በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስን በትሕትናውና በርኅራኄው ምሰሉት

ኢየሱስን በትሕትናውና በርኅራኄው ምሰሉት

‘ክርስቶስ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል።’—1 ጴጥ. 2:21

1. ኢየሱስን መምሰላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ የሚረዳን ለምንድን ነው?

ብዙውን ጊዜ፣ በባሕርያቸውና በአኗኗራቸው የምናደንቃቸውን ሰዎች የመምሰል ዝንባሌ አለን። በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ያህል ልንመስለው የሚገባ ሰው የለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ራሱ በአንድ ወቅት “እኔን ያየ አብንም አይቷል” ብሏል። (ዮሐ. 14:9) ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ ስላንጸባረቀ ወልድን ማየት አብን የማየት ያህል ነው። በመሆኑም ኢየሱስን በመሰልን መጠን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሁሉ የበላይ ወደሆነው አካል ማለትም ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን። በእርግጥም የልጁን ባሕርያትና አኗኗር መከተል ታላቅ ወሮታ ያስገኛል!

2, 3. (ሀ) ይሖዋ ስለ ልጁ ማንነት የሚገልጽ ዘገባ እንዲሰፍርልን ያደረገው ለምንድን ነው? ምን እንድናደርግስ ይፈልጋል? (ለ) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

2 ይሁንና የኢየሱስን ማንነት እንዴት ማወቅ እንችላለን? ደስ የሚለው ነገር፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃል የኢየሱስን ማንነት ይገልጽልናል። ይሖዋ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን ይህን ዘገባ ያሰፈረልን ልጁን በሚገባ እንድናውቀውና እንድንመስለው ስለሚፈልግ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:21ን አንብብ።) ኢየሱስ የተወው ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ከፈለግ’ ወይም ከዱካ ጋር ተመሳስሏል። በመሆኑም  ይሖዋ፣ የኢየሱስን ዱካ እየረገጥን እሱን ተከትለን እንድንሄድ የነገረን ያህል ነው። እርግጥ፣ ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ፍጹም ነው፤ እኛ ደግሞ ከፍጽምና እጅግ የራቅን ነን። ይሁንና ይሖዋ የኢየሱስን ፈለግ ፍጹም በሆነ መንገድ እንድንከተል አይጠብቅብንም። ከዚህ ይልቅ አብ፣ ፍጽምና የጎደለን ቢሆንም አቅማችን በፈቀደው መጠን ልጁን እንድንመስል ይፈልጋል።

3 እንግዲያው ማራኪ ከሆኑት የኢየሱስ ባሕርያት መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት። በዚህ ርዕስ ላይ ትሕትናውንና ርኅራኄውን እናያለን፤ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ ስላሳየው ድፍረትና ማስተዋል እንመረምራለን። ከእያንዳንዱ ባሕርይ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እናነሳለን፦ ይህ ባሕርይ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ይህን ባሕርይ ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ እሱን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ትሑት ነው

4. ትሕትና ሲባል ምን ማለት ነው?

4 ትሕትና ሲባል ምን ማለት ነው? ትዕቢተኛ የሆኑ ሰዎች በሞሉበት በዚህ ዓለም ላይ ትሕትና የድክመት ወይም በራስ ያለመተማመን ምልክት ተደርጎ ይታያል። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ እውነታው የዚህ ፍጹም ተቃራኒ ነው። ትሕትና ማሳየት ጥንካሬና ድፍረት ይጠይቃል። ትሕትና “የኩራትና የእብሪት ተቃራኒ የሆነ ዝንባሌ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ትሕትና” የሚል ፍቺ የተሰጠው ቃል ለራስ የተጋነነ አመለካከት አለመያዝ ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (ፊልጵ. 2:3) ትሕትናን ማዳበር፣ ስለ ራሳችን ካለን አመለካከት ይጀምራል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው “ትሕትና ሲባል በአምላክ ፊት ስንታይ ከምንም የማንቆጠር መሆናችንን መገንዘብ ማለት ነው።” በተጨማሪም በአምላክ ፊት ከልባችን ትሑት ከሆንን ራሳችንን ከሌሎች ሰዎች ከፍ አድርገን ከማየት እንቆጠባለን። (ሮም 12:3) ፍጽምና ለሚጎድላቸው የሰው ልጆች ትሕትናን ማዳበር ቀላል አይደለም። ሆኖም በአምላክ ፊት ስላለን ቦታ መለስ ብለን ካሰብንና የልጁን ፈለግ ከተከተልን ትሕትና ማንጸባረቅን መማር እንችላለን።

