ደግነት—በአምላክ ዘንድ ውድ የሆነ ባሕርይ
በጃፓን የሚኖር አንድ ወጣት፣ አንድ አረጋዊ ሰው ባሳዩት ደግነት ልቡ ተነክቷል። ሚስዮናዊ የሆኑት እኚህ አረጋዊ ሰው በእስያ ውስጥ ወደምትገኘው ወደዚች አገር የመጡት ከጥቂት ዓመታት በፊት ስለነበር የጃፓን ቋንቋ ችሎታቸው ውስን ነው። ሆኖም በየሳምንቱ ወደ ወጣቱ ቤት በመሄድ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያወያዩታል። ፈገግታ የማይለያቸው እኚህ አረጋዊ፣ የማወቅ ጉጉት ያለው ይህ ተማሪ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በትዕግሥት የሚመልሱለት ከመሆኑም በላይ ደግነት ያሳዩታል።
አረጋዊው ሚስዮናዊ ያሳዩት ደግነት በወጣቱ አእምሮ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳደረ። ይህ ወጣት ‘መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ሰው ይህን ያህል ደግና አፍቃሪ የሚያደርግ ከሆነ እኔም መጽሐፍ ቅዱስን መማር ይኖርብኛል’ ብሎ አሰበ። ሚስዮናዊው ያሳዩት ደግነት፣ ይህ ወጣት ለእሱ ፈጽሞ እንግዳ ስለሆነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመማር ፈቃደኛ እንዲሆን አደረገው። አዎን፣ ደግነት የሰውን ልብ የሚነካ ከመሆኑም ሌላ አብዛኛውን ጊዜ ከቃላት የበለጠ በሌሎች ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል አለው።
ከአምላክ ያገኘነው ባሕርይ
ለቅርብ ዘመዶቻችን ደግነት ማሳየታችን ተፈጥሯዊ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ለምንቀርባቸው ሰዎች ደግነት ማሳየት ይቀለናል። ይሁን እንጂ ደግነት በዋነኝነት መለኮታዊ ባሕርይ ነው። ኢየሱስ፣ በሰማይ ያለው አባቱ ደግነት የሚያሳየው እሱን ለሚወዱት ብቻ ሳይሆን “ለማያመሰግኑም” ጭምር እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ፣ “በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ” በማለት ተከታዮቹ ለሁሉም ሰው ደግነት በማሳየት አምላክን እንዲመስሉ አሳስቧል።—ሉቃስ 6:35፤ ማቴዎስ 5:48፤ ዘፀአት 34:6
ሰዎች በአምላክ መልክ የተፈጠሩ በመሆናቸው ይሖዋ የሚያሳየው ዓይነት ደግነት ማሳየት ይችላሉ። (ዘፍጥረት 1:27) በእርግጥም አምላክን መምሰልና በሥጋ ለሚዛመዱን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎችም ደግነት ማሳየት እንችላለን። ደግነት፣ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ማለትም በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል የሚያፈራው የመንፈስ ፍሬ አንዱ ገጽታ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ገላትያ 5:22) በመሆኑም አንድ ሰው የሁሉም ነገር ፈጣሪ ስለሆነው ስለ አምላክ እየተማረና ወደ እሱ ይበልጥ እየቀረበ ሲሄድ ይህን ባሕርይ እያዳበረ ይሄዳል።
ደግነት የሰው ተፈጥሯዊ ባሕርይ ከመሆኑም በላይ በአምላክ ዘንድ ከፍ ተደርጎ የሚታይ ነገር ነው፤ ስለሆነም አምላክ “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ” ብሎ መናገሩ ምክንያታዊ ነው። (ኤፌሶን 4:32) በተጨማሪም “እንግዳ ተቀባይ መሆንን አትርሱ” የሚለው ማሳሰቢያ ለማናውቃቸው ሰዎችም ደግነት እንድናሳይ ያበረታታናል።—ዕብራውያን 13:2
ደግነት በጎደለውና አመስጋኝነት በጠፋበት ዓለም ውስጥ እየኖርን ለሌሎች ሌላው ቀርቶ ለማናውቃቸው ሰዎች ደግነት ማሳየት እንችላለን? ከሆነ እንዲህ ለማድረግ ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው? ለሁሉም ሰዎች ደግነት የማሳየቱ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባውስ ለምንድን ነው?
