የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
ሕይወት የሚቀይሩ ነጠብጣቦች
ጥቅምት 1, 2021
የሰኔ 1, 1912 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “አብዛኞቹ አንባቢዎቻችን ዓይነ ስውር የሆኑ ሰዎችን እንደሚያውቁ ጥርጥር የለውም። . . . እነዚህ ሰዎች የሚነበብ ጽሑፍ በነፃ ማግኘት ይችላሉ። . . . ለዓይነ ስውራን የተዘጋጀው ይህ ጽሑፍ የሚታተመው ዓይነ ስውራን ሊያነቧቸው የሚችሏቸውን ጉብ ጉብ ያሉ ፊደላት በመጠቀም ነው።” አክሎም መጠበቂያ ግንቡ እንዲህ ይላል፦ “በርካታ ዓይነ ስውራን ታላቅ የበረከት ቀን ወደ ዓለም እየመጣ መሆኑን የሚገልጸውን መልእክት በጣም ወደውታል።”
ይህ ሐሳብ በተጻፈበት ወቅት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወጥ የሆነ የብሬይል አጻጻፍ አልነበረም። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ ዘመንም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ‘ጉብ ጉብ ባሉ ፊደላት’ ማለትም በብሬይል ያቀርቡ ነበር። አሁንም እንዲህ ማድረጋችንን ቀጥለናል! በአሁኑ ወቅት ከ50 በሚበልጡ ቋንቋዎች የብሬይል ጽሑፎችን እናዘጋጃለን። ይሁንና የብሬይል ጽሑፎች የሚዘጋጁት እንዴት ነው?
መገልበጥ እና መቅረጽ
የብሬይል ጽሑፍ ሲዘጋጅ የመጀመሪያው ሂደት ጽሑፉን በብሬይል ፊደላት መገልበጥ ነው። በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የጽሑፍ ንድፍ ክፍል የሚያገለግለው ወንድም ማይክል ሚለን እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል ጽሑፎችን በብሬይል ፊደላት ለመገልበጥ ገበያ ላይ ያሉ ሶፍትዌሮችን እንጠቀም ነበር፤ ሆኖም እነዚህ ሶፍትዌሮች እኛ የምንፈልጋቸውን ቋንቋዎች በሙሉ ያካተቱ አልነበሩም። አሁን የምንጠቀመው ዎችታወር ትራንስሌሽን ሲስተም የተባለውን ሶፍትዌር ነው፤ ይህ ሶፍትዌር በአብዛኞቹ የዓለማችን ቋንቋዎች የብሬይል ፊደላትን ለመገልበጥ ያስችላል። እንዲህ ያለ ሌላ ፕሮግራም ያለ አይመስለኝም።”
የብሬይል ጽሑፎች ምንባቡን ብቻ ሳይሆን የሥዕሎቹን መግለጫዎችም ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል በብሬይል የተዘጋጀው ለዘላለም በደስታ ኑር! ሽፋኑ ላይ “አንድ ሰው በሚያማምሩ አትክልቶች፣ ኮረብቶችና ተራሮች መሃል በጠመዝማዛ መንገድ ላይ መጓዝ ሲጀምር” የሚል መግለጫ አለው። ዓይነ ስውር የሆነው እና በጉባኤ አገልጋይነትና በአቅኚነት የሚያገለግለው ያምሼድ “የሥዕሎቹ መግለጫዎች በጣም ይጠቅሙኛል” ብሏል።
ጽሑፉ በብሬይል ፊደላት ከተገለበጠ በኋላ ፋይሉ የብሬይል ጽሑፎችን ወደሚቀርጹ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይላካል። በዚያም ጽሑፉ በጠንካራ ወረቀት ላይ ይቀረጻል፤ ወረቀቱ በጣም ጠንካራ ስለሆነ ፊደላቱ ሲቀረጹበት አይቀደድም፤ እንዲሁም ረጅም ጊዜ ቢያገለግልም አይተጣጠፍም። ቀጥሎ ወረቀቶቹ ተሰብስበው ይጠረዛሉ፤ ከዚያም ከመደበኛው የጉባኤ የጽሑፍ ትእዛዝ ጋር ይላካሉ፤ ወይም ደግሞ “ለዓይነ ስውራን ነፃ ጽሑፎች” በሚልኩ ፖስታ ቤቶች አማካኝነት ይላካሉ። ዓይነ ስውራን ወይም የማየት ችግር ያለባቸው ወንድሞች ለጉባኤ ስብሰባቸው ጽሑፍ በሰዓቱ እንዲደርሳቸው ሲባል አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ የብሬይል ጽሑፎቹን በፈጣን የመላኪያ አገልግሎት ይልኳቸዋል።
ይህ ሁሉ ሥራ ብዙ ጊዜና ገንዘብ ይፈልጋል። እንዲያውም በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው ማተሚያ ቤታችን 50,000 መደበኛ መጽሐፍ ቅዱሶችን ለማተም የሚወስድበት ሰዓትና 2 የብሬይል መጽሐፍ ቅዱሶችን ለማዘጋጀት የሚፈጀው ጊዜ እኩል ነው። በደረጃ ሁለት የእንግሊዝኛ ብሬይል የሚዘጋጀው እያንዳንዱ መጽሐፍ ቅዱስ 25 ጥራዝ አለው፤ እነዚህን ጥራዞች ለማዘጋጀት የሚጠይቀው ወጪ መደበኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለማተም ከሚጠይቀው ወጪ በ123 እጥፍ ይበልጣል። a የእነዚህን 25 ጥራዞች ሽፋን ለማዘጋጀት ብቻ እንኳ 150 የአሜሪካ ዶላር ይወስዳል!
