አዎንታዊ አመለካከት ይዘን ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
“ሰው ምንም ያህል ብዙ ዓመት ቢኖር፣ በእነዚህ ሁሉ ይደሰት።”—መክ. 11:8
1. ለደስታችን ምክንያት የሚሆኑ ከይሖዋ ያገኘናቸው በረከቶች የትኞቹ ናቸው?
ይሖዋ ደስተኛ እንድንሆን ይፈልጋል፤ በመሆኑም ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮችን አትረፍርፎ ሰጥቶናል። በመጀመሪያ ደረጃ ሕይወትን ሰጥቶናል። አምላክ ወደ እውነተኛው አምልኮ ስለሳበን ሕይወታችንን እሱን ለማወደስ ልንጠቀምበት እንችላለን። (መዝ. 144:15፤ ዮሐ. 6:44) ይሖዋ እንደሚወድደን አረጋግጦልናል፤ እንዲሁም እሱን ማገልገላችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። (ኤር. 31:3፤ 2 ቆሮ. 4:16) የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ የምናገኝበትና አፍቃሪ የሆነ የወንድማማች ኅብረት ያለበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ስለምንኖር ደስተኞች ነን። ከዚህም በተጨማሪ ከፊታችን አስደናቂ ተስፋ ተዘርግቶልናል።
2. አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከምን ዓይነት ስሜት ጋር ይታገላሉ?
2 ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ቢኖሩም አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ስለ ራሳቸው አሉታዊ አመለካከት ያድርባቸዋል። ለይሖዋ የሚያቀርቡት አገልግሎትም ሆነ እነሱ ራሳቸው በእሱ ዘንድ ምንም ያህል ዋጋ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ካለ አሉታዊ ስሜት ጋር ሁልጊዜ የሚታገሉ ክርስቲያኖች “ብዙ ዓመት” በመኖር መደሰት የሚለው ሐሳብ የሕልም እንጀራ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ሁሉ ነገር ጨለማ ሆኖ ይታያቸው ይሆናል።—መክ. 11:8
3. አንዳንዶች አሉታዊ ስሜት እንዲያድርባቸው የሚያደርጓቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
3 እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸው ወንድሞችና እህቶች አሉታዊ ስሜት እንዲያድርባቸው ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል ያሰቡት አለመሳካቱ፣ የዕድሜ መግፋት የሚያመጣቸው አንዳንድ ችግሮች ወይም በሽታ ይገኙበታል። (መዝ. 71:9፤ ምሳሌ 13:12፤ መክ. 7:7) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ እየተደሰተብን ቢሆንም እንኳ ሁላችንንም አታላይ የሆነው ልባችን ሊኮንነን ይችላል። (ኤር. 17:9፤ 1 ዮሐ. 3:20) ዲያብሎስ በአምላክ አገልጋዮች ላይ የሐሰት ክስ ይሰነዝራል። የሰይጣን ዓይነት አመለካከት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በአምላክ ዘንድ ዋጋ እንደሌለን እንዲሰማን ሊያደርጉ ይሞክራሉ፤ እምነት ያልነበረው ኤልፋዝ፣ ኢዮብ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲያድርበት ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ይህ ሐሳብ በኢዮብ ዘመንም ሆነ ዛሬ ውሸት እንደሆነ ግልጽ ነው።—ኢዮብ 4:18, 19
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ምን ነገር እንመረምራለን?
