በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳምንታዊውን ሰንበት መጠበቅ ይኖርብሃል?

ሳምንታዊውን ሰንበት መጠበቅ ይኖርብሃል?

ሳምንታዊውን ሰንበት መጠበቅ ይኖርብሃል?

በ1980ዎቹ መገባደጃ አካባቢ የፊጂ ዋና ከተማ በሆነችው በሱቫ ጥቂት የሜቶዲስት እምነት ተከታዮች የከተማዋን መንገድ ዘግተው ነበር። ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ የሚለብሱትን ልብስ የለበሱ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች 70 የሚሆኑ መንገዶችን ዘግተው ነበር። እነዚህ ሰዎች ለዕለት የሚያስፈልጉ ነገሮችን የሚያጓጉዙ መኪናዎችን እንዳያልፉ እንዲሁም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ በረራዎች እንዳይከናወኑ አግደው ነበር። ይህን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ምን ነበር? አገሪቱ ልክ እንደ ቀድሞ የሰንበትን ሕግ በጥብቅ እንድትከተል ለማስገደድ ነበር።

በእስራኤል ከ2001 ወዲህ የተገነቡ አዳዲስ ፎቆች በእያንዳንዱ ፎቅ ላይ ማንም ሳይነካው በራሱ የሚቆም ቢያንስ አንድ ሊፍት ተገጥሞላቸዋል። የዚህ ሊፍት ዓላማ ምንድን ነው? ከዓርብ ምሽት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ምሽት ድረስ ሰንበትን የሚያከብሩ ቀናተኛ አይሁዳውያን በሊፍት ሲጠቀሙ የሊፍቱን ቁልፍ እንደመጫን ያለ “ሥራ” እንዳይሠሩ ነው።

በደቡብ ፓስፊክ በምትገኘው ቶንጋ በተባለች ግዛት እሁድ ዕለት ማንኛውንም ሥራ መሥራት የተከለከለ ነው። በዚያ ቀን በአገሪቱ ውስጥ አውሮፕላንም ሆነ መርከብ እንዲንቀሳቀስ አይፈቀድም። በዚያን ቀን የሚደረግ ማንኛውም ውል ተቀባይነት አይኖረውም። የቶንጋ ሕገ መንግሥት እያንዳንዱ ሰው እምነቱ ምንም ይሁን ምን እሁድን “ቅዱስ አድርጎ” እንዲመለከት ያዛል። ለምን? ሰንበት በመላው አገሪቱ እንዲከበር ለማድረግ ነው።

ከእነዚህ ምሳሌዎች መመልከት እንደሚቻለው ብዙ ሰዎች አምላክ በየሳምንቱ ሰንበት እንዲያከብሩ እንደሚፈልግባቸው ይሰማቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ሰንበትን መጠበቅ ከዘላለማዊ መዳን ጋር የተያያዘ እንደሆነ ስለሚያምኑ ይህን ማድረግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ አምላክ ከሰጣቸው ትእዛዛት ሁሉ የላቀ ስፍራ ያለው የሰንበት ሕግ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ሰንበት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በየሳምንቱ ሰንበትን እንዲጠብቁ ያዛል?

ሰንበት ምንድን ነው?

“ሰንበት” የሚለው የአማርኛ ቃል “ማረፍ፣ ማቆም፣ መተው” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ነው። የዘፍጥረት ዘገባ፣ ይሖዋ አምላክ በሰባተኛው ቀን ከፍጥረት ሥራው እንዳረፈ ቢናገርም ከሙሴ ዘመን በፊት የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች 24 ሰዓት የሚቆየውን የእረፍት ቀን ወይም ሰንበት እንዲጠብቁ አልታዘዙም። (ዘፍጥረት 2:2) በ1513 ዓ.ዓ. እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ይሖዋ በምድረ በዳ ሳሉ በተአምር መና ሰጣቸው። አምላክ ይህን መና መሰብሰብ የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ “ስድስት ቀን ትሰበስቡታላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ዕለት ግን ምንም ነገር አይኖርም” የሚል መመሪያ ሰጣቸው። (ዘፀአት 16:26) ከዚያም ‘ሕዝቡ በሰባተኛው ቀን’ ማለትም ዓርብ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ አንስቶ እስከ ቅዳሜ ምሽት ድረስ ‘እንዳረፉ’ የሚናገር ዘገባ እናገኛለን።—ዘፀአት 16:30

