በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

የእርዳታ ሥራ በ2021—ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አልተተዉም

የእርዳታ ሥራ በ2021—ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አልተተዉም

ጥር 1, 2022

 በ2021 የአገልግሎት ዓመት a ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መታመሱን ቀጥሎ ነበር። “በዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ዓለም አቀፍ እርዳታ መስጠት” በሚለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው በኮቪድ-19 የተጎዱትን ለመርዳት በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር አውጥተናል፤ እንዲሁም ከ950 የሚበልጡ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁመናል።

 ወረርሽኙ ዓለምን እያናወጠ በነበረበት ወቅት በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቻችን በሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎችም ተጠቅተዋል። ከ200 በሚበልጡት አደጋዎች የተጎዱትን ወንድሞችና እህቶች ለመርዳት የበላይ አካሉ የአስተባባሪዎች ኮሚቴ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተሰጠው እርዳታ በተጨማሪ 8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለእርዳታ ሥራ እንዲውል ፈቅዷል። የምታደርጉት መዋጮ በቅርቡ በተከሰቱ ሁለት አደጋዎች የተጎዱትን ለመርዳት የዋለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የኒራጎንጎ ተራራ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ

 ግንቦት 22, 2021 በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ በሚገኘው በኒራጎንጎ ተራራ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ተከሰተ። ከዚያ የፈሰሰው የቀለጠ ድንጋይ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችንና አንድን የውኃ ማጠራቀሚያ ግድብ አውድሟል። ሆኖም ጉዳት ያስከተለው የቀለጠው ድንጋይ ብቻ አልነበረም። የእሳተ ገሞራ ፍንዳታው ከተከሰተ በኋላ ባሉት ቀናት እሳተ ገሞራው የሚተፋው መርዛማ አመድ የጎማ ከተማን ሞልቶት ነበር። በተጨማሪም በርካታ ትናንሽ የምድር ነውጦች ተከስተዋል። ከከተማው ነዋሪዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ታዘው ነበር። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ሸሽተዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ድንበር ተሻግረው ሩዋንዳ ገብተዋል።

የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው በስብሰባ አዳራሽ ግቢ ውስጥ ትኩስ አጥሚት ሲያቀርብ

 መኖሪያቸውን ለቀው ከተሰደዱት መካከል 5,000 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። አንዳንዶቹ በእሳተ ገሞራው ምክንያት ቤታቸው ወድሞባቸዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ አካባቢውን ለቀው ከሸሹ በኋላ ቤታቸው ተዘርፏል። በሩዋንዳና በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሚገኙ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች የእርዳታ ሥራውን አስተባብረዋል። የኮንጎ (ኪንሻሳ) ቅርንጫፍ ቢሮ ስለ አንደኛው የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከተማው ተተራምሶ ነበር፤ ያም ቢሆን ገና ነዋሪዎቹ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ከመታዘዛቸው በፊት እንኳ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው ምግብ፣ ውኃ፣ መተኛ እና አልባሳት ማከፋፈል ጀምሮ ነበር።” ከ2,000 የሚበልጡ ወንድሞቻችን ሸሽተው በሄዱበት አንድ ከተማ ውስጥ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው ድንኳን ተክሏል፤ ማስክ አከፋፍሏል፤ እንዲሁም ኮቪድ-19⁠ንና ኮሌራን መከላከል ስለሚቻልበት መንገድ ትምህርት ሰጥቷል።

ምግብ የያዙ ከረጢቶች ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ወንድሞች ከመከፋፈላቸው በፊት ሲመዘኑ

 አደጋው ከደረሰ በኋላ ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ ወንድሞቻችን ቢያንስ ስድስት ቶን ሩዝ፣ ስድስት ቶን የበቆሎ ዱቄት፣ ሦስት ቶን የምግብ ዘይት እንዲሁም ሦስት ቶን ውኃ አከፋፍለዋል። ቅርንጫፍ ቢሮው ገንዘብ ለመቆጠብ ሲል፣ ከውጭ አገር ውድ ምግብ ከማስመጣት ይልቅ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የምግብ ቁሳቁሶችን በጅምላ ገዝቷል።