4 ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ [ቢሄዱ] እንኳ” አብሯቸው እንደሚሆን በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በግልጽ ተናግሯል። (መዝ. 23:4) ከእኛ ጋር መሆኑን የሚያሳይበት አንደኛው መንገድ በቃሉ አማካኝነት የሚሰጠን እርዳታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የተሳሳቱ አመለካከቶችንና አሉታዊ ሐሳቦችን ጨምሮ “ምሽግን ለመደርመስ የሚያስችል መለኮታዊ ኃይል” አለው። (2 ቆሮ. 10:4, 5) እንግዲያው አዎንታዊ አመለካከትን ለማዳበር ብሎም ይህን አመለካከት ይዘን ለመቀጠል መጽሐፍ ቅዱስ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ይህን ስናደርግ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ለማበረታታት የሚጠቅም ሐሳብ እናገኛለን።
አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም
5. አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር የሚረዳን ምን ዓይነት ምርመራ ማድረጋችን ነው?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር የሚረዱንን አንዳንድ ነጥቦች ገልጿል። በቆሮንቶስ ያሉ ክርስቲያኖችን “በእምነት ውስጥ እየተመላለሳችሁ መሆናችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ” በማለት አሳስቧቸዋል። (2 ቆሮ. 13:5) “እምነት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የክርስትና ትምህርቶች በአጠቃላይ ያመለክታል። ንግግራችንና ድርጊታችን ከእነዚህ ትምህርቶች ጋር የሚስማማ ከሆነ ምርመራውን አልፈናል እንዲሁም ‘በእምነት ውስጥ እየተመላለስን’ እንደሆነ እያሳየን ነው ሊባል ይችላል። በእርግጥ አኗኗራችን ከሁሉም የክርስትና ትምህርቶች ጋር የሚስማማ መሆኑንም መመርመር አለብን። ከእነዚህ ትምህርቶች መካከል የምንታዘዘው እኛ የፈለግነውን ብቻ መሆን የለበትም።—ያዕ. 2:10, 11
6. ‘በእምነት ውስጥ እየተመላለስን መሆናችንን ለማወቅ’ ራሳችንን መመርመር ያለብን ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
6 ምርመራውን እንደማታልፍ ከተሰማህ እንዲህ ያለ ምርመራ ለማድረግ ታመነታ ይሆናል። ይሁንና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው፣ እኛ ለራሳችን ያለን አመለካከት ሳይሆን ይሖዋ እኛን የሚያይበት መንገድ ነው፤ ምክንያቱም የእሱ ሐሳብ ከእኛ በጣም ከፍ ያለ ነው። (ኢሳ. 55:8, 9) አምላክ፣ አገልጋዮቹን የሚመረምራቸው እነሱን ለመኮነን ሳይሆን ጥሩ ባሕርያቸውን ለማግኘትና እነሱን ለመርዳት ነው። ‘በእምነት ውስጥ እየተመላለስህ መሆንህን ለማወቅ’ በአምላክ ቃል ተጠቅመህ ራስህን ስትመረምር፣ አምላክ አንተን በሚያይበት መንገድ ራስህን መመልከት ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ‘በአምላክ ፊት ዋጋ የለኝም’ የሚለውን አመለካከት አስወግደህ በእሱ ፊት ውድ እንደሆንክ የሚገልጸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት ለማዳበር ይረዳሃል። ይህም ጨለማ በሆነ ክፍል ውስጥ የመስኮቱን መጋረጃ ስትገልጠውና ብርሃን ሲገባ የሚያድርብህ ዓይነት ስሜት እንዲፈጠርብህ ያደርጋል።
7. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ታማኝ ሰዎች ከተዉት ምሳሌ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
7 ራሳችንን በዚህ መንገድ ለመመርመር የሚረዳን አንዱ ጥሩ መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ታማኝ ሰዎች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰል ነው። እነሱ የነበሩበትን ሁኔታ ወይም ስሜታቸውን ከራስህ ጋር አወዳድር፤ እንዲሁም በእነሱ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ እንደነበረ ለማሰብ ሞክር። ‘በእምነት ውስጥ እየተመላለስህ መሆንህን’ ለማረጋገጥና አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚረዳህ የሚያሳዩ ሦስት ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።
ድሃዋ መበለት
8, 9. (ሀ) ድሃዋ መበለት የነበረችበት ሁኔታ ምን ይመስላል? (ለ) ይህች መበለት ምን ዓይነት አሉታዊ ስሜት አድሮባት ሊሆን ይችላል?
