“በቤት ውስጥ የሚሠሩ”
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሕይወት
“በቤት ውስጥ የሚሠሩ”
“እየተጓዙ ሳሉም ወደ አንድ መንደር ገባ። በዚያም ማርታ የምትባል አንዲት ሴት በቤቷ በእንግድነት ተቀበለችው። ይህች ሴት ማርያም የምትባል እህት ነበረቻት፤ ይሁንና ማርያም በጌታ እግር ሥር ተቀምጣ የሚናገረውን ታዳምጥ ነበር። ማርታ ግን በብዙ ሥራ ተጠምዳ ትባክን ነበር። በመሆኑም ወደ እሱ ቀርባ ‘ጌታ ሆይ፣ እህቴ ሥራውን ሁሉ ለእኔ ጥላ ስትቀመጥ ምንም ግድ አይሰጥህም? እንድታግዘኝ ንገራት እንጂ’ አለችው። ጌታም መልሶ እንዲህ አላት፦ ‘ማርታ፣ ማርታ፣ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፣ ትጠበቢያለሽ። ይሁንና የሚያስፈልገው ጥቂት ወይም አንድ ነገር ብቻ ነው። ማርያም በበኩሏ የተሻለውን ነገር መርጣለች፤ ይህም ከእሷ አይወሰድባትም።’”—ሉቃስ 10:38-42
ማርታ ታታሪ ሠራተኛ እንደነበረች እሙን ነው። ይህ ደግሞ የሌሎችን ከበሬታ እንዳስገኘላት ምንም ጥርጥር የለውም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት አይሁዳውያን ዘንድ የአንዲት ሴት ማንነት የሚለካው የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመሥራት በምታሳየው ትጋትና የቤተሰቧን ፍላጎት ለማሟላት ባላት ችሎታ ላይ ነበር።
በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያን ሴቶችም “በቤት ውስጥ የሚሠሩ” እንዲሆኑ ይበረታቱ ነበር። (ቲቶ 2:5) ከዚህም በተጨማሪ ለሌሎች ሰዎች ስለ እምነታቸው የመናገር መብትና ኃላፊነት ነበረባቸው። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ የሐዋርያት ሥራ 2:18) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረች አንዲት አይሁዳዊት ታከናውናቸው ከነበሩት ‘ብዙ ሥራዎች’ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ኢየሱስ ስለ ማርያም ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?
‘በብዙ ሥራ መጠመድ’፦ አንዲት አይሁዳዊት የቤት እመቤት አብዛኛውን ጊዜ ሥራ የምትጀምረው ገና ወፍ ሳይጮኽ ነው። (ምሳሌ 31:15) ለቤተሰቧ እንደ ገንፎ ያለ ቀለል ያለ ቁርስ ካዘጋጀች በኋላ ወንዶች ልጆቿን ለትምህርት ወደ ምኩራብ ትሸኛቸዋለች። ሴቶች ልጆቿ ደግሞ ከእሷ ጋር በቤት ውስጥ ውለው ወደፊት ጥሩ ሚስት ለመሆን የሚያስችላቸውን ሙያ ይማራሉ።
እናትየውና ሴት ልጆቿ የቀኑን ውሏቸውን የሚጀምሩት የመብራት ዘይት መሙላት (1)፣ ቤት መጥረግ (2) እና ፍየል ማለብ (3) የመሳሰሉ የዕለት ተዕለት ሥራዎችን በማከናወን ነበር። ከዚያም ለዕለቱ የሚያስፈልጋቸውን ዳቦ ይጋግራሉ። ሴቶቹ ልጆች እህሉን ያበጥሩና (4) በድንጋይ ወፍጮ ይፈጩታል (5)። እናትየው ዱቄቱን ወስዳ ውኃና እርሾ ጨምራ ታቦካዋለች። ከዚያም ሊጡን በደንብ አድርጋ ካሸችው (6) በኋላ ኩፍ እስኪል ድረስ ሌላ ሥራ ትሠራለች። በዚህ ጊዜ ሴቶቹ ልጆች የፍየሉን ወተት ካረጉ በኋላ (7) አይብ ያወጣሉ።
ረፈድ ሲል እናትየው ሴቶች ልጆቿን ይዛ ወደ ገበያ ትወጣለች። በቅመማ ቅመም ሽታ በታወደው፣ በእንስሳት ጩኸት እንዲሁም በገዥና በሻጭ መካከል በሚደረገው የዋጋ ድርድር ሞቅ ደመቅ ባለው ገበያ ውስጥ ለዕለቱ የሚያስፈልጓትን ነገሮች ትሸማምታለች (8)። ከምትገዛቸው ነገሮች መካከል አትክልቶችና የደረቁ ዓሣዎች ሊገኙበት ይችላሉ። ይህች እናት ክርስቲያን ከሆነች ደግሞ አጋጣሚውን ተጠቅማ በገበያው ውስጥ ለምታገኛቸው ሰዎች ስለ እምነቷ መናገሯ አይቀርም።—የሐዋርያት ሥራ 17:17
ንቁ የሆነች አንዲት እናት ወደ ገበያ ቦታ ሲሄዱና ሲመለሱ አጋጣሚውን ተጠቅማ ልጆቿ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች አድናቆት እንዲኖራቸው ታስተምራቸዋለች። (ዘዳግም 6:6, 7) ከዚህም በተጨማሪ ዕቃ ረከስ ባለ ዋጋ መግዛት የሚችሉበትን ዘዴ ትነግራቸው ይሆናል።—ምሳሌ 31:14, 18
