በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ምዕራብ አፍሪካ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ምዕራብ አፍሪካ

ኮት ዲቩዋር ውስጥ በድሆች መንደር ያደገው ፓስካል ኑሮውን ለማሻሻል ይጓጓ ነበር። አማተር ቦክሰኛ የነበረው ፓስካል ‘ታዋቂ ስፖርተኛና ሀብታም ለመሆን የት አገር ብሄድ ይሻላል?’ ብሎ ያስብ ነበር። በ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ በነበረበት ወቅት አውሮፓ ቢሄድ እንደሚሳካለት ተሰማው። ይሁንና አስፈላጊው የጉዞ ሠነድ ስላልነበረው በሕገ ወጥ መንገድ አውሮፓ ለመግባት ወሰነ።

በ1998 ፓስካል በ27 ዓመቱ ጉዞ ጀመረ። ድንበሩን ተሻግሮ ጋና ገባ፤ ከዚያም ቶጎንና ቤኒንን አቋርጦ ኒጀር ውስጥ ወደምትገኘው ቢርኒ ንኮኒ ወደተባለች ከተማ ደረሰ። በጣም አደገኛ የሆነውን ጉዞ የሚጀምረው ከዚህ በኋላ ነው። ወደ ሰሜን ለመጓዝ በከባድ መኪና ላይ ተጭኖ የሰሃራን በረሃ ማቋረጥ ነበረበት። ከዚያም ሜድትራንያን ባሕር ሲደርስ ወደ አውሮፓ የሚሄድ ጀልባ ላይ ይሳፈራል። ዕቅዱ ይህን ይመስል ነበር፤ ይሁንና በኒጀር ሳለ ያጋጠሙት ሁለት ነገሮች ጉዞውን እንዳይቀጥል አደረጉት።

በመጀመሪያ ደረጃ ገንዘብ አለቀበት። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኖኤ ከተባለ አቅኚ ጋር ተገናኝቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ። የተማረው ነገር በጣም ስለነካው ለሕይወት የነበረው አመለካከት ተቀየረ። ቁሳዊ ሀብት ለማካበት የነበረውን ግብ ትቶ ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት መስጠት ጀመረ። ፓስካል በታኅሣሥ 1999 ተጠመቀ። ለይሖዋ ያለውን የአመስጋኝነት ስሜት ለመግለጽ በ2001 በኒጀር እውነትን በሰማበት በዚያው ከተማ አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። አገልግሎቱን በተመለከተ ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው? “ሕይወቴ በጣም አስደሳች ሆኖልኛል!” በማለት ተናግሯል።

በአፍሪካ የተሻለ ሕይወት መምራት

አነ-ራከል

እንደ ፓስካል ሁሉ ብዙዎች እርካታ የተሞላበት ሕይወት ለመምራት መንፈሳዊ ግቦች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። እንዲህ ያሉ ግቦች ላይ ለመድረስ አንዳንዶች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ለማገልገል ሲሉ አውሮፓን ለቀው በአፍሪካ መኖር ጀምረዋል። እንዲያውም ከ17 እስከ 70 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 65 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከአውሮፓ ተነስተው ብዙ ሰባኪዎች ወደሚያስፈልጉባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ማለትም ወደ ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኒጀርና ቶጎ ተዛውረዋል። * እንዲህ ያለ ትልቅ እርምጃ እንዲወስዱ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? እዚያስ ምን አጋጠማቸው?

ከዴንማርክ የመጣችው አነ-ራከል እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “ወላጆቼ በሴኔጋል ሚስዮናውያን ሆነው አገልግለዋል። የሚስዮናዊነት ሕይወት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ በየጊዜው ያወሩ ስለነበር እኔም ይህን ሕይወት መቅመስ ፈለግኩ።” አነ-ራከል ከ15 ዓመት ገደማ በፊት በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ በነበረችበት ወቅት ወደ ቶጎ ተዛውራ በምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ ማገልገል ጀመረች። እንዲህ ማድረጓ ሌሎችን ያበረታታው እንዴት ነው? “ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ታናሽ እህቴና ወንድሜ እኔ ወዳለሁበት ወደ ቶጎ መጡ” በማለት ተናግራለች።