5, 6. (ሀ) የመላእክት አለቃ ሚካኤል ማን ነው? (ለ) ሚካኤል ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው? የአምላክ ልጅ፣ ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ በሰማይ እያለም ሆነ ፍጹም ሰው ሆኖ በምድር በኖረበት ወቅት ሁሉ ትሑት ነበር። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

6 አስተሳሰቡ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ይሁዳ፣ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በዚህ ረገድ የተወውን ምሳሌ አስፍሮልናል። (ይሁዳ 9ን አንብብ።) የመላእክት አለቃ ሚካኤል ይኸውም ኢየሱስ፣ ከክፉው ‘ከዲያብሎስ ጋር ተከራክሮ’ ነበር። የተከራከሩት “የሙሴን ሥጋ በተመለከተ” ነው። ሙሴ ከሞተ በኋላ ይሖዋ፣ ማንም በማያውቀው ቦታ እንደቀበረው ታስታውስ ይሆናል። (ዘዳ. 34:5, 6) ዲያብሎስ፣ የሙሴን አስከሬን የሐሰት አምልኮ ለማስፋፋት ሊጠቀምበት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ዲያብሎስ የነበረው የክፋት ሐሳብ ምንም ይሁን ምን፣ ሚካኤል በድፍረት ተቃውሞታል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “በተከራከረ ጊዜ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ “ከፍርድ ቤት ሙግት ጋር በተያያዘም ተሠርቶበታል።” ይህ አገላለጽ “ሚካኤል፣ ‘የሙሴን ሥጋ የመውሰድ መብት እንደሌለው በመግለጽ ዲያብሎስን እንደተከራከረው’” የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ይሁንና ሊቀ መላእክቱ፣ በዲያብሎስ ላይ የመፍረድ ሥልጣን እንደሌለው ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ጉዳዩን ወደ አጽናፈ ዓለሙ ዳኛ ማለትም ወደ ይሖዋ አቅርቦታል። ሚካኤል፣ የሚያስቆጣ ሁኔታ ቢያጋጥመውም ከሥልጣኑ አልፎ ከመሄድ ተቆጥቧል። ይህ፣ ኢየሱስ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ እንዳለው የሚጠቁም እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

7. ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በተግባሩ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት የተናገራቸውም ሆነ ያደረጋቸው ነገሮች እውነተኛ ትሕትና እንዳለው ይጠቁማሉ። ንግግሩ፦  ወደ ራሱ ትኩረት ለመሳብ በፍጹም አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ክብር ሁሉ ለአባቱ እንዲሰጥ ያደርግ ነበር። (ማር. 10:17, 18፤ ዮሐ. 7:16) ደቀ መዛሙርቱን በንግግሩ አቃልሏቸው ወይም የበታችነት ስሜት እንዲያድርባቸው አድርጎ አያውቅም። እንዲያውም መልካም ባሕርያቸውን በማድነቅና እንደሚተማመንባቸው በመግለጽ አክብሯቸዋል። (ሉቃስ 22:31, 32፤ ዮሐ. 1:47) ተግባሩ፦ ኢየሱስ ቁሳዊ ነገሮች በማብዛት ሕይወቱን ከማወሳሰብ ይልቅ ቀላል የሆነ አኗኗር በመምረጥ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ማቴ. 8:20) እጅግ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን በፈቃደኝነት አከናውኗል። (ዮሐ. 13:3-15) ታዛዥ በመሆን የላቀ ትሕትና አሳይቷል። (ፊልጵስዩስ 2:5-8ን አንብብ።) መታዘዝን ከሚጠሉ ትዕቢተኛ ሰዎች በተለየ ኢየሱስ “እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ” በመሆን ለአምላክ ፈቃድ በትሕትና ተገዝቷል። የሰው ልጅ የተባለው ኢየሱስ ‘በልቡ ትሑት’ እንደሆነ ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል።—ማቴ. 11:29

ኢየሱስን በትሕትናው ምሰሉት

8, 9. ትሕትና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

8 ትሕትና በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? አስተሳሰባችን፦ ትሑት ከሆንን ቦታችንን አልፈን ከመሄድ እንቆጠባለን። በሌሎች ላይ የመፍረድ ሥልጣን እንዳልተሰጠን ከተገነዘብን ሌሎች ስህተት ሲሠሩ ለመንቀፍ ወይም አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሱበትን ዓላማ ለመጠራጠር አንቸኩልም። (ሉቃስ 6:37፤ ያዕ. 4:12) ትሕትና፣ እኛ ያሉን ችሎታዎች ወይም መብቶች የሌሏቸውን ሰዎች ዝቅ አድርገን በመመልከት “እጅግ ጻድቅ” ከመሆን እንድንቆጠብ ይረዳናል። (መክ. 7:16) ትሑት የሆኑ ሽማግሌዎች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው እንደሚበልጡ አድርገው አያስቡም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያሉ እረኞች ‘ሌሎች ከእነሱ እንደሚበልጡ’ በማሰብ ራሳቸውን ከሁሉ እንደሚያንሱ አድርገው ይቆጥራሉ።—ፊልጵ. 2:3፤ ሉቃስ 9:48