8 ኢየሱስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ሆኖ አንዲትን መበለት እየተመለከተ ነው። ይህች መበለት የተወችው ምሳሌ የአቅም ገደብ ቢኖርብንም ስለ ራሳችን አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። (ሉቃስ 21:1-4ን አንብብ።) እስቲ የዚህችን መበለት ሁኔታ እንመልከት። ይህች ሴት ባሏን በሞት ማጣቷ ያስከተለባት ሐዘን ሳያንሳት መበለቶችን ከመርዳት ይልቅ እንደ እሷ ያሉ ምስኪኖችን ‘ቤት የሚያራቁቱ’ የሃይማኖት መሪዎች የሚያደርሱባትን እንግልት ችላ መኖር ነበረባት። (ሉቃስ 20:47) ይህች ሴት በጣም ድሃ ስለነበረች ለቤተ መቅደሱ መስጠት የምትችለው አንድ የቀን ሠራተኛ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚያገኘውን ገቢ ያህል ብቻ ነበር።
9 መበለቷ ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞችን ይዛ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ስትሄድ ምን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል አስበው። ባሏ በሕይወት በነበረበት ወቅት ትሰጥ ከነበረው አንጻር አሁን የምትሰጠው ምን ያህል ትንሽ እንደሆነ እያሰበች ይሆን? ከእሷ በፊት ያሉት ሰዎች የሚሰጡትን ብዛት ያለው ገንዘብ ስትመለከት ትሸማቀቅ ምናልባትም የእሷ ስጦታ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ ይሰማት ይሆን? እንዲህ ዓይነት ስሜት አድሮባት ሊሆን ቢችልም እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ አቅሟ የፈቀደውን ከማድረግ ወደኋላ አላለችም።
10. ኢየሱስ፣ መበለቲቷን አምላክ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታት ያሳየው እንዴት ነው?
10 መበለቲቷንም ሆነ የሰጠችውን ገንዘብ ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ኢየሱስ አሳይቷል። “[ከሀብታሞቹ ሁሉ] የበለጠ የከተተችው እሷ ነች” በማለት ተናግሯል። መበለቷ የሰጠችው ገንዘብ ሌሎቹ ከሰጡት ጋር መቀላቀሉ አይቀርም፤ ያም ቢሆን ኢየሱስ፣ መበለቷን ለይቶ በመጥቀስ አድንቋታል። በመዋጮ ዕቃዎቹ ውስጥ ያለውን መባ የሚሰበስቡት ሰዎች በኋላ ላይ መጥተው ሁለቱን ሳንቲሞች ሲያገኙ፣ እነዚያ ሳንቲሞችም ሆኑ ያንን ስጦታ የሰጠችው ሴት በይሖዋ ፊት ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ማወቅ አይችሉም። ይሁን እንጂ ዋናው ነገር ሌሎች ሰዎች ያላቸው አመለካከት ወይም መበለቷ ስለ ራሷ ያላት ስሜት ሳይሆን የአምላክ አመለካከት ነው። በዚህ ዘገባ ተጠቅመህ፣ በእምነት ውስጥ እየተመላለስህ መሆንህን ለማወቅ ራስህን መመርመር ትችላለህ?
11. ከመበለቷ ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?
11 ለይሖዋ መስጠት የምትችለው ነገር ባለህበት ሁኔታ ላይ የተመካ ሊሆን ይችላል። በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል ሳቢያ አንዳንዶች ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ በጣም ትንሽ ይሆናል። ታዲያ እነዚህ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ ያሳለፉት ሰዓት ሪፖርት ለማድረግ የሚበቃ እንዳልሆነ ሊሰማቸው ይገባል? በሌላ በኩል ደግሞ ከባድ የአቅም ገደብ ባይኖርብህም እንኳ የአምላክ ሕዝቦች በእሱ አገልግሎት ከሚያሳልፉት ሰዓት አንጻር የአንተ አስተዋጽኦ ከቁብ የሚቆጠር እንዳልሆነ ይሰማህ ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ በእሱ አገልግሎት የምናከናውነውን እያንዳንዱን ነገር በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የምናደርገውን ነገር ልብ የሚል ከመሆኑም በላይ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ከድሃዋ መበለት ታሪክ መማር እንችላለን። እስቲ ባለፈው ዓመት በይሖዋ አገልግሎት ስላሳለፍከው ጊዜ መለስ ብለህ አስብ። አገልግሎትህን ለማከናወን ስትል ለየት ያለ መሥዋዕት የከፈልክበት ሰዓት አለ? ከሆነ ይሖዋ በዚያ ሰዓት ያከናወንከውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። እንደ ድሃዋ መበለት በይሖዋ አገልግሎት የተቻለህን ሁሉ እያደረግህ ከሆነ ‘በእምነት ውስጥ እየተመላለስክ’ መሆንህን ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለህ።
“ነፍሴን ውሰዳት”
12-14. (ሀ) ኤልያስ ምን ዓይነት አሉታዊ ስሜት ተፈጥሮበት ነበር? (ለ) ኤልያስ እንዲህ የተሰማው ለምን ሊሆን ይችላል?