አልቤር-ፌኤት እና ኦሬል

 በፈረንሳይ የሚኖሩትና ባለትዳር የሆኑት የ70 ዓመቱ ኦሬል እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “ከአምስት ዓመት በፊት ጡረታ ስወጣ በፊቴ ሁለት ምርጫ ተደቅኖ ነበር፦ አንዱ በፈረንሳይ የተረጋጋ ሕይወት እየመራሁ ገነትን መጠባበቅ ሲሆን ሌላው ደግሞ አገልግሎቴን ለማስፋት የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰድ ነበር።” ኦሬል አገልግሎታቸውን ለማስፋት ወሰኑ። ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት እሳቸውና ባለቤታቸው አልቤር-ፌኤት ወደ ቤኒን ተዛወሩ። ኦሬል “ይሖዋን ለማገልገል ራሳችንን ማቅረባችንና ወደዚህ መምጣታችን እስከ ዛሬ ካደረግነው ነገር ሁሉ የተሻለ ውሳኔ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “ደግሞም በባሕሩ ዳርቻ የሚገኘው የአገልግሎት ክልላችን ራሱ ገነት ይመስላል” በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ክሎዶሚር እና ባለቤቱ ሊስያን ከፈረንሳይ ወደ ቤኒን የተዛወሩት ከ16 ዓመት በፊት ነበር። መጀመሪያ ላይ በፈረንሳይ ያሉትን ቤተሰቦቻቸውንና ጓደኞቻቸውን በጣም ይናፍቁ ነበር፤ በተጨማሪም አዲሱን ሕይወት መልመድ እንደሚችሉ አልተሰማቸውም ነበር። ይሁንና ሁኔታው እንደፈሩት አልነበረም። ይልቁንም እጅግ አስደሳች ሆኖላቸዋል። ክሎዶሚር “ላለፉት 16 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ አንድ ሰው እውነትን እንዲማር የመርዳት መብት አግኝተናል” በማለት ተናግሯል።

ሊስያን እና ክሎዶሚር እውነትን እንዲያውቁ ከረዷቸው የተወሰኑ ወንድሞች ጋር

ዦኣና እና ሴባስትያን

ሴባስትያን እና ባለቤቱ ዦኣና ከፈረንሳይ ወደ ቤኒን የተዛወሩት በ2010 ነበር። ሴባስትያን “በጉባኤ ውስጥ ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ። እዚህ ማገልገል ፈጣን የሆነ ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና የመውሰድ ያህል ነው!” ብሏል። በአገልግሎት የሚያገኟቸው ሰዎች ምላሽ ምን ይመስላል? ዦኣና እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች እውነትን የማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። አገልግሎት ላይ በማንሆንበት ጊዜም እንኳ በመንገድ ላይ የሚያገኙን ሰዎች አስቁመው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን የሚያቀርቡልን ከመሆኑም ሌላ ጽሑፍ እንድንሰጣቸው ይጠይቁናል።” ወደ ቤኒን መሄዳቸው በትዳራቸው ላይ ያመጣው ለውጥ አለ? ሴባስትያን “ትዳራችንን አጠናክሮልናል። ከባለቤቴ ጋር ቀኑን ሙሉ በአገልግሎት ማሳለፍ በጣም አስደሳች ነው” ብሏል።

ኤሪክ እና ባለቤቱ ካቲ ብዙ ሕዝብ በማይኖርበት በሰሜናዊ ቤኒን በአቅኚነት ያገለግላሉ። ከአሥር ዓመት ገደማ በፊት በፈረንሳይ እያሉ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ስለማገልገል የሚያወሱ ርዕሶችን ማንበብና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ማማከር ጀመሩ። እንዲህ ማድረጋቸው ወደ ሌላ አገር ተዛውረው የማገልገል ፍላጎት አሳደረባቸው፤ ከዚያም በ2005 ወደ ቤኒን ተዛወሩ። የተመለከቱት እድገት በጣም አስደናቂ ነው። ኤሪክ እንዲህ ብሏል፦ “ከሁለት ዓመት በፊት ታንጊኤታ በምትባለው ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቡድን 9 አስፋፊዎች ብቻ የነበሩት ሲሆን አሁን ግን 30 ደርሰዋል። እሁድ በምናደርገው ስብሰባ ላይ ከ50 እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች ይገኛሉ። እንዲህ የመሰለ እድገት መመልከት ወደር የሌለው ደስታ ያስገኛል።”