እነዚህ መመሪያዎች ከተሰጡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይሖዋ ለሙሴ በሰጠው አሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ የሰንበት ሕግ ተካትቶ ነበር። (ዘፀአት 19:1) የአሥርቱ ትእዛዛት አራተኛ ሕግ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብር። ስድስት ቀን ትሠራለህ፤ ሥራህንም ሁሉ አከናውን። ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው።” (ዘፀአት 20:8-10) በመሆኑም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰንበትን መጠበቅ የእስራኤላውያን ሕይወት ዓቢይ ክፍል ሆነ።—ዘዳግም 5:12

ኢየሱስ ሳምንታዊውን ሰንበት አክብሮ ነበር?

አዎን፣ ኢየሱስ ሰንበትን አክብሮ ነበር። ኢየሱስን በተመለከተ የሚከተለው ተገልጾልናል፦ “ዘመኑ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሲደርስ አምላክ ከሴት የተወለደውንና በሕግ ሥር የሆነውን ልጁን ላከ።” (ገላትያ 4:4) ኢየሱስ እስራኤላዊ ሆኖ የተወለደ ሲሆን እስራኤላውያን ደግሞ በሕጉ ሥር ነበሩ፤ ከሕጎቹ መካከል የሰንበት ሕግ ይገኝበታል። ኢየሱስ እስኪሞት ድረስ የሕጉ ቃል ኪዳን አልተወገደም ነበር። (ቆላስይስ 2:13, 14) በታሪክ ውስጥ እነዚህ ሁኔታዎች የተከናወኑበትን ጊዜ ማወቃችን አምላክ ስለ ሰንበት ያለውን አመለካከት ለመረዳት ያስችለናል።— በገጽ 15 ላይ የሚገኘውን ሠንጠረዥ ተመልከት።

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ “ሕግን ወይም የነቢያትን ቃል ልደመስስ እንደመጣሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ልፈጽም እንጂ ልደመስስ አልመጣሁም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:17) ኢየሱስ “ልፈጽም” ሲል ምን ማለቱ ነበር? ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ መሐንዲስ የገባውን ውል የሚፈጽመው ውሉን በማፍረስ ሳይሆን ሕንፃውን አጠናቆ በማስረከብ ነው። ይሁን እንጂ ሥራው ባለቤቱ በሚፈልገው መንገድ አንድ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ውሉ ስለሚፈጸም ከዚያ በኋላ መሐንዲሱ ምንም አይጠበቅበትም። በተመሳሳይም ኢየሱስ ሕጉን አልደመሰሰም ወይም አላፈረሰም፤ ከዚህ ይልቅ ሕጉን ሙሉ በሙሉ በመጠበቅ ፈጽሞታል። “ውሉ” ወይም ሕጉ ሙሉ በሙሉ ስለተፈጸመ ከዚያ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች መጠበቅ አያስፈልጋቸውም።

ክርስቲያኖች ሊያከብሩት ይገባል?

ክርስቶስ ሕጉን ስለፈጸመ ክርስቲያኖች ሳምንታዊውን ሰንበት ማክበር ይጠበቅባቸዋል? ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቷል፦ “ስለዚህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ የወር መባቻንና ሰንበትን በማክበር ረገድ ማንም ሰው አይፍረድባችሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ለሚመጡት ነገሮች ጥላ ናቸው፤ እውነተኛው ነገር ግን የክርስቶስ ነው።”—ቆላስይስ 2:16, 17

በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ አምላክ ከአገልጋዮቹ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ለውጥ እንዳደረገ ይጠቁማል። ለውጥ ማድረግ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ክርስቲያኖች በአዲስ ሕግ ሥር ይኸውም ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ናቸው። (ገላትያ 6:2) በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን ተሰጥቶ የነበረው የሕጉ ቃል ኪዳን በኢየሱስ ሞት አማካኝነት ፍጻሜውን ሲያገኝ ከዚያ በኋላ መሥራቱን አቁሟል። (ሮም 10:4፤ ኤፌሶን 2:15) ታዲያ ሰንበትን ስለ መጠበቅ የሚናገረው ሕግስ ፍጻሜውን አግኝቷል? አዎን። ጳውሎስ “ከሕጉ ነፃ ወጥተናል” ብሎ ከተናገረ በኋላ ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል አንዱን ጠቅሷል። (ሮም 7:6, 7) በመሆኑም ፍጻሜያቸውን ካገኙት ሕጎች መካከል የሰንበትን ሕግ የሚያካትተው አሥርቱ ትእዛዛት ይገኝበታል። ስለሆነም የአምላክ አገልጋዮች ሳምንታዊውን ሰንበት ማክበር አይጠበቅባቸውም።

ከአይሁድ እምነት ወደ ክርስትና የተደረገውን ለውጥ በሚከተለው ምሳሌ ማስረዳት ይቻላል፦ አንድ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ለወጠ እንበል። አዲሱ ሕገ መንግሥት ከጸና በኋላ የዚያ አገር ዜጎች የቀድሞውን ሕግ እንዲታዘዙ አይጠበቅባቸውም። በአዲሱ ሕገ መንግሥት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሕጎች በቀድሞ ውስጥ የነበሩ ቢሆኑም በአዲሱ ሕገ መንግሥት ውስጥ አዳዲስ ሕጎችም ተካተው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም አንድ ሰው የአገሪቱን ሕግ ለማወቅ አዲሱን ሕገ መንግሥት በጥንቃቄ ማጥናት ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ጥሩ ዜጋ አዲሱ ሕገ መንግሥት የሚጸናው ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ ማወቅ እንደሚፈልግ ጥርጥር የለውም።

በተመሳሳይም ይሖዋ አምላክ ለእስራኤል ሕዝብ 10 ዋና ዋና ትእዛዛትን ጨምሮ ከ600 በላይ ሕጎችን ሰጥቶ ነበር። ከእነዚህ ሕጎች መካከል ከሥነ ምግባር፣ ከመሥዋዕት፣ ከጤና እንዲሁም ሰንበትን ከመጠበቅ ጋር በተያያዙ የተሰጡ ደንቦች ይገኙበታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮቹ አዲስ “ሕዝብ” ሆነው እንደሚደራጁ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 21:43) ከ33 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ ሕዝብ በሁለት መሠረታዊ ሕጎች ይኸውም ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር በማሳየት ላይ የተመሠረተ አዲስ “ሕገ መንግሥት” ተሰጥቶታል። (ማቴዎስ 22:36-40) ‘የክርስቶስ ሕግ’ ለእስራኤላውያን ከተሰጧቸው ሕጎች ጋር የሚመሳሰሉ መመሪያዎችን የሚጨምር ቢሆንም አንዳንዶቹ ሕጎች አዳዲስ ሌሎቹ ደግሞ ከዚያ በኋላ የማይሠሩ መሆናቸው ሊያስደንቀን አይገባም። በአሁኑ ጊዜ በክርስቲያኖች ላይ ከማይሠሩት ሕጎች መካከል ሳምንታዊውን የሰንበት ሕግ ማክበር ይገኝበታል።

አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ለውጧል?