9 ከ1894 ጀምሮ ፒልግሪም ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል የነበረውን የዋልተር ቶርን ምሳሌ እንመልከት። በዚህ ምድብ ላይ ለብዙ ዓመታት ካገለገለ በኋላ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመንግሥቱ እርሻ ላይ በዶሮ እርባታ ክፍል እንዲሠራ ተመደበ። ወንድም ቶርን፣ ራሱን ከፍ አድርጎ እየተመለከተ እንደሆነ ሲሰማው “አንተ የአቧራ ቅንጣት፣ ምን የምትኮራበት ነገር አለ?” በማለት ራሱን እንደሚገሥጽ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 40:12-15ን አንብብ።) ይህ በእርግጥም ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ነው!

10. በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን ትሕትና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ንግግራችን፦ ከልባችን ትሑት ከሆንን ይህ በንግግራችን ይንጸባረቃል። (ሉቃስ 6:45) ከሌሎች ጋር ስናወራ ባከናወንናቸው ነገሮች ወይም ባገኘናቸው መብቶች ላይ ከማተኮር እንርቃለን። (ምሳሌ 27:2) ይልቁንም የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን መልካም ጎን ለመመልከት እንጥራለን፤ እንዲሁም ለጥሩ ባሕርያቸው፣ ለችሎታቸውና ላከናወኑት ነገር አድናቆታችንን እንገልጽላቸዋለን። (ምሳሌ 15:23) ተግባራችን፦ ትሑት የሆኑ ክርስቲያኖች በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ የማግኘት ፍላጎት የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ለማገልገል ሲሉ ዓለም ዝቅተኛ እንደሆኑ አድርጎ የሚመለከታቸውን ሥራዎች እንኳ በመሥራት ቀላል ሕይወት ይመራሉ። (1 ጢሞ. 6:6, 8) ትሕትና ማሳየት የምንችልበት ከሁሉ የላቀው መንገድ ደግሞ ታዛዥነት ነው። በጉባኤ ውስጥ “ግንባር ቀደም ሆነው አመራር” ለሚሰጡን ወንድሞች መታዘዝ እና ከይሖዋ ድርጅት የምናገኘውን መመሪያ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ትሕትና ይጠይቃል።—ዕብ. 13:17

ኢየሱስ ሩኅሩኅ ነው

11. ርኅራኄ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አብራራ።

11 ርኅራኄ ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ርኅራኄ” ለሚለው ቃል “ለተጨነቀ ወይም ለተቸገረ ማዘንና ርዳታን መስጠት” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ርኅራኄ የፍቅር አንዱ ገጽታ ሲሆን እንደ ምሕረትና አዘኔታ ካሉት ለስለስ ያሉ ባሕርያት ጋር ይዛመዳል። ቅዱሳን መጻሕፍት “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ” እና “ከርኅራኄ  የመነጨ ምሕረት” የሚሉትን አገላለጾች ይጠቀማሉ። (ሉቃስ 1:78፤ 2 ቆሮ. 1:3፤ ፊልጵ. 1:8) አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ርኅራኄ እንድናሳይ የሚሰጡንን ሐሳብ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሐሳብ፣ የተቸገሩ ሰዎችን ስሜት እንድንረዳና ለእነሱ እንድናዝን የሚጠይቅ ብቻ አይደለም። በአሳቢነት ተነሳስተን ለእነሱ ትኩረት እንድንሰጥ እንዲሁም ሕይወታቸው እንዲታደስና አዲስ አቅጣጫ እንዲይዝ የሚያደርግ እርምጃ እንድንወስድ የቀረበ ማሳሰቢያ ነው።” ርኅራኄ ለተግባር የሚያነሳሳ ኃይል ነው። ሩኅሩኅ የሆነ ሰው በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ያደርጋል።

12. ኢየሱስ ለሌሎች ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? ይህስ ምን እንዲያደርግ አነሳስቶታል?