ካቲ እና ኤሪክ

 ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለይቶ ማወቅና መወጣት

ቤንያሚን

ብዙ ሰባኪዎች በሚያስፈልጉበት ቦታ የሚያገለግሉ አንዳንድ ወንጌላውያን ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል? የ33 ዓመቱ ቤንያሚን የአነ-ራከል ወንድም ነው። በ2000 ዴንማርክ ውስጥ ከአንድ ሚስዮናዊ ጋር ተገናኝቶ የነበረ ሲሆን ይህ ሚስዮናዊ በቶጎ አገልግሏል። ቤንያሚን እንዲህ ብሏል፦ “አቅኚ መሆን እንደምፈልግ ለሚስዮናዊው ስነግረው ‘ወደ ቶጎ ተዛውረህ በአቅኚነት ማገልገል ትችላለህ’ አለኝ።” ቤንያሚን በጉዳዩ ላይ አሰበበት። “በወቅቱ ገና 20 ዓመት አልሞላኝም ነበር፤ ሆኖም ሁለቱ እህቶቼ በቶጎ እያገለገሉ ነበር። ይህም ወደዚያ መሄድ እንድችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልኛል” ብሏል። በመሆኑም ወደ ቶጎ ተዛወረ። ያም ሆኖ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። ቤንያሚን እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ፈረንሳይኛ የሚባል ነገር ጨርሶ አላውቅም ነበር። ከሰዎች ጋር መግባባት ባለመቻሌ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በጣም ተቸግሬ ነበር።” በጊዜ ሂደት ግን ቋንቋውን ቻለ። በአሁኑ ወቅት ቤንያሚን በቤኒን ቤቴል ውስጥ እያገለገለ ሲሆን ጽሑፎችን የሚያደርስ ከመሆኑም ሌላ በኮምፒውተር ክፍል ይሠራል።

ማሪ-አንዬስ እና ሚሼል

ቀደም ሲል የተጠቀሱት ኤሪክ እና ካቲ ወደ ቤኒን ከመዛወራቸው በፊት በፈረንሳይ የውጭ አገር ቋንቋ በሚነገርበት ጉባኤ ውስጥ ያገለግሉ ነበር። ይሁንና በምዕራብ አፍሪካ ምን የተለየ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል? ካቲ “ጥሩ መኖሪያ ቤት ማግኘት ቀላል አልነበረም። ለብዙ ወራት መብራትና ውኃ በሌለው ቤት ውስጥ ኖረናል” በማለት ተናግራለች። ኤሪክ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በአካባቢያችን የሚሰማው ኃይለኛ የሙዚቃ ድምፅ እስከ ሌሊት ድረስ ይጮኽብን ነበር። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን በትዕግሥት ማሳለፍና ተቀብሎ መኖር መቻል አስፈላጊ ነው።” ሁለቱም “ባልተነካ ክልል ውስጥ ማገልገል የሚያስገኘው ደስታ ማንኛውንም ዓይነት ችግር ያስረሳል” ሲሉ ተናግረዋል።

በ50ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኙ ሚሼል እና ማሪ-አንዬስ የተባሉ ባልና ሚስት ከፈረንሳይ ወደ ቤኒን የመጡት ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት ነበር። መጀመሪያ ላይ ሁኔታው አስጨንቋቸው ነበር። ሚሼል እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዶች የወሰድነውን እርምጃ በተወጠረ ገመድ ላይ ጋሪ እየገፋ ከሚሄድ ሰው ጋር ያመሳሰሉት ሲሆን በጋሪው ላይ የተቀመጥን ያህል ሆኖ ተሰምቷቸዋል! በተወጠረው ገመድ ላይ ጋሪውን የሚገፋው ይሖዋ መሆኑን ባናውቅ ኖሮ በፍርሃት እንዋጥ ነበር። በመሆኑም ወደዚያ የሄድነው ለይሖዋ ብለንና ከይሖዋ ጋር ሆነን ነበር።”

ቅድመ ዝግጅት ማድረግ

ብዙ ሰባኪዎች በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች የማገልገል ልምድ ያላቸው ወንድሞች የሚከተሉትን እርምጃዎች በመውሰድ ራስን ማዘጋጀት ያለውን ጠቀሜታ አበክረው ይገልጻሉ፦ አስቀድሞ ዕቅድ ማውጣት። ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር መላመድ። ያወጡትን ባጀት ተከትሎ መኖር። በይሖዋ መታመን።—ሉቃስ 14:28-30

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሴባስትያን እንዲህ ብሏል፦ “ወደዚህ ከመዛወራችን በፊት እኔና ዦኣና ለመዝናናት የምናወጣውን ወጪ በመቀነስና የማያስፈልጉንን ነገሮች ከመግዛት በመቆጠብ ለሁለት ዓመት ገንዘብ አጠራቅመናል።” ከአገራቸው ውጭ  ማገልገላቸውን መቀጠል እንዲችሉ በየዓመቱ ወደ አውሮፓ ተመልሰው ለጥቂት ወራት ይሠራሉ፤ ይህን ማድረጋቸው በቀሩት ወራት በቤኒን በአቅኚነት ለማገልገል ያስችላቸዋል።

