኮሚቴዎች ወዲያውኑ ለወንድሞቻችን ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ለማቅረብ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ከ33,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ፣ ቤቶችን መልሶ ለመገንባትና ለማደስ ደግሞ ከ300,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ አውጥተናል።
የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ ገንዘቡን በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል፤ በተለይ ከነበረው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አንጻር እንዲህ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነበር። ለምሳሌ የእርዳታ ሥራው ከተጀመረ በኋላ በነበሩት ሰባት ወራት ውስጥ የማላዊ ዋነኛ ምግብ የሆነው በቆሎ ዋጋው በ70 በመቶ ገደማ ጨምሯል። የነዳጅ ዋጋም ንሯል። ወንድሞች ገንዘብ ለመቆጠብ ሲሉ ምግብና የግንባታ ቁሳቁሶችን በአካባቢው ከሚገኙ አቅራቢዎች በጅምላ ለመግዛት ወስነዋል። በዚህ መንገድ የዋጋ ቅናሽ ማግኘትና የትራንስፖርት ወጪ መቀነስ ችለዋል።
የይሖዋ ሕዝቦች በእርዳታ ሥራው ልባቸው ተነክቷል። በሞዛምቢክ የሚኖር ፌሊስቤርቶ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ያህል የግንባታ ቁሳቁስ፣ ማጓጓዣ፣ የግንባታ ሠራተኞች፣ ምግብና ፍቅራዊ አመራር የሰጠ ድርጅት አይቼ አላውቅም። ይህ የእርዳታ ሥራ ኢየሱስ በዮሐንስ 13:34, 35 ላይ የጠቀሰውን የወንድማማች ፍቅር የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው።” በማላዊ የምትኖረው ኤስተር ቤቷ ፈርሶባታል፤ እንዲህ ብላለች፦ “ሌላ ቤት ለመገንባት አቅም ስለሌለኝ ተስፋ ቆርጬ ነበር። ስለዚህ ወንድሞች መጥተው ቤት ሲሠሩልኝ ገነት እንደገባሁ ነው የተሰማኝ።”
ወደ አዲሱ ዓለም እየተቃረብን ስንሄድ ተጨማሪ አደጋዎች እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን። (ማቴዎስ 24:7, 8) ያም ቢሆን በልግስና መዋጮ ስለምታደርጉ የይሖዋ ሕዝቦች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንደሚያገኙ እርግጠኞች ነን። መዋጮ ማድረግ የሚቻልባቸውን መንገዶች donate.jw.org ላይ ማግኘት ይቻላል። ለልግስናችሁ ከልብ እናመሰግናለን።
a የ2022 የአገልግሎት ዓመት መስከረም 1, 2021 ጀምሮ ነሐሴ 31, 2022 አልቋል።