በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጥፎ አስተዳደግ የነበረው አንድ ሰው ደስተኛና ስኬታማ ባል እንዲሁም አባት መሆን የቻለው እንዴት ነው? ብዙ መጥፎ ልማዶች የነበሯት አንዲት ሴት ሕይወቷን እንድታስተካክል ያነሳሳት ምንድን ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።

“ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር።”​—ቢክቶር ዩጎ ኤሬራ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1974

  • የትውልድ አገር፦ ቺሊ

  • የኋላ ታሪክ፦ የአልኮል ሱሰኛ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት አንጎል በምትባል ውብ በሆነው የቺሊ ደቡባዊ ክፍል የምትገኝ ከተማ ነው። አባቴን አይቼው አላውቅም። የሦስት ዓመት ልጅ እያለሁ እናቴ፣ ታናሽ ወንድሜንና እኔን ይዛ ወደ ዋና ከተማዋ ሳንቲያጎ ሄደች። እዚያም ቤት አልባ ለሆኑ ሰዎች በተሠራ ጊዜያዊ ሠፈር በአንዲት ደሳሳ ቤት ውስጥ መኖር ጀመርን። ከቤታችን ውጭ በሚገኝ የጋራ መጸዳጃ ቤት የምንጠቀም ሲሆን ውኃ የምንቀዳው ለእሳት አደጋ መኪኖች ከተዘጋጀ የውኃ ማጠራቀሚያ ነበር።

ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ መንግሥት አንዲት ትንሽ ቤት ሰጠን። የሚያሳዝነው ነገር አዲሱ ሰፈራችን የዕፅና የአልኮል ሱሰኞች፣ ወንጀለኞች እንዲሁም ዝሙት አዳሪዎች ይበዙበት ነበር።

አንድ ቀን እናቴ ከአንድ ሰው ጋር ተዋወቀች፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ከዚህ ሰው ጋር ተጋቡ። የእንጀራ አባቴ ሰካራም ነበር። እኔንና እናቴን ስለሚደበድበን ማንም ሳያየኝ የማለቅስባቸው ጊዜያት ብዙ ነበሩ፤ እንዲሁም ከሚደርስብኝ ጥቃት የሚከላከልልኝ አባት ቢኖረኝ ብዬ እመኝ ነበር።

እናቴ የሚያስፈልገንን ለማሟላት ጠንክራ ብትሠራም በጣም ድሆች ነበርን። አንዳንድ ጊዜ ርቦን የምንበላው ስናጣ ዱቄት ወተትና ስኳር እንቅማለን። እኔና ወንድሜ በአንዲት ጎረቤታችን መስኮት አጮልቀን ቴሌቪዥን በማየት እንዝናና ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ሴትየዋ ስለደረሰችብን ከዚያ በኋላ ማየት አልቻልንም!

የእንጀራ አባቴ የማይሰክረው አልፎ አልፎ ቢሆንም በእነዚያ ወቅቶች ለእኔና ለወንድሜ የሚበላ ነገር ይገዛልን ነበር። በአንድ ወቅት አንዲት አነስተኛ ቴሌቪዥን ገዛልን። ያ ቀን በልጅነቴ ከተደሰትኩባቸው በጣም ጥቂት ጊዜያት አንዱ ነበር።

በ12 ዓመቴ ማንበብ ተማርኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ትምህርት ትቼ ሙሉ ቀን መሥራት ጀመርኩ። ከሥራ በኋላ አዋቂ ከሆኑ የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ወደ ጭፈራ ቤቶች በመሄድ እንሰክርና ዕፅ እንወስድ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሱሰኛ ሆንኩ።

ሃያ ዓመት ሲሆነኝ ካቲ ከተባለች ወጣት ጋር ተዋወቅሁና ውሎ አድሮ ተጋባን። መጀመሪያ ላይ ሕይወታችን ጥሩ ነበር፤ እያደር ግን ወደ ቀድሞው ሕይወቴ ተመለስኩ። ጠባዬ ከበፊቱም የባሰ ሆነ። ከጊዜ በኋላ ግን በዚህ አያያዜ ወይ ወኅኒ እንደምወርድ አሊያም መሞቴ እንደማይቀር ተገነዘብኩ። ከሁሉም የከፋው ደግሞ ልክ እኔ በልጅነቴ እንደተሠቃየሁት ልጄን ቢክቶርን እያሠቃየሁት መሆኔ ነበር። በዚህም አዝንና በራሴ እበሳጭ እንዲሁም ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር።