 አዲሱ ቤቷ በእሳት ገሞራው ምክንያት የወደመባት አንዲት እህት “በጣም አዝነንና ተስፋ ቆርጠን ነበር” ብላለች። ሆኖም ቤተሰቧ ቁሳዊና መንፈሳዊ እርዳታ አግኝቷል። እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ እርዳታ ስላልተለየን የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ አለን። ይሖዋ ሸክማችንን ስለተሸከመልን ጫናው ቀንሶልናል።”

የቬኔዙዌላ የኢኮኖሚ ውድቀት

 ቬኔዙዌላ ለበርካታ ዓመታት በከባድ የኢኮኖሚ ውድቀት ስትማቅቅ ቆይታለች። በዚያ ያሉ ወንድሞቻችን በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ፣ በምግብ እጥረት እንዲሁም በወንጀል መበራከት የተነሳ እየተሠቃዩ ነው። ሆኖም የይሖዋ ድርጅት አልተዋቸውም።

ወደተለያዩ የቬኔዙዌላ ክፍሎች የሚላክ ሩዝ መኪና ላይ ሲጫን

 ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ውስጥ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ቤተሰቦች ምግብና ሳሙና ለመግዛት እንዲሁም ለማጓጓዝ ከ1.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጥቷል። የቬኔዙዌላ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ብሏል፦ “በየወሩ 130 ቶን ምግብ ወደ አራቱም የአገሪቱ ማዕዘኖች ማጓጓዝና ወደተቸገሩት ወንድሞቻችን እጅ እንዲገባ ማድረግ ቀላል አይደለም።” ምግቡ እንዳይበላሽ ብዙውን ጊዜ ወንድሞቻችን የሚልኩት ረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል ምግብ ነው። ቅርንጫፍ ቢሮው አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ምግቡን በጅምላና በሚመረትበት ጊዜ ስለምንገዛ ረከስ ባለ ዋጋ ማግኘት እንችላለን። ከዚያም ከሁሉ ይበልጥ ወጪ ቆጣቢ የሆነውን ዘዴ ተጠቅመን እናጓጉዘዋለን።”

ከፍተኛ የነዳጅና የተሽከርካሪ እጥረት ስላለ ወጣት ወንድሞች ለጉባኤያቸው ምግብ ለማድረስ ሲሉ ደርሶ መልስ 18 ኪሎ ሜትር በብስክሌት ይጓዛሉ

 ቬኔዙዌላ ውስጥ በአንድ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለው ሊዮኔል የተሰጠውን ኃላፊነት በጣም ይወደዋል። እንዲህ ብሏል፦ “የእርዳታ ሥራ ልዩ ነገር ነው። በዚህ ሥራ መካፈሌ ውዷን ባለቤቴን በኮቪድ-19 ምክንያት ካጣሁበት ጊዜ አንስቶ በጣም አጽናንቶኛል። በሥራ እንድጠመድ ረድቶኛል፤ እንዲሁም ለተቸገሩት ወንድሞች ጠቃሚ እርዳታ እንደማበረክት ይሰማኛል። ይሖዋ ሕዝቦቹን እንደማይተው የገባውን ቃል እንዴት እንደሚፈጽም በገዛ ዓይኔ ተመልክቻለሁ።”

 እርዳታ ከተሰጣቸው ወንድሞች አንዱ፣ እሱ ራሱም ከዚያ ቀደም በአንድ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ ያገለግል ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አሁን እኔም በተራዬ እርዳታ አስፈልጎኛል። ያገኘነው ቁሳዊ እርዳታ ብቻ አይደለም። ወንድሞች እኔና ባለቤቴ እንድንረጋጋ ረድተውናል። ተንከባክበውናል፤ አጽናንተውናል፤ እንዲሁም አበረታተውናል።”

 አንዳንድ አደጋዎች የሚከሰቱት ያለምንም ማስጠንቀቂያ ነው ሊባል ይችላል። ያም ቢሆን የይሖዋ ድርጅት ብዙውን ጊዜ የእርዳታ ቁሳቁሶችን በፍጥነት ማሰባሰብና ማሰራጨት ይችላል። ይህ ሊሆን የቻለው ለዓለም አቀፉ ሥራ በምታደርጉት መዋጮ የተነሳ ነው። መዋጮ ማድረግ የሚቻልባቸውን አንዳንድ መንገዶች በ​donate.jw.org ላይ ማግኘት ይቻላል። የምታሳዩትን የልግስና መንፈስ ከልብ እናደንቃለን።

a የ2021 የአገልግሎት ዓመት መስከረም 1, 2020 ጀምሮ ነሐሴ 31, 2021 አልቋል።