መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
አንዲት ታዋቂ ዘፋኝ በወንጌላዊነት ሥራ ረዘም ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ስትል ሙያዋን የተወችው ለምንድን ነው? እንዲሁም አንድ ዳኛ ፈጽሞ የማይታረም እንደሆነ አድርገው የገለጹት አንድ ወንጀለኛ ለኅብረተሰቡ የሚጠቅም ዜጋ እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው? ለመልሱ ቀጥሎ የቀረቡትን የሕይወት ታሪኮች አንድታነብ እንጋብዝሃለን።
“ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል የለም።”—አንቶሊና ኦርዴን ካስቲዮ
የትውልድ ዘመን፦ 1962
የትውልድ አገር፦ ስፔን
የኋላ ታሪክ፦ ተዋናይና ዘፋኝ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት ላ ማንቻ በተባለው ክልል ውስጥ በምትገኘው ትሬስሁንኮስ በምትባል አንዲት አነስተኛ መንደር ነው። ቤተሰቦቼ የሚተዳደሩት በግብርና ነበር። እናቴ ካቶሊክ ስትሆን አባቴ ደግሞ ፕሮቴስታንት ነበር። አባቴ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲኖረኝ ያስተማረኝ ከመሆኑም ሌላ ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ አየው ነበር። ይሁን እንጂ እናቴ ካቶሊክ አድርጋ ያሳደገችኝ ሲሆን እሁድ እሁድ ወደ ቅዳሴ ይዛኝ ትሄድ ነበር።
አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ የትውልድ ቀዬን ትቼ ከታላቅ እህቴ ጋር ለመኖር ወደ ማድሪድ አቀናሁ። ወላጆቼን በጣም ብናፍቅም ቀስ እያልኩ ግን የከተማውን ኑሮ ለመድኩት። በ17 ዓመቴ ዛርዙዌይላ በተባለ በስፔን የባሕል ሙዚቃዊ ተውኔት ውስጥ ገብቼ ለጥቂት ወራት የመሥራት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ይህን ሕይወት በጣም ስለወደድኩት ተዋናይ ለመሆን ወሰንኩ። ስለዚህ በጸሐፊነት ሙያ ለመሰማራት ስከታተል የነበረውን ትምህርት ትቼ ከተለያዩ የዛርዙዌይላ ኩባንያዎች ጋር መሥራት ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ ከጓደኛዬ ወንድም ጋር የፍቅር ጓደኝነት ጀመርኩ። ጥሩ ሥራ፣ ገንዘብና ፍቅረኛ ስላገኘሁ በጣም ዕድለኛ እንደሆንኩ ተሰማኝ።
ከተለያዩ የዛርዙዌይላ ኩባንያዎች ጋር በመሆን በመላው ስፔን እንዲሁም እንደ ኮሎምቢያ፣ ኮስታ ሪካ፣ ኢኳዶርና ቬኔዙዌላ ወደመሳሰሉት ሌሎች አገሮች እየተዘዋወርኩ መዝፈን ጀመርኩ። እንዲሁም በማድሪድ ውስጥ“ላ ሞቬዳ ማድሪላኛ” በመባል የሚጠራ ተወዳጅ የሙዚቃ ስልት ከሚከተሉ የተለያዩ ቡድኖች ጋርም እዘፍን ነበር። በዋና ድምፃዊነት እሠራበት የነበረው አንደኛው ቡድን በጣም ስኬታማ ሆኖ ነበር።
ሥራውን ብወደውም በዙሪያዬ የማየውን ሥነ ምግባራዊ ብልሹነት እጠላው ነበር። ከዚህም በላይ ስለ ውበቴና ስለ ስሜ ከልክ በላይ መጨነቅ ጀመርኩ። በጣም ጥብቅ የሆነ የአመጋገብ ልማድ እከተል ስለነበር በአመጋገብ ችግር ምክንያት የሚመጣ የጤና መታወክ ደረሰብኝ።
