በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?

መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?

መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?

ኢየሱስ በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሎ ጠይቋቸው ነበር፦ “ከመካከላችሁ ልጁ ዓሣ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ የሚሰጥ አባት ይኖራል? ወይስ እንቁላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋል?” (ሉቃስ 11:11, 12) በገሊላ የሚኖሩ ልጆች እንቁላልና ዓሣ መብላት ስለሚወዱ ምን መጠየቅ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር።

አንድ የራበው ልጅ ምግብ ለማግኘት አጥብቆ እንደሚጠይቅ ሁሉ እኛም መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት ደጋግመን መጠየቅ አለብን። (ሉቃስ 11:9, 13) መንፈስ ቅዱስ ምን እንደሆነ ማወቃችን በሕይወታችን ውስጥ የሚጫወተውን ቁልፍ ሚና እንድንረዳ ያስችለናል። ስለሆነም በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ የሚያስተምረውን ትምህርት እንመልከት።

‘የልዑሉ ኃይል’

መንፈስ ቅዱስ፣ አምላክ ፈቃዱን ለማስፈጸም የሚጠቀምበት ኃይል እንደሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ይናገራሉ። መልአኩ ገብርኤል፣ ማርያም ድንግል ብትሆንም እንኳ ልጅ እንደምትወልድ በነገራት ጊዜ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስ፣ የአምላክ ልጅ ይባላል” ብሏት ነበር። (ሉቃስ 1:35) ገብርኤል ከተናገረው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው በመንፈስ ቅዱስና ‘በልዑሉ ኃይል’ መካከል ግንኙነት አለ።

ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ይገኛል። ነቢዩ ሚክያስ “ኃይልን፣ በእግዚአብሔር መንፈስ . . . ተሞልቻለሁ” በማለት ተናግሯል። (ሚክያስ 3:8) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ስለ መንፈስ ቅዱስ ኃይል’ ተናግሯል።—ሮም 15:13, 19

ታዲያ ከላይ ካየናቸው ጥቅሶች ሐሳብ በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? በመንፈስ ቅዱስና በአምላክ ኃይል መካከል የጠበቀ ግንኙነት አለ። ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጠው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። በቀላል አነጋገር መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል ነው። እንዴት ያለ አስደናቂ ኃይል ነው! መላውን ጽንፈ ዓለም ለመፍጠር ምን ያህል ኃይል እንዳስፈለገ መገመት ከአቅማችን በላይ ነው። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ ላይ እንድናሰላስል አበረታቶናል፦ “ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።”—ኢሳይያስ 40:26

በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሥርዓታማና የተደራጀ የሆነው ጽንፈ ዓለም የተፈጠረው ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ‘ታላቅ ኃይል’ እንደሆነ ይነግረናል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል እጅግ ታላቅ ሲሆን ሕይወታችን የተመካውም በእሱ ላይ ነው።—“በሥራ ላይ ያለው ቅዱስ መንፈስ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ይሖዋ ጽንፈ ዓለሙን ሲፈጥር እንደታየው መንፈስ ቅዱስን በከፍተኛ መጠን ሊጠቀምበት ይችላል። የሰው ልጆችን ለመርዳትም መንፈስ ቅዱስን ይጠቀማል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹን ለመርዳት ኃይል የሰጣቸው እንዴት እንደሆነ የሚናገሩ በርካታ ምሳሌዎችን ይዟል።

“የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው”

ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ያከናወነው አገልግሎት አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለአገልጋዮቹ ኃይል የሚሰጠው በምን መንገድ እንደሆነ ፍንጭ ይሰጠናል። ኢየሱስ፣ ለናዝሬት ሰዎች “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 4:18) ኢየሱስ “በመንፈስ ኃይል” ምን ነገሮችን አከናውኗል? (ሉቃስ 4:14) የተለያየ የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች ፈውሷል፣ በማዕበል የሚናወጠውን ባሕር ጸጥ አሰኝቷል፣ በጥቂት ዳቦና ዓሣ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መግቧል፤ ሌላው ቀርቶ የሞቱ ሰዎችን አስነስቷል። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ “አምላክ . . . በመካከላችሁ ተአምራትን፣ ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በመፈጸም ለእናንተ በይፋ የገለጠው [ሰው]” በማለት ስለ ኢየሱስ ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 2:22

እርግጥ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ በአሁኑ ወቅት እንዲህ ያሉ ተአምራትን እንድንፈጽም አያደርገንም። ያም ሆኖ አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን እንድናደርግ ይረዳናል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዳረጋገጠላቸው ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ለአምላኪዎቹ ለመስጠት ፈቃደኛ ነው። (ሉቃስ 11:13) ሐዋርያው ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ” ለማለት የቻለው ለዚህ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:13) አንተስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንዲህ ያለ ብርታት ማግኘት የምትችል ይመስልሃል? የሚቀጥለው ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ያብራራል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መንፈስ ቅዱስ አካል አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስን ከውኃ ጋር ያመሳስለዋል። አምላክ ወደፊት በረከት እንደሚሰጣቸው ለሕዝቦቹ ቃል ሲገባ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ።”—ኢሳይያስ 44:3 የ1954 ትርጉም

አምላክ በአገልጋዮቹ ላይ መንፈሱን ሲያፈስ ‘መንፈስ ቅዱስ ይሞላቸዋል’ ወይም ‘በመንፈስ ቅዱስ ይሞላሉ።’ ኢየሱስ፣ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ጴጥሮስ፣ ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት ተሰብስበው የነበሩት ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ እንደሞላባቸው ወይም በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ሉቃስ 1:15፤ 4:1፤ የሐዋርያት ሥራ 4:8፤ 9:17፤ 11:22, 24፤ 13:9

እስቲ ይህን አስብ፦ አካል ያለው ነገር በተለያዩ ሰዎች ላይ ‘መፍሰስ’ ይችላል? መንፈስ ቅዱስ አካል ቢሆን ኖሮ በአንድነት የተሰበሰቡ ሰዎችን ‘መሙላት’ ይችል ነበር? እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በጥበብ፣ በማስተዋል ሌላው ቀርቶ በትክክለኛ እውቀት እንደተሞሉ የሚናገር ቢሆንም አካል ያለው አንድ ነገር አካል ባለው ሌላ ነገር እንደተሞላ የተናገረበትን ቦታ ፈጽሞ አናገኝም።—ዘፀአት 28:3፤ 1 ነገሥት 7:14፤ ሉቃስ 2:40፤ ቆላስይስ 1:9

“መንፈስ” ተብሎ የተተረጎመው ፕኒውማ የሚለው የግሪክኛ ቃል ለሰው ዓይን የማይታይ አንድን ኃይል ሊያመለክትም ይችላል። በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ እንደገለጸው ከሆነ ፕኒውማ የሚለው ቃል “ቀጥተኛ ትርጉሙ ነፋስ ሲሆን . . . በተጨማሪም ትንፋሽን ሊያመለክት ይችላል፤ በመሆኑም እንደ ነፋስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ የማይታይና የማይዳሰስ እንዲሁም ኃይል ያለው ነው።”

ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መንፈስ ቅዱስ አካል የለውም። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.19 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ “አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?” የሚለውን ከገጽ 201 እስከ 204 ላይ የሚገኘውን ክፍል ተመልከት። መጽሐፉ የተዘጋጀው በይሖዋ ምሥክሮች ነው።

[የሥዕል ምንጭ]

Photodisc/SuperStock