በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጾም ወደ አምላክ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳሃል?

ጾም ወደ አምላክ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳሃል?

ጾም​—ወደ አምላክ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳሃል?

‘ጾም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንድታሰላስልና በሕይወትህ ውስጥ ትልቁን ቦታ መያዝ ያለበት ቁሳዊ ነገር አለመሆኑን እንድታስታውስ ይረዳሃል።’—የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ የሆነች ሴት

‘ጾም ከአምላክ ጋር መንፈሳዊ ግንኙነት ለመፍጠር ይረዳሃል።’—የአይሁድ ረቢ

‘በሃይማኖቴ መጾም ግዴታ ነው፤ ጾም ለአምላክ ፍቅር እንዳለኝና እሱን ማመስገን እንደምፈልግ ለመግለጽ የሚያስችለኝ ዋነኛ መንገድ ነው። የምጾመው አምላክን ስለምወደው ነው።’—የባሃዪ እምነት ተከታይ የሆነች ሴት

በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ውስጥ ጾም የተለመደ ተግባር ነው። ቡድሂዝምን፣ ሂንዱይዝምን፣ እስልምናን፣ ጃይኒዝምንና የአይሁድ እምነትን ጨምሮ የበርካታ ሃይማኖቶች ተከታዮች ይጾማሉ። ብዙ ሰዎች የተወሰነ ጊዜ ምግብ ሳይበሉ መቆየት ይበልጥ ወደ አምላክ ለመቅረብ እንደሚረዳ ይሰማቸዋል።

አንተስ ምን ይመስልሃል? መጾም ይኖርብሃል? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ጾምበጥንት ዘመን

በጥንት ዘመን የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ይጾሙ የነበረ ሲሆን ለመጾም የተነሳሱባቸው ምክንያቶችም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል። አንዳንዶች በጥልቅ ማዘናቸውን ወይም ከኃጢአታቸው ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት (1 ሳሙኤል 7:4-6)፣ የአምላክን ሞገስ ወይም መመሪያ ለማግኘት (መሳፍንት 20:26-28፤ ሉቃስ 2:36, 37)፣ አሊያም ትኩረታቸውን አሰባስበው ለማሰላሰል ሲሉ ይጾሙ ነበር።—ማቴዎስ 4:1, 2

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጾማቸው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘ ሰዎች እንደነበሩ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ሳኦል ወደ ሙታን ሳቢ ከመሄዱ በፊት ጾሞ ነበር። (ዘሌዋውያን 20:6፤ 1 ሳሙኤል 28:20) እንዲሁም እንደ ኤልዛቤልና ሐዋርያው ጳውሎስን ለመግደል እንዳሴሩት አክራሪ ሃይማኖተኞች ያሉ ክፉ ሰዎች ጾም አውጀው ነበር። (1 ነገሥት 21:7-12፤ የሐዋርያት ሥራ 23:12-14) ፈሪሳውያንም አዘውትረው በመጾም የታወቁ ነበሩ። (ማርቆስ 2:18) ያም ሆኖ ኢየሱስ ድርጊታቸውን ያወገዘው ከመሆኑም ሌላ የአምላክን ሞገስ አላገኙም። (ማቴዎስ 6:16፤ ሉቃስ 18:12) በተመሳሳይም አንዳንድ እስራኤላውያን ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ስለነበረና ለመጾም የተነሳሱበት ምክንያት ትክክል ስላልነበረ ይሖዋ ጾማቸውን አልተቀበለውም።—ኤርምያስ 14:12

ከእነዚህ ምሳሌዎች ማየት እንደሚቻለው አንድ ሰው መጾሙ በራሱ አምላክን ያስደስተዋል ማለት አይደለም። ሆኖም በርካታ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች የጾሙበት ጊዜ የነበረ ሲሆን አምላክ ጾማቸውን ተቀብሎታል። ታዲያ ክርስቲያኖች መጾም ይገባቸዋል?

ክርስቲያኖች የመጾም ግዴታ አለባቸው?

