በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አርማጌዶን እውነታው ምንድን ነው?

አርማጌዶን እውነታው ምንድን ነው?

አርማጌዶን እውነታው ምንድን ነው?

“የአጋንንት መናፍስት . . . ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት [ሄደው] . . . በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።”​—ራእይ 16:14, 16 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

አርማጌዶን የሚለው ቃል አንዳንድ ጊዜ “ሐር ማጌዶን” ተብሎም የሚተረጎም ሲሆን የቦታ ስም ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ የሚባል ቦታ በምድር ላይ በየትኛውም አካባቢ የነበረ አይመስልም።

ታዲያ “አርማጌዶን” የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ምንድን ነው? ብዙ ጊዜ እንደ ጦርነት ካለ ክስተት ጋር ተያይዞ የሚጠቀሰውስ ለምንድን ነው?

አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ሐር ማጌዶን የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የመጊዶ ተራራ” ማለት ነው። እንዲህ የሚባል ተራራ ባይኖርም መጊዶ የሚባል ስፍራ ግን አለ። ይህ ቦታ የሚገኘው የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ከሚኖርበት አካባቢ በስተሰሜን ምዕራብ ባለ መስቀለኛ መንገድ ላይ ሲሆን ቦታው ወታደራዊ ጠቀሜታ ነበረው። በዚያ ቦታ አቅራቢያ በርካታ ወሳኝ ጦርነቶች ተካሂደዋል። መጊዶ የሚለው ስም ከጦርነት ጋር የተያያዘው በዚህ ምክንያት ነው። *

ይሁን እንጂ መጊዶ የሚለው ስም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በቦታው የትኞቹ ጦርነቶች ተካሂደዋል ከሚለው ጥያቄ አንጻር ሳይሆን ጦርነቶቹ ከተደረጉበት ምክንያት አኳያ ነው። መጊዶ የሚገኘው ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጣቸው በተስፋይቱ ምድር ውስጥ ነበር። (ዘፀአት 33:1፤ ኢያሱ 12:7, 21) አምላክ፣ ሌሎች ሕዝቦች ከሚሰነዝሩባቸው ጥቃት እንደሚታደጋቸው ለእስራኤላውያን ቃል ገብቶላቸው ነበር፤ ደግሞም ታድጓቸዋል። (ዘዳግም 6:18, 19) ለምሳሌ ያህል፣ ኢያቢስ የተባለው የከነዓናውያን ንጉሥ፣ የሠራዊቱ አለቃ በሆነው በሲሣራ አማካኝነት በእስራኤላውያን ላይ ካካሄደው ወረራ ይሖዋ ሕዝቡን ተአምራዊ በሆነ መንገድ የታደጋቸው በመጊዶ ነው።​—መሳፍንት 4:14-16

ስለዚህ “ሐር ማጌዶን” ወይም “አርማጌዶን” የሚለው ቃል ትልቅ ትርጉም አለው። ቃሉ የተሠራበት በሁለት ኃያል ሠራዊቶች መካከል ከሚካሄድ ውጊያ ጋር ተያይዞ ነው።

በራእይ መጽሐፍ ላይ ያለው ትንቢት፣ በቅርቡ ሰብዓዊ መንግሥታት በሰይጣንና በአጋንንቱ አነሳሽነት ሠራዊቶቻቸውን እንደሚያሰባስቡ ይናገራል፤ ይህንንም ሲያደርጉ የአምላክን ሕዝቦችና ሥራቸውን እንደሚቃወሙ በግልጽ ያሳያሉ። በዚህ ወቅት አምላክ እነዚህን መንግሥታት ድል ስለሚያደርጋቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ።​—ራእይ 19:11-18

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‘ርኅሩኅ፣ ለቍጣ የዘገየና ምሕረቱ የበዛ’ እንደሆነ አድርጎ የሚገልጸው አምላክ ይህን ያህል ሕዝብ እንዲያልቅ የሚያደርገው ለምንድን ነው? (ነህምያ 9:17) አምላክ የሚወስደውን እርምጃ ለመረዳት እንድንችል ቀጥሎ ለቀረቡት ሦስት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልገናል፦ (1) ጦርነቱን የሚጀምረው ማን ነው? (2) አምላክ በጦርነቱ የሚካፈለው ለምንድን ነው? (3) ይህ ጦርነት ለምድርና ለነዋሪዎቿ ምን ያመጣላቸዋል?

1. ጦርነቱን የሚጀምረው ማን ነው?

አርማጌዶን በአምላክ ቆስቋሽነት የሚነሳ ጦርነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጦርነቱ የሚጀምረው አምላክ ጥሩ ሰዎችን ሊደመስሷቸው ከሚነሱ ክፉዎች ለመታደግ እርምጃ ሲወስድ ነው። የዚህ ጦርነት ጠብ አጫሪዎች ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ የተባሉት የዓለም መሪዎች ናቸው። እነዚህ የዓለም መሪዎች ጥቃቱን የሚሰነዝሩት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን፣ እንደ አሻንጉሊት የሚመራቸውን መንግሥታትና ወታደራዊ ኃይሎችን በመቀስቀስ ይሖዋ አምላክን የሚያመልኩ ሰዎችን በሙሉ ለመደምሰስ እንዲነሱ ስለሚያደርጋቸው ነው።​—ራእይ 16:13, 14፤ 19:17, 18

በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ አገሮች ሐሳብን ለመግለጽ መብትና ለሃይማኖት ነፃነት ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጥ ከመሆኑ አንጻር መንግሥታት በየትኛውም ሃይማኖት ላይ እገዳ ለመጣል ወይም ሃይማኖትን እስከ ጭራሹ ለማጥፋት ይነሳሉ ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹ ጥቃቶች በ20ኛው መቶ ዘመን የተፈጸሙ ሲሆን አሁንም እንኳ ሲፈጸሙ እያየን ነው። * እንደዚያም ሆኖ ከዚህ በፊት በደረሱት ጥቃቶችና ከአርማጌዶን ጋር ተያይዞ በሚሰነዘረው ጥቃት መካከል ቢያንስ ሁለት ዋና ዋና ልዩነቶች አሉ። አንደኛ፣ በአርማጌዶን ወቅት መንግሥታት የሚሰነዝሩት ጥቃት ዓለም አቀፋዊ ይሆናል። ሁለተኛ፣ ይሖዋ አምላክ በአጸፋው የሚያደርገው ነገር ባለፉት ዘመናት ከወሰዳቸው እርምጃዎች ሁሉ የሚበልጥ ይሆናል። (ኤርምያስ 25:32, 33) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፍልሚያ ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ ጦርነት’ በማለት ይገልጸዋል።

2. አምላክ በጦርነቱ የሚካፈለው ለምንድን ነው?

ይሖዋ፣ እሱን የሚያመልኩትን ሰዎች ሰላማዊ እንዲሆኑና ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ አዝዟቸዋል። (ሚክያስ 4:1-3፤ ማቴዎስ 5:43, 44፤ 26:52) ስለዚህ አምላኪዎቹ ከላይ የተጠቀሰው የጭካኔ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ራሳቸውን ለመከላከል የጦር መሣሪያ አያነሱም። አምላክ ሕዝቦቹን ለማዳን ጣልቃ ገብቶ እርምጃ ካልወሰደ መንግሥታት ሙሉ በሙሉ ያጠፏቸዋል። ይህ ደግሞ የይሖዋ አምላክ ስም እንዲነቀፍ ያደርጋል። እነዚህ መንግሥታት የአምላክን ሕዝቦች ማጥፋት ከቻሉ ይሖዋ ፍቅር እንደጎደለው፣ ፍትሐዊ እንዳልሆነ ወይም አቅም እንደሌለው አምላክ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ይህ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው!​—መዝሙር 37:28, 29

አምላክ ማንንም ማጥፋት ስለማይፈልግ ወደፊት ስለሚያደርገው ነገር አስቀድሞ ተገቢውን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (2 ጴጥሮስ 3:9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች እንደሚያሳዩት በቀድሞ ዘመን የአምላክ ሕዝቦች ጥቃት በተሰነዘረባቸው ጊዜ አምላክ የበቀል እርምጃ ወስዶ ነበር፤ እነዚህ ታሪኮች ለሁሉም ሰው ትምህርት የሚሰጡ ናቸው። (2 ነገሥት 19:35) በተጨማሪም ወደፊት ሰይጣንና እንደ አሻንጉሊት የሚያንቀሳቅሳቸው ሰብዓዊ ወኪሎቹ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ይሖዋ በድጋሚ ጣልቃ እንደሚገባና የኃይል እርምጃ በመውሰድ የእጃቸውን እንደሚሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። እንዲያውም የአምላክ ቃል ይሖዋ ክፉዎችን እንደሚያጠፋ ከረጅም ጊዜ በፊት ትንቢት ተናግሯል። (ምሳሌ 2:21, 22፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-9) በዚያን ጊዜ እነዚህ ጠብ አጫሪዎች በገዛ እጃቸው ቆስቁሰው ጦርነት የገጠሙት ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እንደሆነ ይገነዘባሉ።​—ሕዝቅኤል 38:21-23

3. ይህ ጦርነት ለምድርና ለነዋሪዎቿ ምን ያመጣላቸዋል?

የአርማጌዶን ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንዲተርፍ ምክንያት ይሆናል። እንዲያውም ይህ ጦርነት ከዚያ በኋላ በምድር ላይ ለሚኖረው ሰላም የሰፈነበት ዘመን መንገድ ይከፍታል።​—ራእይ 21:3, 4

የራእይ መጽሐፍ ከዚህ ጦርነት በሕይወት ስለሚተርፍ ስፍር ቁጥር የሌለው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ይናገራል። (ራእይ 7:9, 14) እነዚህ ሰዎች የአምላክን አመራር በመከተል ይሖዋ መጀመሪያ አስቦት እንደነበረው ምድርን ገነት በማድረጉ ሥራ ተካፋይ ይሆናሉ።

ይሁን እንጂ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት የሚሰነዘረው መቼ እንደሆነ የምናውቀው ነገር አለ?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 አንድን ቦታ ከጦርነት ጋር ማያያዝ አዲስ ነገር አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በአቶሚክ ቦምብ ምክንያት ሙሉ በሙሉ የተደመሰሰችው ሂሮሺማ የተባለች የጃፓን ከተማ አሁን ከኑክሌር ጦርነት ጋር በተያያዘ ትታወሳለች።

^ አን.13 ናዚዎች ያደረሱት እልቂት፣ አንድ መንግሥት የተወሰኑ ሃይማኖታዊ ቡድኖችንና ዘሮችን ከምድር ገጽ ለማጥፋት ያደረገውን ሙከራ የሚያሳይ ነው። በሶቪየት ኅብረት ሥር በነበሩ ግዛቶች ውስጥ ያሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖችም ከባድ ጭቆና ደርሶባቸው ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች በሚዘጋጀው መጠበቂያ ግንብ መጽሔት የግንቦት 1, 2011 እትም ላይ የወጣውን “በሩሲያ የሚኖሩ ሰላማዊ ሕዝቦች ለስማቸው ጥብቅና ቆሙ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ አምላክ በቀድሞ ዘመን ሕዝቦቹን ታድጓል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ወደፊትም በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ሕዝቦቹን ይታደጋል