ያም ሆኖ ዋነኛው ግቤ ተዋናይ መሆን ነበር። ውሎ አድሮም በማድሪድ የድራማ ጥበብ ትምህርት ቤት ገብቼ መማር ጀመርኩ። የትወና ሙያ፣ የገጸ ባሕርይውን ስሜት በጥልቀት መረዳትንና ያንን ስሜት ከራስ ጋር ማዋሃድ እንደሚጠይቅ በትምህርት ቤቱ ተምረን ነበር። ይህን ምክር ተግባራዊ ሳደርግ የራሴ የምለው ስሜት እያጣሁ መጣሁ። በዚህም ምክንያት አስመሳይና ራስ ወዳድ ሴት ሆንኩ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ጥሩ ባሕርያትን ማዳበር ከፈለግሁ ጥረት ማድረግ እንዳለብኝ አውቅ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ ከየት መጀመር እንዳለብኝ አላውቅም ነበር። በመሆኑም በአንድ ወቅት ከወላጆቼ ጋር ሄጄበት ወደነበረ ማድሪድ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የኢቫንጀሊካን ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ወሰንኩ። በተጨማሪም ይሖዋ የሚለውን ስሙን እየጠራሁ ወደ አምላክ ጸለይኩ።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቴ መጡ። ከእነሱ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በከፍተኛ ጉጉት ብወያይም ከትምህርታቸው ውስጥ ብዙ የማልቀበላቸው ነገሮች እንዳሉ ገለጽኩ። መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት የምታስጠናኝ ኤስተር የተባለችው የይሖዋ ምሥክር በጣም ታጋሽ ነበረች። እሷና ቤተሰቧ ይህ ነው የማይባል ፍቅርና አሳቢነት አሳይተውኛል። በኋላም የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመርኩ ሲሆን ስፈልገው የነበረውን እውነት እንዳገኘሁ ወዲያው ተገነዘብኩ።
የድራማ ጥበብ ትምህርቴን ገና ከመጨረሴ ብዙ የሥራ አጋጣሚ ተከፈተልኝ። በማድሪድ ውስጥ በአንድ ታዋቂ ቲያትር ቤት በሚቀርብ ተውኔት ላይ አንድን ገጸ ባሕርይ ወክዬ እንድጫወት ተጋብዤ ነበር። ይሁን እንጂ በትወና ሥራ ስኬታማ ለመሆን ሙሉ በሙሉ ራሴን ለሙያው ማስገዛት እንዳለብኝ ተገንዝቤ ነበር። በመጨረሻም አምላክን በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት እንድመራ የሚያስችለኝ ሌላ ዓይነት ሥራ ለመፈለግ ወሰንኩ። ኢየሱስ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም ለአንዱ ተገዝቶ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም” በማለት የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን ተረድቼ ነበር። (ማቴዎስ 6:24) ለስምንት ዓመታት አብሮኝ የቆየው የወንድ ጓደኛዬ በወሰድኩት አቋም ስላልተስማማ ከእሱ ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማቆም ወሰንኩ። እነዚህን ውሳኔዎች ማድረግ ቀላል አልነበረም።
ያገኘሁት ጥቅም፦ አሁን የምሠራው ሥራ አረጋውያንን በሳምንት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ማዝናናት ነው። ይህ ሥራዬ በአካባቢዬ ለሚኖሩ አረብኛ ተናጋሪ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ሰፊ ጊዜ እንዳገኝ አስችሎኛል። ቋንቋውን ለመማር ጥረት ማድረግ ቢጠይቅብኝም ሰው ወዳድ ለሆኑና መንፈሳዊ ፍላጎት ላላቸው ለእነዚህ ሰዎች የተማርኳቸውን መልካም ነገሮች ማካፈል በጣም ያስደስተኛል።
ተዋናይ ለመሆን በምማርበት ጊዜ ይሰማኝ የነበረው የባዶነት ስሜት ተወግዶ አሁን ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት ችያለሁ። ይሖዋ የተሻልኩና ደስተኛ ሰው እንድሆን እንደረዳኝ ይሰማኛል።
“ዳኛው እንደተሳሳቱ በተግባር ማሳየት ችያለሁ።”—ፖል ኬቨን ሩቤሪ
የትውልድ ዘመን፦ 1954
የትውልድ አገር፦ እንግሊዝ