12 ነቢዩ ኤልያስ ለይሖዋ ታማኝ ከመሆኑም ሌላ ጠንካራ እምነት ነበረው። ያም ቢሆን ግን በአንድ ወቅት በጣም ተስፋ ቆርጦ ስለነበር “በቅቶኛል፤ . . . ነፍሴን ውሰዳት” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (1 ነገ. 19:4) እንዲህ ዓይነት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰምቷቸው የማያውቁ ሰዎች የኤልያስን ጸሎት እንደ ‘ኀይለ ቃል’ ይቆጥሩት ይሆናል። (ኢዮብ 6:3) ኤልያስ ግን የተናገረው በልቡ የተሰማውን ነበር። ኤልያስ ሞትን በመመኘቱ ይሖዋ እንዳልገሠጸው ከዚህ ይልቅ እንደረዳው ልብ በል።
13 ኤልያስ እንዲህ የተሰማው ለምን ነበር? ይህን ከማለቱ ትንሽ ቀደም ብሎ፣ ለእስራኤላውያን አቋማቸውን እንዲመረምሩ የሚያደርግ ፈተና አቅርቦላቸው ነበር፤ በውጤቱም ይሖዋ እውነተኛው አምላክ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ከዚያ በኋላ 450 የበዓል ነቢያት ተገደሉ። (1 ነገ. 18:37-40) ኤልያስ፣ የአምላክ ሕዝቦች ከዚህ በኋላ ወደ ንጹሑ አምልኮ እንደሚመለሱ ተስፋ አድርጎ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ነገሩ እንዳሰበው አልሆነም። ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል፣ እንደምታስገድለው የሚገልጽ መልእክት ለኤልያስ ላከችበት። እሱም ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል በስተ ደቡብ ያለችውን ይሁዳን አቋርጦ ማንም ሰው ዝር ወደማይልበት ምድረ በዳ ሸሸ።—1 ነገ. 19:2-4
14 ኤልያስ በዚያ ምድረ በዳ ብቻውን በነበረበት ወቅት የተለያዩ ሐሳቦችን ያወጣና ያወርድ ነበር፤ በዚህ ጊዜ፣ ነቢይ ሆኖ ያከናወነው ሥራ ከንቱ እንደሆነ ሳያስብ አልቀረም። በመሆኑም “እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥም” በማለት ለይሖዋ ተናገረ። ኤልያስ ይህን ሲል፣ ሞተው አፈር እንደሆኑት የቀድሞ አባቶቹ ሁሉ እሱም ምንም የማይረባ እንደሆነ እንደተሰማው መግለጹ ነበር። በሌላ አባባል፣ በራሱ መሥፈርት ራሱን መርምሮ በይሖዋም ሆነ በሌላ በማንም ሰው ዓይን ምንም የማይጠቀም እንደሆነ ተሰምቶት ነበር።
15. አምላክ፣ ኤልያስን ምንጊዜም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ያረጋገጠለት እንዴት ነው?
