ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተራውን ሕዝብ የሚመለከቱት እንዴት ነበር?
▪ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በእስራኤላውያን ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ሰዎችና የሃይማኖት መሪዎች፣ እምብዛም ያልተማሩትንም ሆነ ጨርሶ ያልተማሩትን ሰዎች ዝቅ አድርገው ይመለከቱ ነበር። እንዲያውም ፈሪሳውያን “ሕጉን የማያውቀው ይህ ሕዝብ . . . የተረገመ ነው” በማለት ይናገሩ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል።—ዮሐንስ 7:49
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያሉ አንዳንድ ምንጮች እንደሚያሳዩት በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች ያልተማሩትን ሰዎች አምሃአሬትስ (“የምድሪቱ ሰዎች” ወይም ‘የአገሬው ሰዎች’ የሚል ፍቺ አለው) በማለት በንቀት ይጠሯቸው ነበር። መጀመሪያ ላይ አምሃአሬትስ የሚለው ቃል በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን በሙሉ ለማመልከት የሚያገለግል የአክብሮት መጠሪያ ነበር። ይህ ቃል ድሆችንና ተራ የሆኑ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ከፍ ተደርገው የሚታዩ ሰዎችንም ጭምር ያመለክት ነበር።—ዘፍጥረት 23:7፤ 2 ነገሥት 23:35፤ ሕዝቅኤል 39:13
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ግን ይህ ቃል የሙሴን ሕግ በደንብ የማያውቁ ወይም የረቢዎችን ዝርዝር ወጎች የማይጠብቁ ሰዎችን ለማመልከት የሚያገለግል የንቀት መጠሪያ ሆኖ ነበር። ሚሽና የተባለው መጽሐፍ (ለታልሙድ መሠረት የሆነው የትንታኔዎች ጥንቅር) አምሃአሬትስ ተብለው በሚጠሩ ሰዎች ቤት ማደርን ያወግዛል። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ታልሙዲክ ሴጅስ የተባለው መጽሐፍ በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖሩት ሚር የተባሉ ምሑርና ረቢ የሆኑ አንድ ሰው እንዲህ ሲሉ ማስተማራቸውን ገልጿል፦ “አንድ ሰው ሴት ልጁን አምሃአሬጽ ለሆነ ሰው መዳሩ የልጁን እጅና እግር ጠፍሮ በማሰር እሷን ለመብላት አሰፍስፎ ለሚጠብቅ አንበሳ እንደመስጠት ይቆጠራል።” ሌላ ረቢ ደግሞ “ያልተማሩ ሰዎች ትንሣኤ አያገኙም” በማለት መናገራቸውን ታልሙድ ጠቅሷል።
ቄሳር የሚለው መጠሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ምንን ለማመልከት ነው?
▪ ቄሳር የሚለው መጠሪያ በ46 ዓ.ዓ. በሮም ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ መግዛት የጀመረው የጋየስ ጁሊየስ ቄሳር የቤተሰብ ስም ነው። ከጁሊየስ በኋላ የነገሡ በርካታ የሮም ንጉሠ ነገሥታትም ቄሳር በሚለው መጠሪያ ይጠቀሙ ነበር፤ ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ማለትም አውግስጦስ፣ ጢባርዮስና ቀላውዴዎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስም ተጠቅሰዋል።—ሉቃስ 2:1፤ 3:1፤ የሐዋርያት ሥራ 11:28
ጢባርዮስ ንጉሠ ነገሥት የሆነው በ14 ዓ.ም. ሲሆን ኢየሱስ ምድር ላይ ባገለገለባቸው ዓመታት ሁሉ የሮም ገዥ የነበረው እሱ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ግብር መክፈልን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” የሚል መልስ በሰጠበት ጊዜ በሥልጣን ላይ የነበረው ቄሳር ጢባርዮስ ነበር። (ማርቆስ 12:17) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ “ቄሳር” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ጢባርዮስን ብቻ ለማመልከት አልነበረም። ይህ ቃል የአገሪቱን መንግሥት በአጠቃላይ ለማመልከትም ያገለግላል።
በ58 ዓ.ም. ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ የፍትሕ መጓደል በደረሰበት ጊዜ የሮም ዜግነቱ ያስገኘለትን መብት ተጠቅሞ ወደ ቄሳር ይግባኝ ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 25:8-11) ጳውሎስ ወደ ቄሳር ይግባኝ ሲል በወቅቱ የሮም ንጉሠ ነገሥት በነበረው በኔሮ በቀጥታ ለመዳኘት መጠየቁ ሳይሆን ጉዳዩ በሮም ግዛት ውስጥ ባለ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲታይለት ጥያቄ ማቅረቡ ነበር።
ቄሳር የሚለው የቤተሰብ ስም ሉዓላዊ የሆነን መንግሥት ለማመልከት የሚሠራበት የተለመደ ቃል እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ የቄሳር ሥርወ መንግሥት ካበቃም በኋላ ሥልጣን ላይ ለሚወጡ ሰዎች ሕጋዊ መጠሪያ በመሆን ማገልገሉን ቀጥሎ ነበር።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጢባርዮስ ምስል የተቀረጸበት የብር ዲናር