የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ዲያብሎስ የመጣው ከየት ነው?
አምላክ ክፉ ወይም ዲያብሎስ አድርጎ የፈጠረው መልአክ የለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የፈጠረው አንድ መልአክ ከጊዜ በኋላ ዲያብሎስ ሆነ፤ ይህ መልአክ ሰይጣን ተብሎም ተጠርቷል። ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ዲያብሎስ በአንድ ወቅት እውነተኛና በደል የሌለበት መልአክ ነበር። በመሆኑም ዲያብሎስ፣ በተፈጠረበት ወቅት ጻድቅ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ነበር።—ዮሐንስ 8:44ን አንብብ።
አንድ ጥሩ መልአክ ዲያብሎስ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
ከጊዜ በኋላ ዲያብሎስ የሆነው መልአክ በአምላክ ላይ ያመፀ ከመሆኑም ሌላ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የእሱን መንገድ እንዲከተሉ ገፋፋቸው። በዚህ መንገድ ራሱን ሰይጣን ማለትም ተቃዋሚ አደረገ።—ዘፍጥረት 3:1-5ን እና ራእይ 12:9ን አንብብ።
እንደ ሌሎቹ ማሰብ የሚችሉ የአምላክ ፍጡራን ሁሉ ሰይጣንም ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር ለማድረግ የመምረጥ ነፃነት ነበረው፤ ይሁንና ሰይጣን የመመለክ ፍላጎት አዳበረ። እንዲያውም ይህ ፍላጎቱ ለአምላክ ካለው ፍቅር በልጦበታል።—ማቴዎስ 4:8, 9ን እና ያዕቆብ 1:13, 14ን አንብብ።
ዲያብሎስ በሰው ልጆች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የቀጠለው እንዴት ነው? ዲያብሎስ ሊያስፈራህ ይገባል? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ትችላለህ።