በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ማጨስ በአምላክ ዘንድ እንዴት ይታያል?

ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ

ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ

ትንባሆ ምሕረት የማያውቅ ገዳይ ነው።

  • ባለፈው መቶ ዓመት ውስጥ 100,000,000 ሰዎችን ገድሏል።

  • በየዓመቱ 6,000,000 የሚያህሉ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል።

  • በአማካይ በየስድስት ሴኮንዱ አንድ ሰው ይገድላል።

ደግሞም ይህ ሁኔታ እንደሚለወጥ የሚጠቁም ምንም ፍንጭ የለም።

አሁን ያለው ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ በ2030 በማጨስ ምክንያት በየዓመቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ8,000,000 በላይ እንደሚደርስ ባለሙያዎች ይገምታሉ። እንዲሁም እስከ 21ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ድረስ በሲጋራ ምክንያት 1,000,000,000 ሰዎች እንደሚሞቱ ተንብየዋል።

በትንባሆ ምክንያት ጉዳት የሚደርስባቸው አጫሾቹ ብቻ አይደሉም። ትንባሆ በቀሪዎቹ የቤተሰብ አባላት ላይ የስሜት ጉዳት የሚያስከትል ከመሆኑም ሌላ የኢኮኖሚ ጫናም ያመጣል፤ በተጨማሪም በየዓመቱ 600,000 የሚያህሉ ሰዎች ለሲጋራ ጭስ በመጋለጣቸው ምክንያት ይሞታሉ። ከዚህም ሌላ ለጤና የሚወጣው ወጪ ስለሚያሻቅብ ጫናው የሁሉንም ሰው ኪስ ይነካል።

ሐኪሞች መድኃኒት ለማግኘት ከሚደክሙላቸው ወረርሽኞች በተለየ መልኩ ይህን መቅሰፍት በቀላሉ ማስቆም ይቻላል፤ መፍትሔው የታወቀ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ማርጋሬት ቻን የሚከተለውን ተናግረዋል፦ “የትንባሆ ወረርሽኝ ሰዎች በገዛ እጃቸው ያመጡት ችግር ሲሆን መንግሥትና ማኅበረሰቡ በሚያደርገው ርብርብ ሊወገድ ይችላል።”

ይህን የጤና ቀውስ ለማስወገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። ከነሐሴ 2012 አንስቶ 175 የሚያህሉ አገራት፣ የትንባሆ ተጠቃሚዎችን ለመቀነስ አንዳንድ እርምጃዎችን ሊወስዱ ተስማምተዋል። * ይሁን እንጂ ወረርሽኙ በኃይል መዛመቱን እንዲቀጥል የሚያደርጉ ሌሎች ኃይሎች አሉ። የትንባሆው ኢንዱስትሪ አዳዲስ ደንበኞችን፣ በተለይም በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ ሴቶችንና ወጣቶችን ለመማረክ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣል። ትንባሆ ሱስ የሚያስይዝ በመሆኑ በዚህ ሱስ ከተያዙት አንድ ቢሊዮን ሰዎች መካከል አብዛኞቹ መሞታቸው አይቀርም። በአሁኑ ጊዜ ያሉት ትንባሆ ተጠቃሚዎች ማጨሳቸውን ካላቆሙ ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር በቀጣዮቹ አራት አሥርተ ዓመታት በፍጥነት እያሻቀበ ይሄዳል።

ብዙዎች ከዚህ ሱስ መላቀቅ ቢፈልጉም የትንባሆ ማስታወቂያዎችና ትንባሆ ሱስ የሚያስይዝ መሆኑ ከዚህ ወጥመድ መላቀቅ ከባድ እንዲሆንባቸው አድርገዋል። ናኦኮ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟት ነበር። ማጨስ የጀመረችው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለች ነው። መገናኛ ብዙኃን እንደ መልካም ነገር አድርገው የሚያቀርቡትን ልማድ መኮረጇ ዘመናዊ እንደሆነች እንዲሰማት አድርጎ ነበር። ሁለቱም ወላጆቿ የሞቱት በሳንባ ካንሰር ቢሆንም ናኦኮ ማጨሷን አላቆመችም፤ ሁለት ሴት ልጆቿን በምታሳድግበት ወቅትም ከዚህ ልማድ አልተላቀቀችም። እንዲህ ብላለች፦ “በሳንባ ካንሰር ልያዝ የምችል መሆኑ እንዲሁም የልጆቼ ጤንነት ቢያስጨንቀኝም ማጨሴን ማቆም አልቻልኩም። ማጨስን ፈጽሞ ማቆም እንደማልችል ይሰማኝ ነበር።”

ሆኖም ናኦኮ ሲጋራ አቆመች። እሷንም ሆነ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችን ከትንባሆ ለመላቀቅ ኃይል የሰጣቸው ነገር ተመሳሳይ ነው። ታዲያ የረዳቸው ነገር ምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ማንበብህን እንድትቀጥል እናበረታታሃለን።

^ አን.11 እነዚህ እርምጃዎች፣ ማጨስ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ግንዛቤ ማስጨበጥን፣ ከትንባሆ ንግድ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን መገደብን፣ በትንባሆ ላይ ቀረጥ መጨመርንና የሚያጨሱ ሰዎች እንዲያቆሙ ለመርዳት የሚያስችሉ መርሐ ግብሮች መዘርጋትን ይጨምራሉ።