በአምላክ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?
አንድ በጣም የምታደንቀው ጓደኛ አለህ እንበል፤ ሆኖም ይህ ጓደኛህ የሚያደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች ግራ ይገቡሃል። ሌሎች ሰዎችም ጓደኛህን ይነቅፉታል፤ የሚያደርገውን ነገር በተሳሳተ መንገድ የሚረዱት ከመሆኑም ሌላ ጨካኝ እንደሆነ ይናገራሉ። አንተስ ቸኩለህ እነሱ ባሉት ነገር ትስማማለህ ወይስ በመጀመሪያ ጓደኛህ የሚለውን ለመስማት ትጠብቃለህ? ጓደኛህ የሆነውን ነገር ለማስረዳት በቦታው ባይኖር እንኳ በእሱ ላይ ያለህን አመኔታ ሳታጣ በትዕግሥት ትጠብቃለህ?
ይህን ጥያቄ ከመመለስህ በፊት ስለ ጓደኛህ የበለጠ ለማወቅ ትፈልግ ይሆናል። ‘ስለ ጓደኛዬ ያላወቅኋቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆን? እሱን የማደንቀውስ ለምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል። እንዲህ ማሰብህ ተገቢ ነው። እስቲ ደግሞ ይህን አስብ፦ ‘አምላክ ጨካኝ ነው ወይስ አይደለም’ ከሚለው ጉዳይ ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳት አይኖርብንም?
አምላክ ያደረጋቸውን አንዳንድ ነገሮች መረዳት አዳጋች ሆኖብህ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ አንዳንድ ነገሮች እንዲደርሱ ለምን እንደፈቀደ ግራ ተጋብተህ ሊሆን ይችላል። አምላክ ጨካኝ እንደሆነ የሚነግሩህና ስለ እሱ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖርህ ለማድረግ የሚሞክሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ታዲያ በአምላክ ላይ አመኔታ ጥለህ ስለ እሱ የበለጠ እስክታውቅ ድረስ በትዕግሥት ትጠብቃለህ? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ አምላክን ምን ያህል ታውቀዋለህ በሚለው ጉዳይ ላይ የተመካ ነው። ስለዚህ ‘አምላክ ለእኔ ምን ዓይነት ወዳጅ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
አስቸጋሪ ሕይወት አሳልፈህ ከሆነ አምላክ ጭራሹንም ወዳጅህ ሆኖ እንደማያውቅ ለመናገር ትፈተን ይሆናል። ይሁን እንጂ እስቲ ይህን ለአንድ አፍታ አስብ። አምላክ በሕይወትህ ውስጥ ላጋጠሙህ መከራዎች ተጠያቂ ሊሆን ይችላል? ወይስ ከእሱ ያገኘኸው ጥሩ ነገሮችን ነው? ቀደም ሲል እንደተመለከትነው “የዚህ ዓለም ገዥ” ሰይጣን እንጂ ይሖዋ አይደለም። (ዮሐንስ 12:31) በመሆኑም በዚህ ዓለም ላይ ለሚደርሱት አብዛኞቹ መከራዎችና የፍትሕ መዛባት ተጠያቂው ሰይጣን ነው። ከዚህም ሌላ ፍጹም አለመሆናችን እንዲሁም ያልተጠበቁ አጋጣሚዎች ለአብዛኞቹ ችግሮቻችን መንስኤ ናቸው ቢባል እንደምትስማማ የታወቀ ነው።
አምላክ በሕይወትህ ውስጥ ላጋጠሙህ መከራዎች ተጠያቂ ሊሆን ይችላል? ወይስ ከእሱ ያገኘኸው ጥሩ ነገሮችን ነው?
በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ ምን ነገሮችን አድርጎልናል? መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ልብ በል፦ አምላክ “የሰማይና የምድር ፈጣሪ” እንደሆነና ከሠራቸው ነገሮች መካከል “ግሩምና ድንቅ” የሆነው ሰውነታችን እንደሚገኝበት ይናገራል። ከዚህም በላይ ይሖዋ ‘ትንፋሻችንን በእጁ የያዘ’ አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተገልጿል። (መዝሙር 124:8፤ 139:14፤ ዳንኤል 5:23 የ1954 ትርጉም) ታዲያ ይህ ምን ያስገነዝበናል?
ትንፋሻችንን ማለትም ሕልውናችንን ያገኘነው ከፈጣሪ እንደሆነ ያስገነዝበናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:28) ስለዚህ ሕይወታችን፣ በዙሪያችን ያለው ውብ አካባቢ፣ በመውደድና በመወደድ አልፎ ተርፎም ጓደኝነት በመመሥረት የሚገኘው ደስታ እንዲሁም በመቅመስ፣ በመዳሰስ፣ በመስማትና በማሽተት የሚገኘው እርካታ በሙሉ ከአምላክ ያገኘናቸው ስጦታዎች ናቸው። (ያዕቆብ 1:17) እነዚህ ሁሉ በረከቶች አምላክን፣ ከፍ ያለ አድናቆት ሊቸረውና እምነት ሊጣልበት የሚገባ ወዳጅ ያደርጉታል ቢባል አትስማማም?
እርግጥ ነው፣ በአምላክ ላይ እምነት መጣል ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ምናልባትም በእሱ ላይ እምነት ለመጣል በሚያስችል ደረጃ በደንብ እንዳላወቅኸው ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ቢሰማህ ምክንያታዊ ነው። በእነዚህ አጫጭር ርዕሶች ውስጥ አንዳንዶች አምላክ ጨካኝ ነው እንዲሉ ያደረጓቸውን ምክንያቶች ሁሉ ዘርዝረን መጥቀስ አንችልም። ይሁን እንጂ አምላክን የበለጠ ለማወቅ ጥረት ልናደርግ ይገባል ቢባል አትስማማም? * ይህን ጥረት ካደረግህ ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ እንደምትችል እርግጠኞች ነን። ታዲያ ምን ትላለህ? እስካሁን ከተመለከትናቸው ነገሮች አንጻር አምላክ ጨካኝ ነው? በፍጹም! እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ “አምላክ ፍቅር ነው።”—1 ዮሐንስ 4:8
^ አን.8 ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 11ን ተመልከት።