የሙሴ ሕግ፣ አይሁዳውያን በዓመት አንድ ጊዜ በስርየት ቀን ‘ሰውነታቸውን እንዲያደክሙ’ ይኸውም እንዲጾሙ ያዝዛል። (ዘሌዋውያን 16:29-31፤ መዝሙር 35:13) ይሖዋ ለሕዝቡ የሰጠው ጾም ይህ ብቻ ነው። * በሙሴ ሕግ ሥር የነበሩ አይሁዳውያን ይህንን መመሪያ መታዘዝ ይጠበቅባቸው ነበር። ክርስቲያኖች ግን የሙሴን ሕግ እንዲታዘዙ አይጠበቅባቸውም።—ሮም 10:4፤ ቆላስይስ 2:14

ኢየሱስ ሕጉ በሚያዘው መሠረት ይጾም የነበረ ቢሆንም የሚታወቀው በጿሚነቱ አይደለም። ደቀ መዛሙርቱ መጾም ከፈለጉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ቢናገርም እንዲጾሙ አላዘዛቸውም። (ማቴዎስ 6:16-18፤ 9:14) ታዲያ ኢየሱስ እሱ ከሞተ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንደሚጾሙ የተናገረው ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 9:15) ኢየሱስ ይህን ሲል ትእዛዝ መስጠቱ ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱ የእሱ መሞት በጣም ስለሚያሳዝናቸው የምግብ ፍላጎታቸው እንደሚጠፋ መናገሩ ነበር።

ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች የሚገልጹ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አንድ ሰው በቅን ልብ ተነሳስቶ ለመጾም ከወሰነ ጾሙ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 13:2, 3፤ 14:23) * እስካሁን ካየነው አንጻር ክርስቲያኖች የመጾም ግዴታ የለባቸውም። ይሁንና አንድ ሰው ለመጾም ከወሰነ ሊጠነቀቅባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ።

ጥንቃቄ የሚያሻቸው ነገሮች

ከጾም ጋር በተያያዘ ሊወገድ የሚገባው አንደኛው ነገር ራስን ማመጻደቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አጉል ትሕትና” ከማሳየት እንድንቆጠብ ያስጠነቅቃል። (ቆላስይስ 2:20-23) አዘውትሮ በመጸለዩ ከሌሎች እንደሚሻል ስለተሰማው አንድ ትዕቢተኛ ፈሪሳዊ የሚናገረው የኢየሱስ ምሳሌ፣ አምላክ እንዲህ ዓይነቱን ዝንባሌ እንደማይቀበለው በግልጽ ያሳያል።—ሉቃስ 18:9-14

አንተም እንደምትጾም ለሰዎች ማሳወቅህም ሆነ ሌላ ሰው እንድትጾም ስለነገረህ መጾምህ ስህተት ነው። ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 6:16-18 ላይ እንደገለጸው ጾም በአንተና በአምላክ መካከል ያለ የግል ጉዳይ በመሆኑ እንደምትጾም ለሌሎች መናገር የለብህም።

አንድ ሰው መጾሙ ለሠራው ኃጢአት ማካካሻ እንደሚሆን ፈጽሞ ሊያስብ አይገባም። ጾም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ የአምላክን ትእዛዛት መፈጸም ያስፈልጋል። (ኢሳይያስ 58:3-7) የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኘው ከልብ ንስሐ መግባት እንጂ መጾም ብቻ አይደለም። (ኢዩኤል 2:12, 13) መጽሐፍ ቅዱስ ጎላ አድርጎ እንደሚገልጸው ለኃጢአታችን ይቅርታ የምናገኘው ይሖዋ በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት ባሳየን ጸጋ ነው። ጾምን ጨምሮ ማንኛውም ሥራ ለኃጢአታችን ይቅርታ የሚገባን ሰዎች እንድንሆን ሊያደርገን አይችልም።—ሮም 3:24, 27, 28፤ ገላትያ 2:16፤ ኤፌሶን 2:8, 9

በ⁠ኢሳይያስ 58:3 ላይ ደግሞ ብዙዎች የሚፈጽሙት ሌላ ስህተት ተገልጿል። እስራኤላውያን በመጾማቸው ለአምላክ ውለታ የዋሉለት ይመስል፣ ይሖዋ አንድ ነገር ሊያደርግላቸው እንደሚገባ የተሰማቸው መሆኑን የሚጠቁም ነገር ተናግረዋል። “አንተ ካልተቀበልኸው፣ ስለ ምን ብለን ጾምን? አንተ ከጕዳይ ካልቈጠርኸው፣ ስለ ምን ራሳችንን አዋረድን?” ብለው ነበር። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ ሰዎችም ስለሚጾሙ አምላክ አንድ ነገር እንዲያደርግላቸው መጠበቅ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለውን አክብሮት የጎደለውና ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚጋጭ ዝንባሌ እንዳናዳብር እንጠንቀቅ!