12 ኢየሱስ ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነው? በርኅራኄ ያንጸባረቀው ስሜትና ያደረገው ነገር፦ ኢየሱስ ለሌሎች ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ አሳይቷል። ኢየሱስ፣ የማርያም ወንድም አልዓዛር በመሞቱ ማርያምና ሌሎች ሰዎች ሲያለቅሱ በተመለከተ ጊዜ ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:32-35ን አንብብ።) የአንዲትን መበለት ልጅ ባስነሳበት ጊዜ እንደተሰማው ሁሉ በዚህ ወቅትም ከልቡ ስላዘነ አልዓዛርን ከሞት አስነሳው። (ሉቃስ 7:11-15፤ ዮሐ. 11:38-44) ኢየሱስ በርኅራኄ ስሜት ተገፋፍቶ ያከናወነው ይህ ድርጊት አልዓዛር በሰማይ ሕይወት እንዲያገኝ መንገድ ከፍቶ ሊሆን ይችላል። ከዚያ ቀደም ኢየሱስ ወደ እሱ መጥቶ ለነበረው ሕዝብ “ከርኅራኄ የመነጨ አሳቢነት” አሳይቷል። በርኅራኄ ተነሳስቶም ‘ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል።’ (ማር. 6:34 ኪንግደም ኢንተርሊኒየር) ትምህርቱን የተቀበሉ ሰዎች ሁሉ ሕይወታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል። ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው ርኅራኄ ከስሜት አልፎ ሌሎችን ለመርዳት እርምጃ እንዲወስድ እንዳነሳሳው ልብ በል።—ማቴ. 15:32-38፤ 20:29-34፤ ማር. 1:40-42

13. ኢየሱስ ሌሎችን ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ ያነጋገረው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

13 ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት ንግግሩ፦ ኢየሱስ ልቡ ሩኅሩኅ በመሆኑ ሌሎችን በተለይም የተጨቆኑትን ያነጋገራቸው ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ ነበር። ሐዋርያው ማቴዎስ፣ “የተቀጠቀጠ ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤ ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል” በማለት ኢሳይያስ የተናገረው ሐሳብ በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ገልጿል። (ኢሳ. 42:3፤ ማቴ. 12:20) ኢየሱስ የሚናገረው፣ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆ ወይም ሊጠፋ እንደተቃረበ የጧፍ ክር የነበሩ ሰዎችን መንፈስ በሚያድስ መንገድ ነበር። “ልባቸው የተሰበረውን” ለመጠገን ተስፋ የሚሰጥ መልእክት ሰብኳል። (ኢሳ. 61:1) ‘የደከማቸውና ሸክም የከበዳቸው’ ሰዎች ወደ እሱ እንዲመጡ የጋበዘ ሲሆን ‘ለነፍሳቸው እረፍት እንደሚያገኙም’ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 11:28-30) አምላክ፣ በዓለም ዘንድ እንደ ‘ትንሽ’ የሚታዩትን ይኸውም ያን ያህል ቦታ የማይሰጣቸውን ጨምሮ ለአምላኪዎቹ በሙሉ ከርኅራኄ የመነጨ አሳቢነት እንደሚያሳያቸው ኢየሱስ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል።—ማቴ. 18:12-14፤ ሉቃስ 12:6, 7

ኢየሱስን በርኅራኄው ምሰሉት

14. የርኅራኄ ስሜት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

14 ርኅራኄ በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በርኅራኄ የምናሳየው ስሜት፦ የርኅራኄ ስሜት ማሳየት ቀላል ላይሆንልን ይችላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህንን ባሕርይ እንድናዳብር ያሳስበናል። “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ” ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲለብሱ የሚጠበቅባቸው የአዲሱ ስብዕና ክፍል ነው። (ቆላስይስ 3:9, 10, 12ን አንብብ።) አንተስ የርኅራኄ ስሜት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? ልብህን ወለል አድርገህ ክፈት። (2 ቆሮ. 6:11-13) አንድ ሰው ስሜቱንና የሚያሳስቡትን ነገሮች ሲነግርህ በጥሞና አዳምጥ። (ያዕ. 1:19) የግለሰቡን ሁኔታ በአእምሮህ በመሳል ‘እኔ በእሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን ይሰማኝ ነበር? ምን እንዲደረግልኝስ እፈልግ ነበር?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።—1 ጴጥ. 3:8

15. እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆ ወይም እንደሚጤስ የጧፍ ክር የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?