15 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ግን ኤልያስን የተመለከተው ከዚህ በተለየ መንገድ ነው። ኤልያስ በዚያ ወቅትም ቢሆን በይሖዋ ዘንድ ውድ ነበር፤ ደግሞም ይሖዋ ይህንን እንዲገነዘብ ረድቶታል። አምላክ፣ አንድ መልአክ በመላክ ኤልያስን አበረታትቶታል። በተጨማሪም ለኤልያስ ምግብና መጠጥ ያቀረበለት ሲሆን ይህም በስተ ደቡብ እስካለው የኮሬብ ተራራ ድረስ ለ40 ቀን ያህል ለመጓዝ የሚያስችል ኃይል ሰጥቶታል። ከዚህም ሌላ ኤልያስ ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ሌሎች እስራኤላውያን እንደሌሉ ተሰምቶት ነበር፤ ይሁንና አምላክ ይህን አመለካከቱን እንዲያስተካክል በደግነት ረድቶታል። አምላክ ለኤልያስ አዲስ ሥራ የሰጠው መሆኑም ትኩረት የሚስብ ነው፤ ኤልያስም የተሰጠውን ሥራ ተቀብሏል። ኤልያስ ይሖዋ በሰጠው እርዳታ የተጠቀመ ሲሆን ኃይሉ ታድሶ እንደገና የነቢይነት ሥራውን ማከናወን ችሏል።—1 ነገ. 19:5-8, 15-19
16. አምላክ በየትኞቹ መንገዶች ተንከባክቦሃል?
16 የኤልያስ ታሪክ፣ በእምነት ውስጥ እየተመላለስክ መሆንህን ለማረጋገጥና አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር ሊረዳህ ይችላል። በመጀመሪያ፣ ይሖዋ በየትኞቹ መንገዶች እንደተንከባከበህ ለማሰብ ሞክር። ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱ ምናልባትም አንድ ሽማግሌ ወይም ሌላ የጎለመሰ ክርስቲያን፣ እገዛ በሚያስፈልግህ ጊዜ ረድቶሃል? (ገላ. 6:2) ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ወይም ከጉባኤ ስብሰባዎች የምታገኘው መንፈሳዊ ምግብ ይሖዋ እንደሚያስብልህ እንዲሰማህ አድርጎሃል? በሚቀጥለው ጊዜ እንዲህ ዓይነት እርዳታ ስታገኝ የእርዳታው ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ በመገንዘብ በጸሎት አመስግነው።—መዝ. 121:1, 2
17. ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር በተያያዘ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ነገር ምንድን ነው?
17 ሁለተኛ፣ አሉታዊ አስተሳሰብ አሳሳች ሊሆን እንደሚችል አስተውል። ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አምላክ ለእኛ ያለው አመለካከት ነው። (ሮም 14:4ን አንብብ።) ይሖዋ ለእሱ ያደርን መሆናችንን እና ታማኝነታችንን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል፤ ለእኛ ያለው አመለካከት ባከናወንናቸው ነገሮች ላይ የተመካ አይደለም። ደግሞም ልክ እንደ ኤልያስ፣ አንተም ከምታስበው በላይ በይሖዋ አገልግሎት ብዙ አከናውነህ ሊሆን ይችላል። በጉባኤ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ያሳደርክባቸው ወይም በስብከቱ ሥራህ አማካኝነት ወደ እውነት የመጡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ።
18. ይሖዋ የሚሰጥህ ኃላፊነት ምን ያረጋግጣል?
18 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ይሖዋ የሚሰጥህን እያንዳንዱን ኃላፊነት እሱ ከአንተ ጋር መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው። (ኤር. 20:11) እንደ ኤልያስ ሁሉ አንተም አገልግሎትህ ፍሬ እንደሌለው ወይም አንዳንድ መንፈሳዊ ግቦች ላይ መድረስ እንደማትችል ተሰምቶህ ተስፋ ትቆርጥ ይሆናል። ያም ቢሆን ማንኛችንም በአሁኑ ወቅት ሊኖረን ከሚችለው ሁሉ በላቀው መብት መካፈል ችለሃል፤ ይህም ምሥራቹን የመስበክና የአምላክን ስም የመሸከም መብት ነው። ታማኝ ሆነህ ለመቀጠል ጥረት አድርግ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው አንተም “ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” ልትባል ትችላለህ።—ማቴ. 25:23
“የተጨነቀ ሰው ጸሎት”
19. የመዝሙር 102 ጸሐፊ ምን ችግሮች አጋጥመውት ነበር?