የኋላ ታሪክ፦ አደገኛ ወንጀለኛ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በዌስት ሚድላንድስ በምትገኘው ደድሊ የተባለች ትልቅ የኢንዱስትሪ ከተማ ነው። አባቴ ያሳደገኝ የንባብ ፍቅር እንዲኖረኝ አድርጎ ነው። ምንም እንኳ አባቴ ተፈጥሮ የተገኘው በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ ቢያምንም የተፈጥሮን ውበት እንዳደንቅ ያበረታታኝ ነበር። አምላክ የሚባል ነገር እንደሌለ ያስተምረኝ ነበር። ያም ሆኖ ወላጆቼ በአካባቢያችን ወደሚገኝ የሜቶዲስት ሰንበት ትምህርት ቤት ይልኩኝ ነበር።
የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ በአካባቢያችን የሚኖሩ ልጆች አንድ ጀልባ ሲያቃጥሉ አየኋቸው። ልጆቹ አስፈራርተውኝ ስለነበር ፖሊስ መጥቶ ሲጠይቀኝ ማን እንዳቃጠለ ሳልናገር ቀረሁ። በዚህ ጊዜ ያለ ጥፋቴ የተወነጀልኩ ሲሆን እኔም የበቀል ስሜት አደረብኝ። በዚህም የተነሳ በአካባቢው ባሉት አንዳንድ ትምህርት ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያናትና ፋብሪካዎች ላይ ጉዳት በማድረስ በብዙ ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ንብረት አወደምኩ። አሥር ዓመት ሲሆነኝ መኖሪያ ቤቶችንና ሱቆችን ሰብሬ እየገባሁ መስረቅ ጀመርኩ። ማቃጠል በጣም ስለሚያስደስተኝ ብዙ ነገሮችን በማጋየት ወንጀል እፈጽም ነበር። በትምህርት ቤት አስተማሪዎች ከአቅም በላይ እንደሆንኩ ይናገሩ ነበር።
የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ ስለ ምትሐታዊ ኃይል የሚናገር መጽሐፍ ሳገኝ በዚያ ላይ ተመርኩዤ የራሴን የጥንቆላ ሰሌዳ ሠራሁ። ወላጆቼ በአምላክ ስለማያምኑ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች ለማወቅ ጉጉት ማሳደሬ ምንም ጉዳት የሌለው ተራ ጨዋታ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር፤ እንዲያውም ጊዜዬን ስለሚሻማብኝ ችግር ውስጥ ከመግባት ይገላግለዋል ብለው አስበው ነበር። ይሁን እንጂ ትምህርቴን እስከጨረስኩበት ጊዜ ድረስ ወጣት ጥፋተኞች በሚዳኙበት ፍርድ ቤት ብዙ ጊዜ ቀርቤያለሁ። በወቅቱ ስኪንሄድስ ተብሎ በሚጠራ አንድ የዓመፀኞች ቡድን ውስጥ ገብቼ ነበር። ሰዎችን ለማጥቃት ምላጭና የብስክሌት ካቴና እይዝ ነበር። ሥራ አግኝቼ የነበረ ቢሆንም ለአጭር ጊዜ እስራት ስለተፈረደብኝ ወዲያውኑ ሥራዬን አጣሁ። ከተፈታሁ በኋላም ንብረት ማውደም በመጀመሬ እንደገና ተይዤ የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ። ዳኛው ፈጽሞ የማልታረምና ለኅብረተሰብ ጠንቅ እንደሆንኩ ተናግረው ነበር።
ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ከቀድሞ ጓደኛዬ ከአኒታ ጋር ተገናኘሁ። በኋላም ተጋባንና ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሳልሰርቅ ወይም ምንም ችግር ሳልፈጥር ቆየሁ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን እንደገና ወደ ወንጀል ተግባሬ ተመለስኩ። የንግድ ቤቶችን ሰብሬ በመግባት ካዝናቸውን መዝረፍ ጀመርኩ። አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ፣ ከልክ በላይ መጠጣትና ሽጉጥ መያዝ ጀመርኩ። አሁንም እንደገና ተይዤ እስራት ተፈረደብኝ።