የሙሴ ሕግ በክርስቶስ ሕግ መተካቱ አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች እንደለወጠ ያሳያል? በፍጹም። ልክ አንድ ወላጅ የልጆቹን ዕድሜና ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ ለእነሱ የሚያወጣውን ደንብ እንደሚለዋውጥ ሁሉ ይሖዋም ሕዝቡ እንዲጠብቃቸው በሚፈልጋቸው ሕጎች ላይ ማስተካከያ አድርጓል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሁኔታ እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “እምነት ከመምጣቱ በፊት፣ መገለጡ የማይቀረውን እምነት እየተጠባበቅን በሕግ ጥበቃ ሥር አንድ ላይ እስረኞች ሆነን ቆይተናል። በመሆኑም በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ተብለን መጠራት እንችል ዘንድ ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚታችን ሆኗል። አሁን ግን ያ እምነት ስለመጣ በሞግዚት ሥር መሆናችን አብቅቷል።”—ገላትያ 3:23-25

ጳውሎስ ሁኔታውን ለማስረዳት የተጠቀመበት ምሳሌ ከሰንበት ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? ይህን ለማስረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ ተማሪ በትምህርት ዓለም እያለ በየሳምንቱ በአንድ በተወሰነ ቀን እንደ እንጨት ሥራ የመሳሰሉ የትምህርት ዓይነቶችን መማር ይጠበቅበት ይሆናል። ይሁንና ተማሪው ወደ ሥራው ዓለም ሲገባ የተማረውን ሙያ በሳምንቱ ውስጥ በአንድ የተወሰነ ቀን ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ተግባራዊ ማድረግ ይፈለግበት ይሆናል። በተመሳሳይም እስራኤላውያን በሕጉ ሥር በነበሩበት ጊዜ በየሳምንቱ አንዱን ቀን ለእረፍትና ለአምልኮ እንዲመድቡ ይጠበቅባቸው ነበር። በሌላ በኩል ክርስቲያኖች በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ አምላክን እንዲያመልኩ ይጠበቅባቸዋል።

ታዲያ በየሳምንቱ አንዱን ቀን ለእረፍትና ለአምልኮ መመደብ ስህተት ነው? አይደለም። የአምላክ ቃል እንዲህ ያለው ውሳኔ ለእያንዳንዱ ሰው የተተወ እንደሆነ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “አንድ ሰው አንዱን ቀን ከሌላው የተሻለ ቅዱስ አድርጎ ይቈጥራል፤ ሌላው ደግሞ ቀኖች ሁሉ እኩል እንደ ሆኑ ያስባል። እያንዳንዱ የራሱን ውሳኔ ልብ ብሎ ይወስን።” (ሮም 14:5 አ.መ.ት) አንዳንዶች በሳምንቱ ውስጥ አንዱን ቀን ይበልጥ ቅዱስ አድርገው ይመለከቱት ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አምላክ ክርስቲያኖች ሳምንታዊውን ሰንበት እንዲያከብሩ እንደማይጠብቅባቸው በግልጽ ይናገራል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ስድስት ቀን ትሰበስቡታላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ዕለት ግን ምንም ነገር አይኖርም።”—ዘፀአት 16:26

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ተብለን መጠራት እንችል ዘንድ ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚታችን ሆኗል። አሁን ግን ያ እምነት ስለመጣ በሞግዚት ሥር መሆናችን አብቅቷል።”—ገላትያ 3:24, 25

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕላዊ መግለጫ]