 15 በርኅራኄ ተነሳስተን የምናደርገው ነገር፦ ርኅራኄ፣ በሌሎች በተለይም እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆ ወይም እንደሚጤስ የጧፍ ክር በሆኑ ሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት እንድንነሳሳ ያደርገናል። እንዲህ ያሉ ሰዎችን ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? ሮም 12:15 “ከሚያለቅሱ ሰዎች ጋር አልቅሱ” ይላል። ልባቸው የተደቆሰ ሰዎች ከምንም በላይ የሚፈልጉት የመፍትሔ ሐሳብ ሳይሆን ስሜታቸውን የሚረዳላቸው ሰው ሊሆን ይችላል። ልጇን በሞት ካጣች በኋላ የእምነት ባልንጀሮቿ ያጽናኗት አንዲት እህት “ወዳጆቼ መጥተው አብረውኝ ማልቀሳቸው በራሱ አጽናንቶኛል” ብላለች። ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ተግባሮች በማከናወንም ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን። በጉባኤ ውስጥ ቤቷ ጥገና የሚያስፈልገው መበለት ታውቃለህ? ወደ ስብሰባ፣ አገልግሎት ወይም ሐኪም ቤት ለመሄድ እርዳታ የሚያስፈልገው አረጋዊ ክርስቲያን አለ? እርዳታ ለሚያስፈልገው የእምነት ባልንጀራችን፣ በደግነት የምናደርጋቸው ትናንሽ የሚመስሉ ነገሮች እንኳ በሕይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። (1 ዮሐ. 3:17, 18) በርኅራኄ ተነሳስተን ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት የምንችልበት ከሁሉ የላቀው መንገድ ደግሞ በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ነው። ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም!

ለእምነት ባልንጀሮችህ ከልብ ታስባለህ? (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

16. የተጨነቁ ሰዎችን ለማበረታታት ምን ማለት እንችላለን?

16 ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት ንግግራችን፦ ለሌሎች ከርኅራኄ የመነጨ አሳቢነት ካለን ‘የተጨነቁትን ነፍሳት ለማጽናናት’ እንነሳሳለን። (1 ተሰ. 5:14) እንዲህ ያሉ ሰዎችን ለማበረታታት ምን ማለት እንችላለን? ከልባችን እንደምናስብላቸው በመግለጽ መንፈሳቸው እንዲታደስ እናደርጋለን። ከልብ እንደምናደንቃቸው በመናገር መልካም ባሕርያትና ችሎታዎች እንዳሏቸው እንዲያስተውሉ ማድረግ ይቻላል። ይሖዋ ወደ ልጁ የሳባቸው ውድ እንደሆኑ አድርጎ ስለሚመለከታቸው እንደሆነ ልናስታውሳቸው እንችላለን። (ዮሐ. 6:44) እንዲሁም ይሖዋ “ልባቸው ለተሰበረ” ወይም ‘መንፈሳቸው ለተሰበረ’ አገልጋዮቹ በጥልቅ እንደሚያስብ በእርግጠኝነት እንግለጽላቸው። (መዝ. 34:18) በርኅራኄ የምንናገረው ነገር ማጽናኛ ለሚፈልጉ ሰዎች ፈውስ ሊያስገኝላቸው ይችላል።—ምሳሌ 16:24

17, 18. (ሀ) ይሖዋ፣ ሽማግሌዎች በጎቹን እንዴት እንዲይዙ ይጠብቅባቸዋል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

17 እናንት ሽማግሌዎች፣ ይሖዋ በጎቹን በርኅራኄ እንድትይዙ ይጠብቅባችኋል። (ሥራ 20:28, 29) በጎቹን የመመገብ፣ የማበረታታት እንዲሁም መንፈሳቸውን የማደስ ኃላፊነት እንዳለባችሁ አስታውሱ። (ኢሳ. 32:1, 2፤ 1 ጴጥ. 5:2-4) እንግዲያው ለበጎቹ ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ያለው ሽማግሌ፣ ሕጎችን በማውጣት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷቸው ሁኔታቸው ከሚፈቅድላቸው የበለጠ እንዲሠሩ በመጫን በጎቹን ለመቆጣጠር አይሞክርም። ይልቁንም በጎቹ ልባቸው በደስታ እንዲሞላ ለማድረግ ይጥራል፤ እንዲሁም ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር አቅማቸው በፈቀደ መጠን እሱን ለማገልገል እንደሚያነሳሳቸው ይተማመናል።—ማቴ. 22:37

18 ኢየሱስ ባሳየው ትሕትና እና ርኅራኄ ላይ ስናሰላስል ምንጊዜም የእሱን ፈለግ ለመከተል እንደምንነሳሳ ጥርጥር የለውም። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ማራኪ ከሆኑት የኢየሱስ ባሕርያት መካከል ሁለቱን ይኸውም ድፍረቱንና አስተዋይነቱን እንመረምራለን።