የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ኃጢአታችን ይቅር ሊባልልን ይችላል?
ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ ወርሰናል። በመሆኑም በኋላ ላይ የሚጸጽተንን መጥፎ ነገር የምንሠራበት ጊዜ አለ። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል በመሞት ለኃጢአታችን ቤዛ ከፍሎልናል። ይህ ቤዛዊ መሥዋዕት የኃጢአት ይቅርታ ያስገኝልናል። ቤዛው የአምላክ ስጦታ ነው።—ሮም 3:23, 24ን አንብብ።
አንዳንድ ሰዎች ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸው ምክንያት አምላክ እነሱን ይቅር ይላቸው እንደሆነ ይጠራጠራሉ። ደስ የሚለው ነገር የአምላክ ቃል “የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” ይላል። (1 ዮሐንስ 1:7) ይሖዋ፣ ከባድ ኃጢአት ብንሠራ እንኳ ከልብ ንስሐ እስከገባን ድረስ ይቅር ሊለን ፈቃደኛ ነው።—ኢሳይያስ 1:18ን አንብብ።
ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን ምን ማድረግ አለብን?
ይሖዋ አምላክ ይቅር እንዲለን የምንፈልግ ከሆነ መንገዶቹን፣ ምክሩንና ከእኛ የሚፈልገውን ነገር ለማወቅ ስለ እሱ መማር ይኖርብናል። (ዮሐንስ 17:3) ይሖዋ የሚፈጽሙትን መጥፎ ድርጊት ትተው ንስሐ የሚገቡትንና ለመለወጥ ጥረት የሚያደርጉትን ሰዎች በደግነት ይቅር ይላቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 3:19ን አንብብ።
የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከባድ ነገር አይደለም። ይሖዋ ድክመታችንን ይረዳል። እሱ መሐሪና ደግ ነው። ታዲያ አምላክ መሐሪ መሆኑ እሱን እንዴት ማስደሰት እንደምትችል ለመማር አላነሳሳህም?—መዝሙር 103:13, 14ን አንብብ።