በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙሴ—ትሑት ሰው

ሙሴ—ትሑት ሰው

ትሕትና ምንድን ነው?

ትሕትና የሚለው ቃል እብሪተኛ ወይም ትዕቢተኛ አለመሆንን ሊያመለክት ይችላል። ትሑት የሆነ ሰው ሌሎችን ዝቅ አድርጎ አይመለከትም። አንድ ፍጽምና የጎደለው ሰው ትሑት የሚባለው ልኩን የሚያውቅ ማለትም የአቅም ገደቦቹን የሚገነዘብ ከሆነ ነው።

ሙሴ ትሑት እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?

ሙሴ ሥልጣን እንዲያስታብየው አልፈቀደም። ብዙውን ጊዜ፣ አንድ ሰው ትንሽ ሥልጣን ሲያገኝ ትሑት መሆን አለመሆኑ ወዲያውኑ ግልጽ ይሆናል። የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ደራሲ የነበሩት ሮበርት ኢንገርሶል ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ገልጸውታል፦ “ብዙ ሰዎች ችግርን መቋቋም ይችላሉ። ይሁን እንጂ የአንድን ሰው ማንነት በትክክል ለማወቅ ከፈለጋችሁ ሥልጣን ስጡት።” ከዚህ አንጻር ሙሴ ግሩም የትሕትና ምሳሌ ትቷል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር የመምራት ኃላፊነት ለሙሴ ስለሰጠው ትልቅ ሥልጣን ነበረው። ሆኖም የተሰጠው ሥልጣን ሙሴን ፈጽሞ አላስታበየውም። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ውርስ መብት ተነስቶ የነበረን አንድ አስቸጋሪ ጥያቄ የያዘበት መንገድ ሙሴ ቦታውን የሚያውቅ ሰው እንደነበረ ያሳያል። (ዘኍልቍ 27:1-11) ጥያቄው ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነበር፤ ምክንያቱም ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው ውሳኔ በመጪዎቹ ትውልዶች ለሚነሱ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ሕጋዊ መሠረት ሆኖ ያገለግላል።

ታዲያ ሙሴ ምን አደረገ? የእስራኤል መሪ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማድረግ ብቃት እንዳለው ተሰምቶት ይሆን? በተፈጥሮ ችሎታው፣ ለዓመታት ባካበተው ተሞክሮ ወይም ስለ ይሖዋ አስተሳሰብ ባለው ጥልቅ እውቀት ይመካ ይሆን?

ኩሩ የሆነ ሰው እንዲህ ያደርግ ይሆናል። ሙሴ ግን ይህን አላደረገም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙሴ [ጉዳዩን] ወደ እግዚአብሔር አቀረበ” ይላል። (ዘኍልቍ 27:5) የሚገርም ነው! ሙሴ የእስራኤልን ብሔር 40 ለሚያህሉ ዓመታት ሲመራ ከቆየ በኋላም እንኳ የሚታመነው በራሱ ሳይሆን በይሖዋ ነበር። ሙሴ ትሑት ሰው እንደነበር ከዚህ ዘገባ በግልጽ መመልከት እንችላለን።

ሙሴ ‘እኔ ብቻ ሥልጣን ካልያዝኩ’ የሚል ስሜትም አልነበረውም። ይሖዋ ሌሎች እስራኤላውያን እንደ እሱ ነቢያት ሆነው እንዲያገለግሉ ባደረገ ጊዜ ሙሴ ተደስቷል። (ዘኍልቍ 11:24-29) ሙሴ የነበረውን የሥራ ጫና ለማቃለል ኃላፊነቱን ለሌሎች እንዲያካፍል አማቱ ሐሳብ ባቀረበለት ጊዜ ምክሩን በትሕትና ተቀብሎ ተግባራዊ አድርጓል። (ዘፀአት 18:13-24) ደግሞም ሙሴ በሕይወቱ መገባደጃ ላይ ጠንካራ የነበረ ቢሆንም እሱን የሚተካ ሰው እንዲሾም ይሖዋን ጠይቆታል። ይሖዋም ኢያሱን በመረጠ ጊዜ ሙሴ ይህን ወጣት ሙሉ በሙሉ የደገፈው ከመሆኑም በላይ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት የኢያሱን አመራር እንዲከተሉ መክሯቸዋል። (ዘኍልቍ 27:15-18፤ ዘዳግም 31:3-6፤ 34:7) በተጨማሪም ሙሴ እስራኤላውያንን በአምልኮ ረገድ መምራቱን እንደ ትልቅ መብት እንደቆጠረው ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን የነበረውን ሥልጣን ከሌሎች ደኅንነት አስበልጦ አይመለከትም ነበር።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

እኛም ኃይል፣ ሥልጣን ወይም የተፈጥሮ ችሎታ እንዲያስታብየን ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም። ይሖዋ እንዲጠቀምብን ከፈለግን ምንጊዜም ትሕትናችን ከችሎታችን ልቆ መታየት እንዳለበት መዘንጋት አይኖርብንም። (1 ሳሙኤል 15:17) እውነተኛ ትሕትና የምናሳይ ከሆነ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት እናደርጋለን።—ምሳሌ 3:5, 6

በተጨማሪም ክብራችንን ወይም ሥልጣናችንን ከልክ በላይ ከፍ አድርገን እንዳንመለከት ሙሴ ምሳሌ ይሆነናል።

ታዲያ ሙሴ የተወውን የትሕትና ምሳሌ መከተል ጥቅም ያስገኝልን ይሆን? ምንም ጥያቄ የለውም! እውነተኛ ትሕትና ማዳበራችን ሌሎች ሰዎች ከእኛ ጋር መሆን አስደሳች እንዲሆንላቸው የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በእነሱ ዘንድ ተወዳጅ ያደርገናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህን ውብ ባሕርይ በሚያንጸባርቀው በይሖዋ ዘንድ ተወዳጅነት እናተርፋለን። (መዝሙር 18:35) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል። (1 ጴጥሮስ 5:5) ሙሴ የተወውን የትሕትና ምሳሌ ለመከተል የሚገፋፋ እንዴት ያለ አሳማኝ ምክንያት ነው!