ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ጳውሎስ በአቴና የተመለከተው “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት መሠዊያ ምንድን ነው?—የሐዋርያት ሥራ 17:23
▪ በጥንት ዘመን የኖሩ በርካታ የግሪክ ጸሐፊዎች እንዲህ ስላሉት መሠዊያዎች ጠቅሰዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረ ፖሴኒየስ የተባለ የታሪክና የጂኦግራፊ ምሁር በኦሎምፒያ “ለማይታወቁ አማልክት የተሠራ መሠዊያ” እንደነበር ጽፏል። በተጨማሪም በንግግር ችሎታው ታዋቂነትን ያተረፈው ፈላስትረተስ የተባለው ፈላስፋ በአቴና “ለማይታወቁ አማልክት ክብር የቆሙ መሠዊያዎች” እንደነበሩ ተናግሯል።
በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረው ዳያጀኒዝ ሌርሸስ የተባለ ጸሐፊ ስለ እነዚህ “ስም የለሽ መሠዊያዎች” አመጣጥ የሚገልጽ ታሪክ ጽፏል። በስድስተኛው ወይም በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እንደተከናወነ የሚታመነው ይህ ታሪክ ኤፒሜንዲዝ የተባለ ግለሰብ አቴናን እንዴት አድርጎ ከወረርሽኝ እንዳጸዳ ይገልጻል። ዳያጀኒዝ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “[ኤፒሜንዲዝ] . . . በጎችን ወደ አርዮስፋጎስ ካመጣ በኋላ ወደፈለጉበት ቦታ እንዲሄዱ ለቀቃቸው፤ ከዚያም በጎቹን የሚከተሉት ሰዎች እያንዳንዱ በግ ያረፈበት ቦታ ላይ ምልክት እንዲያደርጉና በዚያ ቦታ ለአካባቢው አምላክ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ሰጠ። በዚህ መንገድ ወረርሽኙ እንዳቆመ ይነገራል። በመሆኑም በአቲካ ውስጥ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ስም ያልተቀረጸባቸው መሠዊያዎች ዛሬም ድረስ ይገኛሉ።”
ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እነዚህ ሰዎች ለማይታወቁ አማልክት መሠዊያዎች ይሠሩ የነበረው “ለማይታወቁት ወንድና ሴት አማልክት አክብሮት ሳይሰጡ ቀርተው እነዚህ አማልክት በረከት እንዳይነፍጓቸው ወይም እንዳይቆጧቸው ስለሚፈሩ” ሊሆን እንደሚችልም ገልጿል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችን ይጠሉ የነበረው ለምንድን ነው?
▪ ቀረጥ ሰብሳቢዎች በሰዎች አይወደዱም ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ደግሞ በእስራኤል ውስጥ በጣም ከሚጠሉና ምግባረ ብልሹ እንደሆኑ ተደርገው ከሚታዩ ሰዎች መካከል ይመደቡ ነበር።
በወቅቱ የነበሩት የሮም ባለሥልጣናት በሕዝቡ ላይ ከባድ ግብር ጥለው ነበር። የመሬት ወይም ሌላ ዓይነት ግብርና ቀረጥ የሚሰበስቡት የሮም ባለሥልጣናት ነበሩ፤ ሆኖም ባለሥልጣናቱ ከውጭ በሚመጡ፣ ወደ ውጭ በሚላኩ እና ከውጭ መጥተው በአገሪቱ በሚያልፉ ሸቀጦች ላይ የተጣለውን ግብር የመሰብሰቡን ኃላፊነት የሚሰጡት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ማስገባት ለሚችል ሰው ነበር። ስለዚህ የአካባቢው ነጋዴዎች በአንዳንድ ቦታዎች ቀረጥ የመሰብሰብ መብት ለማግኘት ገንዘብ ይከፍሉ ነበር። በወቅቱ ለሚጠሉት ሮማውያን ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑት እነዚህ ነጋዴዎች “ከአረማውያን ጋር ኅብረት በመፍጠር ራሳቸውን እንዳረከሱ ከሃዲዎች” ተደርገው ስለሚታዩ በሌሎች አይሁዳውያን ዘንድ በጣም ይጠሉ እንደነበር በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ ይገልጻል።
ቀረጥ ሰብሳቢዎቹ የወጣላቸው አጭበርባሪዎች ከመሆናቸውም ሌላ ወገኖቻቸው የሆኑትን አይሁዳውያን ቤት እያራቆቱ የራሳቸውን ኑሮ ያደራጃሉ። አንዳንዶቹ በሸቀጦቹ ላይ ከሚገባው በላይ ቀረጥ በመጣል ትርፉን ወደ ኪሳቸው ያስገቡ የነበረ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ድሆችን በሐሰት በመክሰስ ገንዘባቸውን ይነጥቁ ነበር። (ሉቃስ 3:13፤ 19:8) በዚህም ምክንያት ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንደ ኃጢአተኞች ስለሚታዩ “ዳኛ ሌላው ቀርቶ ምሥክር ለመሆን እንኳ ብቃት እንደሌላቸው ተደርገው ይቆጠሩ” እንደነበር ዘ ጂዊሽ ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል።—ማቴዎስ 9:10, 11
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቱርክ፣ የጴርጋሞን ፍርስራሾች ውስጥ የሚገኝ ለማይታወቅ አምላክ የተሠራ መሠዊያ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀረጥ ሰብሳቢን የሚያሳይ የሮማውያን የተቀረጸ ምስል፣ 2ኛው ወይም 3ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.
[የሥዕሉ ምንጭ]
Erich Lessing/Art Resource, NY