የእኔ ሁኔታ አኒታን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከተታት። ሐኪሟ አእምሮዋን የሚያረጋጉ መድኃኒቶችን አዘዘላት፤ ይሁን እንጂ ትክክለኛው መፍትሔ እኔን መፍታት እንደሆነ ነገራት። ደግነቱ የሐኪሙን ምክር አልተቀበለችም፤ ይህ ደግሞ ለእኔ ጥሩ ሆነልኝ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? የተጋባን ሰሞን አኒታ ለጥቂት ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታ ነበር። ከዚያም እኔ እስር ቤት ሳለሁ (የመጨረሻው እስራቴ መሆኑ ነው) እንደገና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች። “በእርግጥ ካለህ መኖርህን አረጋግጥልኝ” ብዬ በዚያው ቀን ወደ አምላክ ጸልዬ ነበር፤ አኒታ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘችበት ቀንና እኔ የጸለይኩበት ቀን መገጣጠሙ የሚገርም ነው።
ከጥቂት ወራት በኋላ ከእስር ቤት ስለቀቅ የአካባቢውን ቄስ አገኘሁትና እኔንና አኒታን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠናን ጠየቅሁት። እሱም የቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ሥርዓትና ጸሎት ብቻ እንደሚያስተምረን ነገረኝ።
በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስ መናፍስታዊ ድርጊቶችን እንደሚያወግዝ ሳውቅ ተገረምኩ። (ዘዳግም 18:10-12) በኋላም፣ አምላክ እንዲረዳኝ በጸለይኩበት ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ለአኒታ ትተውላት የሄዱትን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አገኘሁ። ያነበብኩት ነገር የይሖዋ ምሥክሮችን ለማግኘት እንድነሳሳ አደረገኝ።
ቤተሰቦቻችን፣ ወዳጆቻችንና በወንጀል ድርጊት አብረውኝ የሚካፈሉት ጓደኞቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እየተማርን መሆኑን ሲያውቁ አልተደሰቱም። አንዳንዶቹም፣ የይሖዋ ምሥክሮች አእምሮዬን እያጠቡት መሆኑን ተናገሩ። እውነቱን ለመናገር፣ አእምሮዬ መጽዳት ያስፈልገው ነበር። ሕሊናዬ የደነዘዘ ከመሆኑም በላይ ብዙ የባሕርይ ችግሮች ነበሩብኝ፤ በዚያ ላይ በቀን እስከ 60 የሚደርስ ሲጋራ አጨስ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር የረዱንና በጉባኤ አብረናቸው የምንሰበሰብ ሌሎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ለእኛ ትልቅ ትዕግሥትና ደግነት አሳይተውናል። የኋላ ኋላም ከመጥፎ ልማዶቼ ሙሉ በሙሉ ተላቀቅሁ።—2 ቆሮንቶስ 7:1
ያገኘሁት ጥቅም፦ አሁን እኔና አኒታ ከተጋባን 35 ዓመት ሆኖናል። አንደኛዋ ልጃችንና ሁለት የልጅ ልጆቻችን አብረውን ይሖዋን እያገለገሉ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እኔና አኒታ አብዛኛውን ጊዜያችንን ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ በመርዳቱ ሥራ ማዋል ችለናል።
ይሖዋ አምላክን ማገልገላችን ሕይወታችን እውነተኛ ዓላማና ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርጎታል። በ1970 አንድ ዳኛ ፈጽሞ መታረም እንደማልችል ለፍርድ ቤቱ ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ በአምላክ እርዳታና ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘሁት አመራር ዳኛው እንደተሳሳቱ በተግባር ማሳየት ችያለሁ።