ይህን ያውቁ ኖሯል?
በጥንት ዘመን ሰዎች በእጅ ወፍጮ የሚጠቀሙት እንዴት ነበር?
የእጅ ወፍጮዎች እህል ፈጭቶ የዳቦ ዱቄት ለማዘጋጀት ያገለግሉ ነበር። በየትኛውም ቤት ውስጥ ማለት ይቻላል በእንዲህ ዓይነት ወፍጮዎች እህል መፍጨት ሴቶች ወይም አገልጋዮች የሚያከናውኑት የዕለት ተዕለት ሥራ ነበር። በጥንት ዘመን የወፍጮ ድምፅ በየዕለቱ ከሚከናወን ሥራ ጋር ተዛማጅነት ነበረው።—ዘፀአት 11:5፤ ኤርምያስ 25:10
በጥንቷ ግብፅ የተገኙ ጥንታዊ ሥዕሎችና ሐውልቶች በእጅ ወፍጮ እንዴት እንደሚፈጭ ያሳያሉ። የእጅ ወፍጮው ጎድጎድ ብሎ ከፊት በኩል ዘቅዘቅ ያለ ሲሆን ከላይ መጅ አለው። የምትፈጨው ሴት ትንበረከክና ወፍጮውን ከፊቷ አድርጋ መጁን በሁለት እጅዋ በመያዝ በኃይል ተጭና ገፋ መለስ እያደረገች በድንጋዮቹ መሃል ያለውን እህል ትፈጫለች። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚናገረው በአብዛኛው የሚሠራበት የአንድ መጅ ክብደት ከ2 እስከ 4 ኪሎ ግራም ይመዝናል። እንዲህ ዓይነቱ መጅ ጥቃት ለማድረስ ከተጠቀሙበት ሰው ሊገድል ይችላል።—መሳፍንት 9:50-54
ወፍጮና መጅ ለአንድ ቤተሰብ ሕልውና ወሳኝ ነገር ስለሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ወፍጮውንና መጁን በመያዣነት መውሰድን ይከለክላል። ዘዳግም 24:6 “ማንም ሰው ወፍጮን ወይም መጅን የብድር መያዣ አድርጎ መውሰድ የለበትም፤ ምክንያቱም የሰውየውን መተዳደሪያ መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆንበታል” በማለት ይገልጻል።
“እቅፍ” የሚለው አባባል ምን ያመለክታል?
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “በአብ እቅፍ” እንዳለ አድርጎ ይገልጻል። (ዮሐንስ 1:18 የግርጌ ማስታወሻ) ይህ አገላለጽ ኢየሱስ ከአምላክ ጋር ያለውን የተለየ ቅርበትና በእሱ ዘንድ ያገኘውን ሞገስ ያመለክታል። ይህ አባባል አይሁዳውያን በማዕድ ፊት በሚቀመጡበት ጊዜ ይከተሉት የነበረውን ልማድ በተዘዋዋሪ የሚጠቅስ ነው።
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አይሁዳውያን በመመገቢያ ጠረጴዛው ዙሪያ በተደረደሩ መከዳዎች ላይ ጋደም ብለው ይቀመጡ ነበር። በማዕዱ ዙሪያ ያለው እያንዳንዱ ተመጋቢ ራሱን ወደ ማዕዱ አድርጎ እግሮቹን ወደ ኋላ በመዘርጋት በግራ ክርኑ መከዳው ላይ ተደግፎ ይቀመጥ ነበር። ይህ አቀማመጥ ቀኝ እጁ ነፃ እንዲሆንለት ያስችለዋል። ተመጋቢዎቹ በሙሉ በግራ ጎናቸው በኩል አንዱ ከሌላው አጠገብ ጋደም ስለሚሉ አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ “የአንዱ ሰው ራስ ከኋላው ወዳለው ሰው ደረት ይጠጋል” በማለት ይገልጻል፤ ይህ ጽሑፍ በመቀጠል “በመሆኑም አንደኛው ሰው በሌላኛው ሰው ‘እቅፍ’ እንዳለ ተደርጎ ይቆጠር ነበር” ብሏል።
በአንድ የቤተሰብ ራስ አሊያም በአንድ ጋባዥ ደረት አጠገብ ጋደም ማለት ልዩ ክብር ወይም መብት እንደማግኘት ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ስለሆነም ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ባከበረው የፋሲካ በዓል ላይ አጠገቡ ጋደም ብሎ የነበረው “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር” ማለትም ሐዋርያው ዮሐንስ ነበር። ስለዚህ ዮሐንስ ኢየሱስን አንድ ነገር ለመጠየቅ ከፈለገ ‘ወደ ደረቱ ጠጋ’ ማለት ይችል ነበር።