መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
ቁማርተኛና ዘራፊ የነበረ ሰው ከእነዚህ ጎጂ ልማዶች እንዲላቀቅና ሕይወቱን እንዲለውጥ ያነሳሳው ምንድን ነው? እስቲ ምን እንደሚል እንስማ።
“የፈረስ ግልቢያ ውድድር በጣም እወድ ነበር።”—ሪቻርድ ስቱዋርት
የትውልድ ዘመን፦ 1965
የትውልድ አገር፦ ጃማይካ
የኋላ ታሪክ፦ ቁማርተኛና ወንጀለኛ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት በጃማይካ ዋና ከተማ በኪንግስተን ሲሆን ሰፈራችን ችምችም ያሉ ቤቶች ያሉበትና ድሆች የበዙበት ነበር። በአካባቢው ብዙ ሥራ አጦች ከመኖራቸውም ባሻገር ወንጀል ተስፋፍቷል። ወሮበሎች በሚፈጽሙት ድርጊት የተነሳ የሰዎች ሕይወት በስጋት የተሞላ ነበር፤ በየቀኑ ማለት ይቻላል ተኩስ እሰማ ነበር።
ትጉህ ሠራተኛ የነበረችው እናታችን ለእኔም ሆነ ለታናሽ ወንድሜና እህቴ የማትሆነው ነገር አልነበራትም። ጥሩ ትምህርት ቤት ብታስገባንም እኔ ግን ልቤ ወደ ትምህርት ያዘነበለ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የፈረስ ግልቢያ ውድድር በጣም እወድ ነበር። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ትምህርቴን ትቼ የፈረስ ግልቢያ ውድድር ለማየት እሄዳለሁ። ፈረስ የምጋልብባቸው ጊዜያትም ነበሩ።
ብዙም ሳይቆይ በፈረስ ግልቢያ ውድድር ላይ መወራረድ የጀመርኩ ሲሆን በቁማር ተዘፈቅኩ። መጥፎ ሥነ ምግባር ነበረኝ፣ ከብዙ ሴቶች ጋር እማግጥ እንዲሁም ማሪዋና አጨስ ነበር። በመሆኑም ለምፈጽማቸው ድርጊቶች ገንዘብ ለማግኘት ስል ዝርፊያ ጀመርኩ። በወቅቱ በርካታ መሣሪያዎች ነበሩኝ፤ አሁን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስበው፣ በፈጸምኳቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዝርፊያዎች በእኔ እጅ የሰው ሕይወት ባለማለፉ አመስጋኝ ነኝ።
ውሎ አድሮ ግን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋልኩና ለሠራሁት ወንጀል ወኅኒ ወረድኩ። ከእስር ቤት ስወጣም ወደነበርኩበት አኗኗር ተመለስኩ። እንዲያውም ከቀድሞው ይልቅ ባሰብኝ። ሰዎች ሲያዩኝ ምስኪን ብመስልም ግትር፣ ግልፍተኛና ጨካኝ ነበርኩ። ከራሴ ሌላ ስለ ማንም ደንታ አልነበረኝም።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ሕይወቴ ምስቅልቅል ባለበት በዚህ ወቅት እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። የእናቴ ባሕርይ ሲሻሻል መመልከቴ እንድትለወጥ ያደረጋት ምን እንደሆነ ለማወቅ አነሳሳኝ፤ ስለዚህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ጀመርኩ።
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩት ትምህርት ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለየ እንደሆነና ለእያንዳንዱ ነገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንደሚያቀርቡ ተረዳሁ። እኔ እስከማውቀው ድረስ እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚሰብኩት እነሱ ብቻ ነበሩ። (ማቴዎስ 28:19፤ የሐዋርያት ሥራ 20:20) አንዳቸው ለሌላው የሚያሳዩትን ልባዊ ፍቅር ስመለከት እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ።—ዮሐንስ 13:35
ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተማርኩት ነገር በመነሳት በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ተረዳሁ። ይሖዋ አምላክ ሴሰኝነትን እንደሚጠላና እሱን ማስደሰት ከፈለግሁ ደግሞ ሰውነቴን ከሚያረክሱ ድርጊቶች መራቅ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። (2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ዕብራውያን 13:4) ይሖዋ ስሜት እንዳለውና የማደርጋቸው ነገሮች ሊያሳዝኑትም ሆነ ሊያስደስቱት እንደሚችሉ ተምሬያለሁ፤ ይህ ደግሞ ለውጥ ለማድረግ አነሳሳኝ። (ምሳሌ 27:11) በመሆኑም ማሪዋና ማጨሴን ለማቆም፣ መሣሪያ ላለመያዝና ባሕርዬን ለማሻሻል ቆርጬ ተነሳሁ። በጣም ተፈታታኝ የነበረው ግን ከሥነ ምግባር ውጭ የነበረውን ሕይወቴን መቀየርና ቁማር መተው ነበር።
መጀመሪያ አካባቢ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደማጠና ጓደኞቼ እንዲያውቁ አልፈለግኩም። ይሁንና ኢየሱስ በማቴዎስ 10:33 ላይ “በሰዎች ፊት የሚክደኝን ሁሉ እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ” በማለት የተናገረውን ሳነብ ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ተረዳሁ። ጥቅሱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደማጠና ለጓደኞቼ እንድነግራቸው አነሳሳኝ። ጓደኞቼ ይህን ሲሰሙ በጣም ደነገጡ። እንደ እኔ ያለ ሰው ክርስቲያን ለመሆን መፈለጉ በራሱ አስገረማቸው። እኔ ግን ከአሁን በኋላ የበፊቱን አኗኗሬን መከተል እንደማልፈልግ አስረግጬ ነገርኳቸው።
ያገኘሁት ጥቅም፦ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ስጀምር እናቴ በጣም ተደሰተች። አሁን፣ መጥፎ ድርጊት ይፈጽማል ብላ አትሰጋም። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ከእናቴ ጋር ይበልጥ ያቀራረበን ሲሆን ብዙ ጊዜ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች እናወራለን። አንዳንድ ጊዜ የቀድሞውን አኗኗሬን ሳስታውስ በአምላክ እርዳታ ይህን ያህል መለወጤ አሁንም ድረስ በጣም ያስገርመኛል። ከዚህ በፊት የነበረኝ ዓይነት በሥነ ምግባር ያዘቀጠና በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ሕይወት አያጓጓኝም።
ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምላሽ ባልሰጥ ኖሮ መጨረሻዬ እስር ቤት አሊያም ሞት ነበር።። በአሁኑ ጊዜ ግን ግሩምና አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት እመራለሁ። የምትደግፈኝ ሚስትና ጥሩ ልጅ አለችኝ፤ ከእነሱ ጋር ሆኖ ይሖዋ አምላክን ማገልገል ትልቅ ደስታ አስገኝቶልኛል። አፍቃሪ በሆነው የክርስቲያን የወንድማማች ኅብረት ውስጥ እንድታቀፍ በማድረጉ ይሖዋን ዘወትር አመሰግነዋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን እንድማር ለመርዳት ጥረት ያደረገ ሰው በመኖሩም አመስጋኝ ነኝ። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለሌሎች የማስተማር መብቴን ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ አምላክ ወደ እሱ እንድቀርብ ላሳየኝ ፍቅራዊ ደግነት አመሰግነዋለሁ።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ይሖዋ ስሜት እንዳለውና የማደርጋቸው ነገሮች ሊያሳዝኑትም ሆነ ሊያስደስቱት እንደሚችሉ ተምሬያለሁ”
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእናቴ ባሕርይ መሻሻሉን ተመለከትኩ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴና ከልጄ ጋር