ማሪ-ቴሬዝ

ማሪ-ቴሬዝ በምዕራብ አፍሪካ ብዙ ሰባኪዎች በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ከሚያገለግሉ ወደ 20 የሚጠጉ ነጠላ እህቶች መካከል አንዷ ነች። በፈረንሳይ የአውቶቡስ ሾፌር ሆኖ ትሠራ ነበር፤ ይሁንና በ2006 በኒጀር አቅኚ ሆና ለማገልገል የአንድ ዓመት እረፍት ወሰደች። ለእሷ አርኪ የሆነው ሕይወት ይህ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀባትም። ማሪ-ቴሬዝ እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ፈረንሳይ ተመልሼ የሥራ ፕሮግራሜ እንዲስተካከልልኝ እንደምፈልግ ለአሠሪዬ ነገርኩት፤ እሱም ፈቃደኛ ሆነ። ከግንቦት እስከ ነሐሴ ድረስ በፈረንሳይ የአውቶቡስ ሾፌር ሆኜ እሠራለሁ፤ ከመስከረም እስከ ሚያዝያ ደግሞ በኒጀር አቅኚ ሆኜ አገለግላለሁ።”

ሳፊራ

‘አስቀድመው የአምላክን መንግሥት የሚፈልጉ’ ሁሉ ይሖዋ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሙሉ እንደሚሰጣቸው መተማመን ይችላሉ። (ማቴ. 6:33) በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የምትገኘው ሳፊራ የተባለች ነጠላ እህት ከፈረንሳይ ወደ ቤኒን በመዛወር አቅኚ ሆና ስታገለግል ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። በ2011 በአፍሪካ ለሌላ ተጨማሪ ዓመት (ለስድስተኛ ጊዜ) ለማገልገል የሚያስችላትን ገንዘብ ሠርታ ለማግኘት ወደ ፈረንሳይ ተመልሳ ነበር። ሳፊራ እንዲህ ብላለች፦ “ዕለቱ ዓርብ ሲሆን ሥራ የምገባበት የመጨረሻ ቀን ነበር፤ ይሁንና ለቀጣዩ ዓመት በቂ ገንዘብ ለማግኘት ተጨማሪ አሥር ቀናት መሥራት ያስፈልገኝ ነበር። ወደ ቤኒን ለመመለስ የቀረኝ ጊዜ ደግሞ ሁለት ሳምንት ብቻ ነበር። ሁኔታውን ግልጽልጽ አድርጌ በመንገር ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ብዙም ሳይቆይ፣ ሥራ የሚያስቀጥር አንድ ድርጅት ደውሎ ሰው ተክቼ ለሁለት ሳምንት መሥራት እችል እንደሆነ ጠየቀኝ።” ሰኞ ዕለት ሳፊራ በምትተካት ሴት አማካኝነት ሥልጠና ለማግኘት ወደ ሥራ ቦታው ሄደች። እንዲህ ብላለች፦ “የምተካት ሴት በአቅኚዎች የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመካፈል አሥር ቀን እረፍት መውጣት የምትፈልግ እህት መሆኗን ሳውቅ በጣም ገረመኝ! አለቃዋ የሚተካት ሰው ካልተገኘ እረፍት እንደማይሰጣት ነግሯት ነበር። እሷም እንደ እኔው ይሖዋ እንዲረዳት አጥብቃ ጸልያ ነበር።”

የእውነተኛ እርካታ ምንጭ

አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በምዕራብ አፍሪካ ለበርካታ ዓመታት ከማገልገላቸው የተነሳ አገራቸው ሆኗል። ሌሎች ደግሞ ለተወሰኑ ዓመታት አገልግለው ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰዋል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰባኪዎች በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ያገለገሉት እነዚህ ክርስቲያኖች ይህን ማድረጋቸው ዛሬም ቢሆን ጥቅም እያስገኘላቸው ነው። እውነተኛ እርካታ ማግኘት የሚቻለው ይሖዋን በማገልገል እንደሆነ ተገንዝበዋል።

^ አን.6 ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በሆኑት በአራቱም አገሮች ያለውን ሥራ በበላይነት የሚከታተለው የቤኒን ቅርንጫፍ ቢሮ ነው።