በአምላክ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባሕርይ
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለማናውቃቸው ሰዎች ደግነት ስለ ማሳየት ከተናገረ በኋላ “አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ ሳያውቁት መላእክትን አስተናግደዋል” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው። መላእክትን የማስተናገድ አጋጣሚ ብታገኝ ምን ሊሰማህ እንደሚችል አስበው! ይሁን እንጂ፣ ጳውሎስ አንዳንዶች መልእክትን ያስተናገዱት “ሳያውቁት” እንደሆነ ተናግሯል። በመሆኑም ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ፣ እንግዶችን ማለትም የማናውቃቸውን ሰዎች ጨምሮ ለሌሎች ደግነት የማሳየት ልማድ ካለን ባልጠበቅነው መንገድ ወሮታ ልናገኝ እንደምንችል ያሳያል።
አብዛኞቹ ማጣቀሻ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ በዘፍጥረት ምዕራፍ 18 እና 19 ላይ ከሰፈሩት ስለ አብርሃምና ስለ ሎጥ ከሚገልጹ ዘገባዎች ጋር ያያይዟቸዋል። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ አስፈላጊ የሆኑ መልእክቶችን የያዙ መላእክት፣ እንግዶች መስለው ተገልጠው እንደነበር እናነባለን። ወደ አብርሃም የመጡት መላእክት የያዙት መልእክት አምላክ ልጅ እንደሚሰጠው ለአብርሃም የገባውን ቃል እንደሚፈጽምለት የሚገልጽ ሲሆን ለሎጥ የደረሰው መልእክት ደግሞ ሰዶምና ገሞራ በሚባሉት ከተሞች ላይ ከሚመጣው ጥፋት መዳን ስለሚያገኝበት መንገድ የሚገልጽ ነበር።—ዘፍጥረት 18:1-10፤ 19:1-3, 15-17
ከላይ ያሉትን ጥቅሶች ስታነብ አብርሃምም ሆነ ሎጥ ደግነት ያሳዩት ለማያውቋቸው መንገደኞች እንደነበረ ትገነዘባለህ። እርግጥ ነው፣ በጥንት ዘመን መንገደኛን በእንግድነት መቀበል እንደ ጥሩ ባሕል ይታይ ነበር፤ መንገደኛው ወዳጅ ዘመድም ሆነ ለአገሩ እንግዳ የሆነ ሰው፣ እንዲህ ዓይነት መስተንግዶ ይደረግለት ነበር። እንዲያውም የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን በምድራቸው የሚኖሩ የባዕድ አገር ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች በመስጠት ረገድ ንፉግ እንዳይሆኑ ያዝዝ ነበር። (ዘዳግም 10:17-19) አብርሃምና ሎጥ ግን ከጊዜ በኋላ በሕጉ ውስጥ የተካተተው ይህ ትእዛዝ ከሚጠይቀው የበለጠ ነገርም አድርገዋል። ለእንግዶች ደግነት ለማሳየት ለየት ያለ ጥረት ያደረጉ ሲሆን እንዲህ በማድረጋቸውም ተባርከዋል።
አብርሃም ያሳየው ደግነት ልጅ እንዲያገኝ አስችሎታል፤ ይሁንና ይህ ለእሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም በረከት አስገኝቷል። እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው? አብርሃምና ልጁ ይስሐቅ በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። እነዚህ ሰዎች መሲሑ ኢየሱስ በተገኘበት የዘር ሐረግ ውስጥ ቁልፍ የሆነ ቦታ ነበራቸው። በተጨማሪም አብርሃምና ይስሐቅ በእምነት ተነሳስተው ያደረጉት ነገር አምላክ በፍቅሩና በጸጋው የሰው ልጆች መዳን የሚያገኙበትን መንገድ የሚያዘጋጀው እንዴት እንደሚሆን የሚያሳይ ጥላ ሆኖ አገልግሏል።—ዘፍጥረት 22:1-18፤ ማቴዎስ 1:1, 2፤ ዮሐንስ 3:16
እነዚህ ዘገባዎች አምላክ ከሚወዳቸው ሰዎች ምን እንደሚጠብቅና ለደግነት ምን ያህል ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጥ አስደናቂ በሆነ መንገድ ይገልጻሉ። ደግነት ማሳየት ለምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም አምላክ ለዚህ ባሕርይ ትልቅ ቦታ ይሰጣል።
ደግነት ማሳየት አምላክን ይበልጥ እንድናውቀው ይረዳናል
መጽሐፍ ቅዱስ ባለንበት ዘመን ብዙ ሰዎች “የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) በየቀኑ እንዲህ ያሉ ሰዎች እንደሚያጋጥሙህ ጥርጥር የለውም። ይሁንና ይህ ለሌሎች ደግነት እንዳናሳይ ምክንያት ሊሆነን አይችልም። ክርስቲያኖች “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አድርጉ” የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።—ሮም 12:17
