በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማውን የቀረጻ ቦታ ለማዘጋጀት ከ27,500 ኪሎ ግራም የሚበልጥ የተፈጨ ድንጋይ ወደ ማውንት ኢቦ ስቱዲዮ ማምጣት አስፈልጓል

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

‘ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ’! ለተባለው የ2020 የይሖዋ ምሥክሮች የክልል ስብሰባ ቪዲዮዎችን ማዘጋጀት

‘ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ’! ለተባለው የ2020 የይሖዋ ምሥክሮች የክልል ስብሰባ ቪዲዮዎችን ማዘጋጀት

ነሐሴ 10, 2020

 በክልል ስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርቡት ቪዲዮዎች ልባችንን የሚነኩት ከመሆኑም በላይ የቅዱሳን መጻሕፍት ግንዛቤያችንን ይበልጥ ያሰፉታል። ‘ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ’! የተባለው የ2020 የክልል ስብሰባ የበላይ አካል አባላትና ረዳቶቻቸው ያቀረቧቸውን 43 ንግግሮች ጨምሮ 114 ቪዲዮዎች አሉት። እነዚህን ቪዲዮዎች ለማዘጋጀት ምን ያህል ጥረትና ወጪ እንደሚጠይቅ አስበህ ታውቃለህ?

 በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ወደ 900 የሚጠጉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጊዜያቸውንና ችሎታቸውን ተጠቅመው ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት እርዳታ አበርክተዋል። ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት የፈጀ ሲሆን ወንድሞች በአጠቃላይ ከ100,000 የሚበልጡ ሰዓታትን አሳልፈዋል። ይህም የ76 ደቂቃ ርዝመት ያለውን ነህምያ፦ ‘የይሖዋ ደስታ ምሽጋችሁ ነው’ የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ለማዘጋጀት የፈጀውን 70,000 ሰዓት ይጨምራል።

 የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ለሚያደርጉት ለእነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለኑሮ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት እንዲሁም ለሥራው የሚያስፈልጉ የቴክኒክ ድጋፎችን፣ መሣሪያዎችንና የቀረጻ ቦታዎችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ መገመት አያዳግትም።

 በኦዲዮ/ቪዲዮ አገልግሎት ውስጥ የሚሠራው ጄረድ ጎስማን እንዲህ ብሏል፦ “የበላይ አካሉ የትምህርት ኮሚቴ በቪዲዮዎቻችን ላይ የተለያየ ባሕል ያላቸው ሰዎችና የተለያዩ አካባቢዎች እንዲታዩ ይፈልጋል። ይህም የወንድማማች ማኅበራችን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለው በግልጽ ለማሳየት ያስችላል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ለዚህም ሲባል በ11 አገሮች ያሉ 24 ቡድኖች በዚህ ሥራ ተሳትፈዋል። እንዲህ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ሥራ ለማከናወን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያስፈልጋል፤ በተጨማሪም ጥሩ ዕቅድ ማውጣትና ማስተባበር ይጠይቃል።”

 አብዛኞቹን ቪዲዮዎቻችንን ለማዘጋጀት ለየት ያሉ መሣሪያዎችና የቀረጻ ቦታዎች ያስፈልጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ነህምያ፦ ‘የይሖዋ ደስታ ምሽጋችሁ ነው’ የተባለው ድራማ የተቀረጸው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ አቅራቢያ በሚገኘው የማውንት ኢቦ ስቱዲዮ ውስጥ ነው። ወንድሞች በአንድ በኩል ድራማው የተቀረጸበት ቦታ በወቅቱ የነበረውን ታሪካዊ ሁኔታ የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በጥበብ መጠቀም ይፈልጋሉ፤ በመሆኑም ቀለል ያለ ክብደት ያላቸውን ነገሮች በመጠቀም የጥንቷን ኢየሩሳሌም ግንቦች አስመስለው ለመሥራት ሞክረዋል። እያንዳንዱን የግንቡን ክፍል የሠሩት ስድስት ሜትር ርዝመት ያለውን እንጨት፣ ድንጋይ እንዲመስል ተደርጎ በተቀባ ፎም በመሸፈን ነው። እነዚህን ግንቦች ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ የተለያዩ ትዕይንቶች ላይ ተጠቅመውባቸዋል፤ በመሆኑም በተወሰኑ የቀረጻ ቦታዎች ብቻ ሥራውን ማከናወን ተችሏል። ያም ሆኖ ለድራማው የሚያስፈልጉ የቀረጻ ቦታዎችን ለማዘጋጀት ብቻ ወደ 100,000 የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አስፈልጓል። a

 ይህን ማወቃችን ለዚህ ዓመት የክልል ስብሰባ ፕሮግራም ያለንን አድናቆት ይጨምረዋል። ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት የተደረገው ጥረት በዓለም ዙሪያ ለይሖዋ ከፍተኛ ውዳሴ እንደሚያመጣ እንተማመናለን። ዓለም አቀፉን ሥራ ለመደገፍ በ​donate.jw.org ወይም በሌሎች መንገዶች ለምታደርጉት የልግስና መዋጮ ከልብ እናመሰግናችኋለን።

a ነህምያ፦ ‘የይሖዋ ደስታ ምሽጋችሁ ነው’ ለተባለው ድራማ የቀረጻ ቦታ የተዘጋጀው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ነው። በወቅቱ አካላዊ ርቀት መጠበቅን የሚጠይቁ ደንቦች አልነበሩም።