19 የመዝሙር 102 ጸሐፊ ታውኮና በጣም ‘ተጨንቆ’ ነበር። ከፍተኛ አካላዊ ሥቃይ የነበረው ይመስላል፤ ከዚህም ሌላ ስሜቱ ተደቁሶ እንዲሁም ችግሮቹን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት አጥቶ ነበር። (በመዝሙር 102 አናት ላይ የሚገኘውን መግለጫ ተመልከት።) መዝሙራዊው የተናገራቸው ቃላት እንደሚጠቁሙት ሐሳቡን ሁሉ የተቆጣጠረው ሥቃዩና ብቸኝነቱ እንዲሁም የውስጥ ስሜቱ ነበር። (መዝ. 102:3, 4, 6, 11) ይሖዋ ሊጥለው እንደፈለገ ተሰምቶት ነበር።—መዝ. 102:10
20. ጸሎት አንድ ሰው አሉታዊ ስሜቶችን ለማስወገድ በሚያደርገው ትግል ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?
20 ያም ቢሆን መዝሙራዊው ይሖዋን ማወደሱን ቀጥሏል። (መዝሙር 102:19-21ን አንብብ።) ከመዝሙር 102 እንደምንመለከተው በእምነት ውስጥ እየተመላለሱ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ ሥቃይ ሊደርስባቸውና ያጋጠማቸው ችግር ሐሳባቸውን ሁሉ ሊቆጣጠረው ይችላል። መዝሙራዊው “[በቤት] ጕልላት ላይ እንዳለ ብቸኛ ወፍ” እንደሆነና ከችግሩ ሌላ ማንም አጠገቡ እንደሌለ ተሰምቶት ነበር። (መዝ. 102:7) አንተም እንዲህ ዓይነት ስሜት ከተፈጠረብህ እንደ መዝሙራዊው የልብህን አውጥተህ ለይሖዋ ንገረው። በተጨነቅህ ወቅት የምታቀርበው ጸሎት አሉታዊ ሐሳቦችን መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል። ይሖዋ ‘የችግረኞችን ጸሎት እንደሚመለከትና ልመናቸውን እንደማይንቅ’ ቃል ገብቷል። (መዝ. 102:17) ይህን ቃሉን እንደሚጠብቅ ሙሉ እምነት ይኑርህ።
21. አሉታዊ አመለካከቶችን ለማሸነፍ የሚታገል ሰው አዎንታዊ አመለካከትን ይበልጥ ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው?
21 መዝሙር 102 አዎንታዊ አመለካከትን ይበልጥ ማዳበር የሚቻለው እንዴት እንደሆነም ይጠቁመናል። መዝሙራዊው ትኩረቱን ከይሖዋ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ በማድረግ አዎንታዊ አመለካከት ማዳበር ችሏል። (መዝ. 102:12, 27) ይሖዋ ሕዝቦቹን በመከራቸው ወቅት ለመርዳት ምንጊዜም ቢሆን ከጎናቸው እንደሚሆን ማወቁ መዝሙራዊውን አጽናንቶታል። አንተም ባደረብህ አሉታዊ ስሜት የተነሳ ለጊዜውም ቢሆን በይሖዋ አገልግሎት የምትፈልገውን ያህል መካፈል ከከበደህ ስለ ጉዳዩ ጸልይ። የምትጸልየው አምላክ ልመናህን ሰምቶ ከጭንቀትህ እንዲገላግልህ ብቻ ሳይሆን ‘የይሖዋ ስም እንዲታወጅ’ ጭምር መሆን አለበት።—መዝ. 102:20, 21
22. ማንኛችንም ብንሆን ይሖዋን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?
22 በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን፣ በእምነት ውስጥ እየተመላለስን እንደሆንን እና ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን ለራሳችን ማረጋገጥ እንችላለን። በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ አሉታዊ ስሜቶችን ወይም ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮችን በሙሉ ማስወገድ እንደማንችል የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ማንኛችንም ብንሆን ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን በመቀጠል እሱን ማስደሰትና መዳንን ማግኘት እንችላለን።—ማቴ. 24:13