ዓለም አቀፍ ዕለተ መስመር እና ሰንበት

ዓለም አቀፍ ዕለተ መስመር፣ ሳምንታዊው ሰንበት በሁሉም ቦታ በተመሳሳይ ቀን መከበር አለበት የሚሉ ሰዎች ይህን እንዳያደርጉ ተፈታታኝ አድርጎባቸዋል። ዓለም አቀፍ ዕለተ መስመር፣ በ180 ዲግሪ ሜሪዲየን ላይ (ከሰሜን ዋልታ ወደ ደቡብ ዋልታ የሚሰመር የሐሳብ መስመር) አብዛኛውን የፓስፊክ ውቅያኖስ አቋርጦ የሚያልፍ የሐሳብ መስመር ነው። ከዚህ መስመር በስተ ምዕራብ የሚገኙ አገሮች በስተ ምሥራቅ ከሚገኙት አገሮች በአንድ ቀን ይቀድማሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ በፊጂና በቶንጋ ዕለቱ እሁድ ሲሆን በሳሞኣና በኒዩኤ ደግሞ ቅዳሜ ይሆናል። በመሆኑም አንድ ሰው በፊጂ ሆኖ ቅዳሜ ዕለት ሰንበትን ሲያከብር 1,145 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለችው በሳሞኣ የሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቹ በዚህ ዕለት አያከብሩም፤ ምክንያቱም በዚህ ዕለት እነሱ ጋር ዓርብ ስለሆነ ይሠራሉ።

በቶንጋ የሚገኙ የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስቶች በ850 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በሳሞኣ ከሚኖሩ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ሰንበትን በተመሳሳይ ቀን ለማክበር ሲሉ የሚያከብሩት እሁድ ዕለት ነው። ይሁንና በዚሁ ጊዜ በ800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በፊጂ ዕለቱ እሁድ በመሆኑ በዚያ የሚገኙ አድቬንቲስቶች አያርፉም፤ ምክንያቱም እነሱ ሰንበትን የሚያከብሩት ቅዳሜ ነው።

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

\

\

\

\ ሳሞኣ

\

— ― ― ― ― ― ― ―

ፊጂ \

እሁድ \ ቅዳሜ

\

\

ቶንጋ \

\

\

\

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ግራፍ]

 (መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ስለ ሰንበት ሊታወቁ የሚገባቸው እውነታዎች፦

ሳምንታዊው ሰንበት መከበር እንዳለበት የሚናገሩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ቢኖሩም በጥቅሶቹ ላይ ያለው ሐሳብ የተነገረበትን ጊዜ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል።

በ4026 ዓ.ዓ. ከሙሴ ዘመን በፊት

አዳም ተፈጠረ ሰንበትን ስለ መጠበቅ የሚናገረው ሕግ

ከሙሴም ሆነ ከእስራኤላውያን ዘመን በፊት

አልተሰጠም።—ዘዳግም 5:1-3, 12-14

በ1513 ዓ.ዓ. አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ

ለእስራኤላውያን ሕግ ተሰጣቸው ስለ ሰንበት የሚናገረው ሕግ ለሌሎች

ሕዝቦች አልተሰጠም። (መዝሙር 147:19, 20)

ሕጉ የተሰጠው በይሖዋና በእስራኤል ልጆች መካከል

“ምልክት” እንዲሆን ነበር።—ዘፀአት 31:16, 17

ሳምንታዊው የሰንበት ሕግ ለእስራኤላውያን

ከተሰጧቸው በርካታ የሰንበት ሕጎች መካከል

አንዱ ብቻ ነበር።—ዘሌዋውያን 16:29-31

23:4-8፤ 25:4, 11፤ ዘኍልቍ 28:26

በ33 ዓ.ም. የክርስቶስ ሕግ

ለእስራኤላውያን የተሰጣቸው ሕግ በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች

መሥራቱ አበቃ በ49 ዓ.ም. አምላክ ከክርስቲያኖች ምን እንደሚጠብቅ

በወሰኑ ጊዜ ሳምንታዊውን ሰንበት ስለ ማክበር

የጠቀሱት ነገር አልነበረም።—የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች

የተወሰኑ ቀናትን ልዩ እንደሆኑ አድርገው

ማክበራቸው አሳስቦት ነበር።—ገላትያ 4:9-11

2010 ዓ.ም.

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሜቶዲስት እምነት ተከታዮች ፊጂ እንደ ቀድሞው ሰንበትን እንድታከብር ለማስገደድ የከተማዋን መንገዶች ዘግተው እንደነበር ጋዜጦች ዘግበዋል

[ምንጭ]

Courtesy of the Fiji Times