በ2001 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጥተው አነጋገሩን፤ ካቲ ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ካቲ ስለምትማረው ነገር ትነግረኝ ነበር። ስለ ጉዳዩ የማወቅ ጉጉት ስላደረብኝ እኔም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። በ2003 ካቲ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

አንድ ቀን በሩት 2:12 ላይ የሚገኘውን ይሖዋ በእሱ ለሚታመኑና እሱን መጠጊያቸው ላደረጉ ሰዎች ወሮታ እንደሚከፍል የሚገልጸውን ሐሳብ አነበብኩ። እኔም በአኗኗሬ ላይ ለውጥ ካደረግሁ አምላክን ማስደሰትና የእሱን በረከት ማግኘት እንደምችል ተገነዘብኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ስካርን ደጋግሞ እንደሚያወግዝ አስተዋልኩ። በ2 ቆሮንቶስ 7:1 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ልቤን ነካው። ይህ ጥቅስ “ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ይላል። ስለዚህ መጥፎ ልማዶቼን ለመተው ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። እንዲህ ሳደርግ መጀመሪያ ላይ ከበፊቱ የበለጠ ብስጩ ሆኜ ነበር፤ ያም ቢሆን ካቲ እኔን ከመደገፍ ወደኋላ ብላ አታውቅም።

በሥራ ቦታዬ እንዳጨስና እንድጠጣ ኃይለኛ ተጽዕኖ ይደረግብኝ ስለነበረ በመጨረሻ ሥራዬን ለቀቅኩ። ለተወሰነ ጊዜ ሥራ በማቆሜ በጥቂት ገቢ ለመኖር ብንገደድም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት ቻልኩ። በመንፈሳዊ ጥሩ እድገት ማድረግ የጀመርኩት በዚህ ጊዜ ነበር። ካቲ በቁሳዊ ረገድ ማቅረብ ከምችለው በላይ ካላመጣህ ብላኝ አታውቅም፤ አኗኗራችን ቀላል እንዲሆን በማድረጌም አልወቀሰችኝም። በፍቅር ተነሳስታ ለምታደርግልኝ ድጋፍ በጣም አመስጋኝ ነኝ።

ቀስ በቀስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ይበልጥ መቀራረብ ጀመርኩ። እነሱም በትምህርቴ ብዙ ባልገፋም ይሖዋ እሱን ለማገልገል ያለኝን ልባዊ ፍላጎት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እንዳስተውል ረዱኝ። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያየነው ፍቅርና አንድነት በቤተሰባችን ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። እንዲህ ዓይነት ሰላም የትም ቦታ አግኝተን አናውቅም። በመሆኑም ታኅሣሥ 2004 እኔም ተጠመቅሁ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ይሖዋ በኢሳይያስ 48:17 ላይ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ . . . ነኝ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት በራሴ ሕይወት ማየት ችያለሁ። እናቴና ወንድሜ ባደረግሁት ለውጥ በጣም ስለተገረሙ አሁን መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ ነው። ጎረቤቶቼም እንኳ ምን ያህል እንደተለወጥኩና ደስተኛ ቤተሰብ እንዳለኝ ሲያዩ ደስ ብሏቸዋል።

ባለቤቴ አምላክን የምትወድ ከመሆኑም ሌላ እኔን እምነት ሊጣልብኝ የምችል የኑሮ አጋሯና ወዳጇ አድርጋ ትመለከተኛለች። አባቴን ጨርሶ ባላውቀውም ሦስት ወንዶች ልጆቼን እንዴት ማሳደግ እንዳለብኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬያለሁ። እነሱም ያከብሩኛል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ እውን ሆኖላቸዋል፤ እንዲሁም ለእሱ ያላቸው ፍቅር እያደገ ነው።

“አባቴን ጨርሶ ባላውቀውም ሦስት ወንዶች ልጆቼን እንዴት ማሳደግ እንዳለብኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬያለሁ”

ጥሩ አስተዳደግ ባይኖረኝም ይሖዋ ደስተኛ ሕይወት የመምራት አጋጣሚ ስለሰጠኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ።

“ቁጡና ጠበኛ ሆንኩ።”—ናቢሃ ላዛሮቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1974

  • የትውልድ አገር፦ ቡልጋሪያ

  • የኋላ ታሪክ፦ ዕፅ አዘዋዋሪ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

በቡልጋሪያ ዋና ከተማ ሶፊያ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ ተወለድኩ። የስድስት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ጥሎን ሄደ። ይህ እጅግ ያስደነገጠኝ ከመሆኑም በላይ ስሜቴን በጣም ጎድቶታል። እንደማልፈለግና መወደድ የማይገባኝ እንደሆንኩ ተሰማኝ። እያደግሁ ስሄድ እነዚህ ስሜቶች ዓመፀኛ እንድሆን አደረጉኝ። ቁጡና ጠበኛ ሆንኩ።

አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ኮበለልኩ። ከእናቴና ከአያቶቼ ብዙ ጊዜ ገንዘብ እሰርቅ ነበር። በትምህርት ቤት ሳለሁ ዓመፀኛ ስለነበርኩ ሁልጊዜ ችግር ውስጥ እገባ ነበር፤ በዚህም ምክንያት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ አምስት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ገብቻለሁ። መደበኛውን ትምህርት ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት ሲቀረኝ ትምህርት አቆምኩ። አኗኗሬ በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ነበር። የሲጋራና የማሪዋና ሱሰኛ ሆንኩ። ከመጠን በላይ እጠጣ እንዲሁም ጭፈራ ቤቶችን አዘወትር ነበር። በተጨማሪም ዕፅ ማዘዋወር ጀመርኩ። ሰዎች ሲሠቃዩና ሲሞቱ ስመለከት ተስፋ ቢስ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ መኖር ምንም ትርጉም እንደሌለው ተሰማኝ። በመሆኑም ሕይወቴ ዕለታዊ ደስታን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሆነ።

በ1998 የ24 ዓመት ወጣት እያለሁ በሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል አውሮፕላን ማረፊያ ዕፅ ሳዘዋውር ተይዤ ታሰርኩ። በዚህ ዓይነት ሕገ ወጥ ሥራ በመካፈሌ የአራት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በ2000 የይሖዋ ምሥክሮች እኔ ወዳለሁበት እስር ቤት በሳምንት አንድ ጊዜ እየመጡ መስበክ ጀመሩ። ከእነሱም መካከል ማሪኔስ የምትባለው ሴት ደግነት ታሳየኝ ነበር። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት እንዲቀሰቀስብኝ አደረገች። ከዚያ በፊት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሰምቼ ስለማላውቅ አብረውኝ የታሰሩትን ሴቶች ስለ እነሱ እንዲነግሩኝ ጠየቅኋቸው። የሚገርመው ነገር ከጠየቅኋቸው ውስጥ አብዛኞቹ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች መጥፎ ነገር ነገሩኝ። እንዲያውም አንዷ እስረኛ የይሖዋ ምሥክር ከምሆን የሌላ የየትኛውም ሃይማኖት አባል ብሆን የተሻለ እንደሆነ ነገረችኝ። ሆኖም እሷ የተናገረችው ነገር የማወቅ ጉጉቴን ይበልጥ ቀሰቀሰው፤ እነዚህ ሰዎች ይህን ያህል የተጠሉት ለምን እንደሆነ ለማወቅ ፈለግሁ። ከጊዜ በኋላ፣ ሰዎች የሚጠሏቸው እውነተኛውን ሃይማኖት ስለያዙ እንደሆነ አመንኩ። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ኢየሱስን ለመከተል ከልብ የሚጥሩ ሰዎች ስደት እንደሚደርስባቸው ይናገራል።—2 ጢሞቴዎስ 3:12

በዚህ ወቅት በወህኒ ቤቱ አስተዳደር ሕንፃ ውስጥ እንድሠራ ተመድቤ ነበር። አንድ ቀን በመጋዘን ውስጥ በካርቶኖች የተቀመጡ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን * አገኘሁ። መጽሔቶቹን ወደ ክፍሌ ወስጄ ማንበብ ጀመርኩ። ይበልጥ ባነበብኩ መጠን በረሃ ላይ ሲንከራተት ከቆየ በኋላ ጥም የሚቆርጥ ቀዝቃዛ ውኃ እንዳገኘ ሰው ያህል ይሰማኝ ጀመር። ሰፊ ጊዜ ስለነበረኝ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ለብዙ ሰዓታት አጠና ነበር።

አንድ ቀን ወደ እስር ቤቱ ቢሮ ተጠራሁ። ከእስር ቤት የምለቀቅ ስለመሰለኝ የነበሩኝን ጥቂት ንብረቶች በፍጥነት ሰበሰብኩና አብረውኝ የታሰሩትን ሴቶች ተሰናብቼ ወደ ቢሮው እየሮጥኩ ሄድኩ። ይሁን እንጂ እዚያ ስደርስ ነገሩ እንደጠበቅሁት እንዳልሆነ ተረዳሁ፤ እንዲያውም የነበሩኝ ሰነዶች የሐሰት በመሆናቸው አዲስ ክስ ተመሥርቶብኝ ነበር። በዚህም የተነሳ ተጨማሪ የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ።