ሴቶች በየዕለቱ ከሚያከናውኗቸው ነገሮች አንዱ ወደ ውኃ ጉድጓድ መሄድ ነው (9)። እዚያ ሄደው ምናልባትም ውኃ ሊቀዱ ከመጡ ሌሎች ሴቶች ጋር እያወሩ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ውኃ ይቀዳሉ። እናትየውና ሴቶች ልጆቿ ወደ ቤት ከተመለሱ በኋላ ዳቦ መጋገር ይጀምራሉ። መጀመሪያ ሊጡን ይጠፈጥፉና የጋለ ምድጃ ውስጥ ይከቱታል (10)፤ ብዙ ጊዜ ምድጃው የሚገኘው ከቤት ውጭ ነው። በዚህ ጊዜ የዳቦው ሽታ አካባቢውን የሚያውደው ሲሆን እርስ በርስ እየተጨዋወቱ ዳቦው መብሰሉን ይከታተላሉ።
ከዚያም ልብስ ለማጠብ አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ወንዝ ይወርዳሉ (11)። ሴቶቹ መጀመሪያ ላይ ልብሶቹን ከአንዳንድ አትክልቶች በተዘጋጀ የሶድየም ወይም የፖታስየም ካርቦኔት ሳሙና በደንብ አሽተው ያጥቡታል። ከዚያም ልብሱን ካለቀለቁና ከጨመቁ በኋላ
እንዲደርቅ በአካባቢው በሚገኝ ቁጥቋጦ ወይም ድንጋይ ላይ ያሰጡታል።እናትየውና ሴቶች ልጆቿ የታጠቡትን ልብሶች ይዘው ወደ ቤት ከተመለሱ በኋላ ልብሶቹን ወደየቦታቸው ከማስገባታቸው በፊት በቤቱ ጣሪያ ላይ ወጥተው የተቀደዱ ልብሶች ካሉ ይሰፋሉ (12)። በኋላም ሴቶቹ ጥልፍና ሽመና ይማሩ (13) ይሆናል። ብዙም ሳይቆይ ሴቶቹ እራት መሥራት ይጀምራሉ (14)። በአካባቢው እንግዳ የመቀበል ባሕል ስላለ ቤተሰቡ ለእራት ያዘጋጀውን ዳቦ፣ አትክልት፣ አይብ፣ የደረቀ ዓሣና የሚጠጣ ውኃ ከእንግዶች ጋር ተካፍሎ ይመገባል።
ምሽት ላይ ልጆቹ ወደ መኝታ ከመሄዳቸው በፊት ምናልባትም ወድቀው ጉልበታቸው ከቆሳሰለ ማስታገሻ ዘይት ይቀባሉ። ከዚያም ወላጆች ጭልጭል በሚለው መብራት ታግዘው ለልጆቻቸው ከቅዱሳን መጻሕፍት አንድ ታሪክ ይተርኩላቸው እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ይጸልዩ ይሆናል። ትንሿ ቤት ጸጥ ረጭ ስትል ባልየው ለሚስቱ “ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቍ እጅግ ይበልጣል” የሚለውን የታወቀ አባባል የሚጠቅስበት በቂ ምክንያት አለው።—ምሳሌ 31:10 የ1954 ትርጉም
“የተሻለውን ነገር” መምረጥ፦ ከላይ እንደተመለከትነው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ትጉ ሴቶች “በብዙ ሥራ” ተጠምደው ይውሉ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 10:40) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ሴቶች በተለይ እናቶች ሕይወታቸው በሥራ የተጠመደ ነው። አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዳቀለሉ እሙን ነው። ይሁንና በርካታ እናቶች ቤተሰባቸውን ከመንከባከብ ባሻገር ከቤት ውጭ እንዲሠሩ ሁኔታዎች ያስገድዷቸዋል።
በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያን ሴቶች ተደራራቢ ኃላፊነቶች ቢኖሩባቸውም ከላይ የተጠቀሰችውን የማርያምን ምሳሌ ይከተላሉ። ከምንም ነገር በላይ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጣሉ። (ማቴዎስ 5:3) ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያበረታቱት ቤተሰባቸውን በሚገባ ይንከባከባሉ። (ምሳሌ 31:11-31) በተጨማሪም ኢየሱስ ለማርታ የሰጣትን ምክር ይከተላሉ። ማርታ መንፈሳዊ ሴት እንደመሆኗ መጠን ኢየሱስ የነገራትን ማሳሰቢያ በተግባር ላይ አውላ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ክርስቲያን ሴቶች በቤት ውስጥ ያለባቸው ኃላፊነት ስለ አምላክ መማር (15) ወይም እምነታቸውን ለሌሎች ማካፈል የሚችሉበትን ጊዜ እንዳይሻማባቸው ይጠነቀቃሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25) በዚህ መንገድ “የተሻለውን ነገር” ይመርጣሉ። (ሉቃስ 10:42) ይህ ደግሞ በአምላክና በክርስቶስ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው ዘንድ ከበሬታ ያስገኝላቸዋል።—ምሳሌ 18:22