የብሬይል ጽሑፎችን በማዘጋጀት ሥራ የሚካፈሉ ወንድሞችና እህቶች ስለ ሥራቸው ምን ይሰማቸዋል? በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ የምታገለግለው ናዲያ እንዲህ ብላለች፦ “ዓይነ ስውር ለሆኑ ወይም የማየት ችግር ላለባቸው ወንድሞቻችን ሕይወት በጣም ከባድ ነው፤ ስለዚህ እነሱን የሚረዳ ነገር ማድረግ መቻሌን እንደ በረከት እቆጥረዋለሁ። ይሖዋ በጣም እንደሚወዳቸው በግልጽ ማየት ይቻላል።”
ብሬይል ማንበብ ተማሩ
ይሁንና ዓይነ ስውር የሆነ አንድ ሰው ብሬይል ማንበብ የማይችል ከሆነስ? ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ብሬይል ማንበብ ተማሩ የሚል መማሪያ ብሮሹር አዘጋጅተን ነበር፤ ይህ ብሮሹር በብሬይልና በሕትመት ፊደላት የተዘጋጀ ነው። ብሮሹሩ በዚህ መንገድ የተዘጋጀው አንድ ዓይነ ስውር ማየት ከሚችል ሰው ጋር ሆኖ እንዲጠቀምበት ታስቦ ነው። ብሬይል ለመጻፍ የሚያገለግሉ መሣሪያዎችም ከብሮሹሩ ጋር አብረው ይካተታሉ። ብሬይል የሚማረው ግለሰብ በእነዚህ መሣሪያዎች ተጠቅሞ የብሬይል ፊደላቱን መቅረጽ ይችላል። በዚህ መንገድ ፊደላቱን ራሱ መቅረጹ ፊደላቱን በደንብ እንዲያስታውሳቸውና በዳበሳ እንዲለያቸው ይረዳዋል።
“‘ሱስ’ ሆኖብኛል”
ዓይነ ስውር የሆኑ ወይም የማየት ችግር ያለባቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከእነዚህ ጽሑፎች የተጠቀሙት እንዴት ነው? በሄይቲ የሚኖረው ኧርንስት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ የነበረ ቢሆንም አንድም የብሬይል ጽሑፍ አልነበረውም። በዚህም የተነሳ የተማሪ ክፍል ለማቅረብና በስብሰባ ላይ መልስ ለመመለስ ሐሳቡን በቃሉ መያዝ ይጠበቅበት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ግን በማንኛውም ሰዓት እጄን አውጥቼ ሐሳብ መስጠት እችላለሁ። ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር አንድ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ሁላችንም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብልናል!”
በኦስትሪያ የሚኖረው ያን የማየት ችግር አለበት፤ ያን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እና የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመራል፤ እንዲህ ብሏል፦ “እስካሁን ካነበብኳቸው ከሌሎቹ የብሬይል ጽሑፎች ይልቅ የእኛ ጽሑፎች በጣም ግልጽ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ጽሑፎቻችን የገጽ ቁጥር፣ ለማንበብ ቀላል የሆኑ የግርጌ ማስታወሻዎች እንዲሁም ግልጽ የሆኑ የሥዕል መግለጫዎች አሏቸው።”
በደቡብ ኮሪያ የምትኖረው ሶን ኦክ የተባለች አቅኚ ዓይነ ስውርና መስማት የተሳናት ነች። ቀደም ሲል ስብሰባ የምትከታተለው በታክታይል የምልክት ቋንቋ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎችን በራሷ ማንበብ ትችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች የብሬይል ጽሑፎች ለማንበብ አስቸጋሪ ናቸው፤ ምክንያቱም አንዳንዶቹ ነጠብጣቦች ይጎድላሉ፤ መስመሮቹ የተንጋደዱ ናቸው፤ ወይም ደግሞ ወረቀቱ በጣም ስስ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ግን ጥራት ያለው ወረቀት ይጠቀማሉ፤ ነጠብጣቦቹም ጎላ ያሉ ናቸው፤ በመሆኑም በቀላሉ ማንበብ እችላለሁ።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማጥናት የሌሎች እርዳታ ያስፈልገኝ ነበር። አሁን ግን በራሴ ማጥናት እችላለሁ። ለሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎቻችን መዘጋጀትና የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። በብሬይል የተዘጋጁ ጽሑፎቻችንን በሙሉ አንብቤያለሁ። ‘ሱስ’ ሆኖብኛል ሊባል ይችላል።”
በሕትመት እንደሚዘጋጁ ጽሑፎቻችን ሁሉ የብሬይል ጽሑፎቻችንም የሚከተለውን ሐሳብ ይዘዋል፦ “ይህ ጽሑፍ የሚሸጥ አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ከሚታተሙት ጽሑፎች መካከል አንዱ ሲሆን ይህ የማስተማር ሥራ የሚደገፈው ደግሞ ሰዎች በፈቃደኝነት በሚያደርጉት መዋጮ ነው።” በdonate.jw.org ላይ በሚገኙት መንገዶች መዋጮ በማድረጋችሁ ከልብ እናመሰግናችኋለን። የምታሳዩት ልግስና ዓይነ ስውራንን እና የማየት ችግር ያለባቸውን ጨምሮ ለሁሉም ሰው መንፈሳዊ ምግብ እንዲደርስ ያስችላል።
a በአንዳንድ የብሬይል አጻጻፎች ቦታ ለመቆጠብ ሲባል ቃላት አጥረው እንዲጻፉ ይደረጋል። ለምሳሌ በደረጃ ሁለት ብሬይል የተለመዱ ቃላት በምህጻረ ቃል መልክ ይቀመጣሉ። በመሆኑም በደረጃ ሁለት ብሬይል የተዘጋጁ መጻሕፍት በደረጃ አንድ ብሬይል ከተዘጋጁ መጻሕፍት ያጥራሉ።