ይህን ስሰማ መጀመሪያ ላይ ቅስሜ ተሰብሮ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ይህ ሁኔታ ለበጎ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ነገሮችን ብማርም ከእስር ቤት ከተለቀቅሁ በኋላ የቀድሞውን አኗኗሬን የመለወጥ ሐሳብ አልነበረኝም። በመሆኑም ልቤ እንዲለወጥ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኝ ነበር።

አምላክ ከአገልጋዮቹ እንደ አንዷ አድርጎ ሊቀበለኝ እንደማይችል የሚሰማኝ ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ በ1 ቆሮንቶስ 6:9-11 ላይ እንደሚገኘው ባሉ ጥቅሶች ላይ አሰላስላለሁ። ይህ ጥቅስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንዶች ይሖዋን ማገልገል ከመጀመራቸው በፊት ሌቦች፣ ሰካራሞችና ቀማኞች እንደነበሩ ይገልጻል። ሆኖም በይሖዋ እርዳታ ተለውጠዋል። የእነሱ ምሳሌነት ለእኔም ትልቅ ማበረታቻ ሆኖኛል።

አንዳንድ መጥፎ ልማዶቼን መተው አልከበደኝም። ለምሳሌ ያህል፣ ዕፅ መውሰዴን ለማቆም ብዙ አልተቸገርኩም። ከሲጋራ ሱስ መላቀቅ ግን በጣም ከባድ ሆኖብኝ ነበር። ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ጠይቆብኛል። በዚህ ረገድ የረዳኝ አንዱ ነገር ማጨስ በጤንነት ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ያለኝን ግንዛቤ ማሳደጌ ነው። ከሁሉ በላይ ግን ማጨስ ለመተው ያስቻለኝ ወደ ይሖዋ ያለማሰለስ መጸለዬ ነበር።

‘ፈጽሞ የማይተወኝ ከሁሉ የተሻለ አባት አግኝቻለሁ!’

አባቴ ጥሎን ከሄደ ጀምሮ እንደማልፈለግ ይሰማኝ ነበር፤ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እየቀረብኩ ስሄድ ግን ለረጅም ጊዜ ሲታገለኝ የኖረውን ይህን አሉታዊ ስሜት ማሸነፍ ቻልኩ። በመዝሙር 27:10 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በጥልቅ ነካኝ። ጥቅሱ “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” ይላል። ፈጽሞ የማይተወኝ ከሁሉ የተሻለ አባት እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ! ይህን ሳውቅ ሕይወቴ ዓላማ ያለው ሆነ። ሚያዝያ 2004 ይኸውም ከእስር ከተለቀቅሁ ከስድስት ወራት በኋላ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

አሁን በጣም ደስተኛ ነኝ። ጎጂ ከሆኑ ልማዶች ስለተላቀቅሁ ወጣት ከነበርኩበት ጊዜ የተሻለ ጤንነትና የተረጋጋ ስሜት አለኝ። ጥሩ ትዳር መመሥረት ችያለሁ፤ እንዲሁም በሰማይ ካለው አባቴ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አለኝ። በይሖዋ አምላኪዎች መካከል ብዙ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች አግኝቻለሁ። (ማርቆስ 10:29, 30) እኔ ራሴ እንኳ የመለወጥ ተስፋ እንደሌለኝ አስብ በነበረበት ወቅት እነሱ ሕይወቴን ላስተካክል እንደምችል አስበው ስለረዱኝ አመስጋኝ ነኝ።

አንዳንድ ጊዜ፣ ባሳለፍኩት ሕይወት የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት እዋጣለሁ። ይሁን እንጂ አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ መጥፎ ትዝታዎች ፈጽሞ ‘እንደማይታወሱ’ ማወቄ ያጽናናኛል። (ኢሳይያስ 65:17) በሌላ በኩል ደግሞ ያሳለፍኩት ሕይወት፣ እኔ ያጋጠመኝ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ለሚያጋጥማቸው ሰዎች ርኅራኄ እንዳሳይ ረድቶኛል። ከዚህ አንጻር ሲታይ እንደዚያ ዓይነት ሕይወት ማሳለፌ ጥቅም አለው ሊባል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በክርስቲያናዊ አገልግሎት በምካፈልበት ጊዜ የዕፅ ሱሰኛም ሆኑ ሰካራም ወይም ወንጀለኛ የሆኑ ሰዎችን ሳልመርጥ ማነጋገር ይቀለኛል። እኔ ይሖዋን ለማስደሰት ስል ለውጥ ማድረግ ከቻልኩ ማንኛውም ሰው ይህን ማድረግ እንደማያቅተው እርግጠኛ ነኝ!

^ አን.29 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።