ሌሎች ደግሞ በጾም፣ ራሳቸውን በመግረፍና በመሳሰሉት መንገዶች ሰውነታቸውን በማጎሳቆላቸው የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። የአምላክ ቃል ‘ሰውነትን መጨቆን’ መጥፎ ምኞቶችን ‘በማሸነፍ ረገድ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው’ በመግለጽ እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት ያወግዛል።—ቆላስይስ 2:20-23

ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ያስፈልጋል

መጾም ግዴታ አይደለም፤ ስህተትም አይደለም። ከላይ የተጠቀሱትን ጥንቃቄ የሚሹ ነገሮች ማስወገድ ከተቻለ ሰዎች በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር በሚሆኑበት ጊዜ ቢጾሙ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ይሁንና አምልኳችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው በዋነኝነት ልናደርገው የሚገባን ነገር ጾም አይደለም። ይሖዋ “ደስተኛ . . . አምላክ” ነው፤ አገልጋዮቹም ደስተኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ለሰዎች፣ . . . [ከዚህ] የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው።”—መክብብ 3:12, 13

አምልኳችንን በደስታ ልናከናውን ይገባል፤ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ጾምን ከደስታ ጋር አያይዞ የገለጸበት ቦታ የለም። በተጨማሪም መጾም ጤንነታችንን የሚጎዳ ወይም አምላክ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲያከናውኑት የሰጣቸውን የመንግሥቱን ምሥራች የማወጁን አስደሳች ሥራ ለማከናወን ኃይላችንን የሚያሟጥጥ ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።

እኛ በግላችን ለመጾምም ሆነ ላለመጾም ብንወስን በሌሎች ላይ ከመፍረድ መቆጠብ ይኖርብናል። “የአምላክ መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ ነው እንጂ የመብልና የመጠጥ ጉዳይ አይደለም።” በመሆኑም ጾምን በተመለከተ በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ውዝግብ ሊፈጠር አይገባም።—ሮም 14:17

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 አስቴር ከፉሪም በዓል በፊት የጾመችውን ጾም ያዘዘው አምላክ ባይሆንም ጾሟ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረ ይመስላል።

^ አን.14 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በጥንቶቹ የግሪክኛ ቅጂዎች ላይ የማይገኙ ስለ ጾም የሚናገሩ ጥቅሶችን ይዘዋል።—ማቴዎስ 17:21 አ.መ.ት፤ ማርቆስ 9:29 አ.መ.ት

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ፈሪሳውያን በሚጾሙበት ጊዜ አጉል ትሕትና ያሳዩ ነበር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የአምላክ መንግሥት . . . ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ ነው እንጂ የመብልና የመጠጥ ጉዳይ አይደለም”

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሁዳዴን ጾም በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

ለ40 ቀናት የሚጾመው የሁዳዴ ጾም (በኢትዮጵያ ወደ ሁለት ወር ገደማ ነው) ዓላማ ክርስቶስ ለ40 ቀናት የጾመበትን ጊዜ ለማሰብ እንደሆነ ይነገራል። ሆኖም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እሱ የጾመውን ጾም እንዲያስቡ አላዘዘም፤ እነሱም እንዲህ እንዳደረጉ የሚያሳይ ማስረጃ የለም። ከፋሲካ በዓል በፊት ስለሚጾመው የ40 ቀን ጾም የሚናገር ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበት እምነት የሚጣልበት ዘገባ የምናገኘው በ330 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጻፈ በሚገመተው የኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ በነበሩት በአትናቴዎስ ደብዳቤ ላይ ነው።

ኢየሱስ የጾመው ከተጠመቀ በኋላ እንጂ ከመሞቱ በፊት ስላልሆነ አንዳንድ ሃይማኖቶች ከፋሲካ በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት የሁዳዴን ጾም መጾማቸው አስገራሚ ይመስል ይሆናል። ይሁንና የጥንቶቹ ባቢሎናውያን፣ ግብጻውያን እና ግሪካውያን በአዲስ ዓመታቸው መጀመሪያ አካባቢ የ40 ቀን ጾም የመጾም ልማድ ነበራቸው። የክርስትና ልማድ እንደሆነ የሚታሰበው የሁዳዴ ጾም ከእነዚህ ሕዝቦች የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም።