በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖሩት እነማን ናቸው?
በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖሩት እነማን ናቸው?
በአውሮፓ አንዲት አረጋዊት ሴት መቁጠሪያ ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመግባት በማርያም ምስል ፊት ተንበርክከው ይጸልያሉ። በአፍሪካ የሚኖሩ አንድ ቤተሰብ በሚያከብሩት ዘመዳቸው መቃብር አጠገብ የአልኮል መጠጥ ያፈስሳሉ። በአሜሪካ አህጉራት ደግሞ አንድ ወጣት የራሱ ጠባቂ መልአክ እንዳለው የሚያምን ሲሆን ወደዚህ መልአክ መቅረብ እንደሚችል ተስፋ በማድረግ ይጾማል እንዲሁም ያሰላስላል። በእስያ፣ አንድ ቄስ የተለያዩ ቀለማት ባላቸው ወረቀቶች የተሠሩ ነገሮችን በማቃጠል ለቀድሞ አባቶች መናፍስት መሥዋዕት ያቀርባል።
እነዚህን ሰዎች የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? ሁሉም፣ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ የማሰብ ችሎታ ያላቸው አካላት እንዳሉ የሚያምኑ ሲሆን እነዚህ መንፈሳዊ አካላት በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ እንዲሁም እነሱን ማነጋገር እንደሚቻል ይሰማቸዋል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ብሎ ማመን በአሁኑ ጊዜ የተጀመረ ወይም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። የሚያስገርመው ነገር፣ በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖሩት እነማን ስለመሆናቸው እርስ በርሳቸው የሚጋጩ በጣም ብዙ አመለካከቶች መኖራቸው ነው።
ሙስሊሞች አንድ አምላክን ማለትም አላህን * ያመልካሉ። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ አምላክ ሥላሴ እንደሆነ ይኸውም እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ እንደሆኑ ይናገራሉ። ሂንዱዎች፣ ከሺህ የሚበልጡ ተባዕትና እንስት አማልክት እንዳሉ ያምናሉ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ መናፍስት በአንዳንድ እንስሳት፣ ዛፎች፣ ዓለቶችና ጅረቶች ውስጥ እንደሚኖሩ ያስባሉ። አንዳንዶች ስለ መላእክትና አጋንንት፣ ስለ ሙታን መናፍስትና ርኩሳን መናፍስት እንዲሁም ስለ ተባዕትና እንስት አማልክት በመጻሕፍት፣ በፊልሞችና በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የሚቀርበው ነገር ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል።
አማልክትን በተመለከተ የተለያዩና እርስ በርስ የሚጋጩ በርካታ አመለካከቶች የመኖራቸውን ያህል ወደ እነዚህ አማልክት መቅረብ ስለሚቻልበት መንገድም የተለያዩና እርስ በርስ የሚጋጩ ብዙ አመለካከቶች አሉ። ሰዎች ከመንፈሳዊ አካላት ጋር ለመነጋገር የሚጠቀሙባቸው መንገዶች በሙሉ ትክክል ናቸው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው። እስቲ አስበው፦ ስልክ ከመደወላችን በፊት ለማን እንደምንደውል ማወቅ እንዲሁም የምንደውልለት ሰው በሕይወት መኖሩንና እኛን ለማነጋገር ፈቃደኛ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልገናል። በምናባችን ከፈጠርነው ሰው ጋር ለመገናኘት መሞከር ትርጉም አይኖረውም። ከሁሉ የከፋው ደግሞ አታላይ ከሆነ ሰው ጋር መገናኘት ሲሆን ይህም ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል።
ታዲያ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ የሚኖሩት እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጠን ከመሆኑም ሌላ ማንን ማነጋገር እንዳለብንና ምን ዓይነት ምላሽ መጠበቅ እንደምንችል ይገልጻል። ቀጥሎ የቀረቡትን ርዕሶች ማንበብህን እንድትቀጥል እናበረታታሃለን። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ስታውቅ ትገረም ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 “አላህ” ስም ሳይሆን “አምላክ” የሚል ትርጉም ያለው ቃል ነው።