ለሌሎች ደግነት ለማሳየት እንድንችል ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍቅር የሚያሳይ ሁሉ ስለ አምላክ እውቀት እንዳለው’ ይናገራል፤ ፍቅር ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ደግሞ ለሌሎች ደግ መሆን ነው። (1 ዮሐንስ 4:7፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4) አዎን፣ ለሰዎች ሁሉ ደግነት በማሳየት አምላክን በተሻለ ሁኔታ ማወቅ የምንችል ሲሆን ይህ ደግሞ ይበልጥ ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ደጎች ደስተኞች ናቸው፤ ደግነት ይደረግላቸዋልና። ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያያሉና።”—ማቴዎስ 5:7, 8 ያንግስ ሊተራል ትራንስሌሽን
ምን መናገር ወይም ማድረግ እንዳለብህ እርግጠኛ በማትሆንበት ጊዜ ደግነት የሚንጸባረቅበት ነገር ተናገር ወይም አድርግ
ሁለት ወንዶች ልጆች ያሏት አኪ የምትባል አንዲት ጃፓናዊ የቤት እመቤትን ምሳሌ እንመልከት። ይህች ወጣት ሴት፣ እናቷን በድንገት በሞት ስታጣ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት አደረባት። አንዳንድ ጊዜ በከባድ ጭንቀት ስለምትዋጥ ሐኪም ማማከር ግድ ይሆንባት ነበር። ከጊዜ በኋላ አንድ ቤተሰብ እነሱ ወዳሉበት አካባቢ ተዛውሮ መኖር ጀመረ። አባትየው በቅርቡ በአደጋ በመሞቱ እናትየው አምስት ትንንሽ ልጆቿን የምታሳድገው ብቻዋን ነበር። አኪ የዚህ ቤተሰብ ሁኔታ በጣም ስላሳዘናት ከእነሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት ማድረግ ጀመረች። አኪ ይህን ቤተሰብ ለመርዳት የተቻላትን ሁሉ ማድረጓ ስሜቷ እንዲረጋጋ ረድቷታል፤ አኪ ለቤተሰቡ ምግብ፣ ልጆቿ የጠበቧቸውን ልብሶችና ሌሎች ነገሮችም ትሰጣቸው ነበር። ይህን በማድረጓም “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነት መሆኑን ከራሷ ተሞክሮ መረዳት ችላለች። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) አዎን፣ በጭንቀት ስትዋጥ ለሌሎች ደግነት ማሳየትህ ከማንኛውም ነገር በላይ ሊጠቅምህ ይችላል።
‘ለይሖዋ ማበደር’
ደግነት ለማሳየት የግድ ብዙ ወጪ ማውጣት አያስፈልግም። ወይም ደግሞ ይህን ማድረግ ለየት ያለ ችሎታ ወይም አካላዊ ጥንካሬ አይጠይቅም። ፈገግ ማለት፣ የሚያጽናና ነገር መናገር፣ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ፣ የታሰበበት አነስተኛ ስጦታ መስጠት ወይም ወረፋ ስንጠብቅ ሌሎችን ማስቀደም ብቻ እንኳ ከፍተኛ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ምን መናገር ወይም ማድረግ እንዳለብህ እርግጠኛ በማትሆንበት ጊዜ ደግነት የሚንጸባረቅበት ነገር ተናገር ወይም አድርግ። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ወጣት፣ አረጋዊው ሚስዮናዊ የቋንቋ እጥረት ቢኖርባቸውም ያሳዩት ደግነት ልቡን በጥልቅ ነክቶታል። በእርግጥም አምላክ ከአገልጋዮቹ ከሚጠብቃቸው መሥፈርቶች አንዱ “ምሕረትን” ወይም ደግነትን መውደድ መሆኑ አያስደንቅም!—ሚክያስ 6:8
“በደግነት የተነገረ አንድ ቃል የሦስት ወሩን ቅዝቃዜ ያስረሳል” የሚል የሩቅ ምሥራቃውያን አባባል አለ። በዚህ አባባል ላይ እንደተገለጸው ደግነት የሚንጸባረቅበት ቀላል ድርጊት ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል። በትክክለኛ ዝንባሌ በተለይም ለአምላክ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ደግነት ማሳየት የእኛም ሆነ ደግነት የምናሳያቸው ሰዎች ልብ በደስታ እንዲሞላ ሊያደርግ ይችላል። ደግነት ያሳየሃቸው ሰዎች አመስጋኝ ባይሆኑም እንኳ ያደረግኸው ነገር በከንቱ እንደ ቀረ ሊሰማህ አይገባም። ደግነት በአምላክ ፊት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ባሕርይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች ደግነት ማሳየት ‘ለይሖዋ እንደ ማበደር’ እንደሚቆጠር ያረጋግጥልናል። (ምሳሌ 19:17) ታዲያ በዙሪያህ ላሉት ሰዎች ደግነት ማሳየት የምትችልበትን አጋጣሚ ለምን አትፈልግም?