በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?”

“ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?”

“ጌታው በአገልጋዮቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?”—ማቴ. 24:45

1, 2. ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ እየመገበን ያለው በማን በኩል ነው? ይህን ማወቃችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

“ወንድሞች፣ በጣም የሚያስፈልገኝን ጽሑፍ ልክ በምፈልገው ሰዓት ላይ ያወጣችሁባቸውን አጋጣሚዎች ቆጥሬ ልጨርሳቸው አልችልም።” አንዲት እህት በዋናው መሥሪያ ቤት ለሚያገለግሉ ወንድሞች ያላትን አድናቆት በደብዳቤ የገለጸችው በዚህ መንገድ ነበር። አንተስ የእሷን ስሜት ትጋራለህ? ብዙዎቻችን እንደዚያ ይሰማናል። ታዲያ እንዲህ ቢሰማን የሚገርም ነው? በፍጹም።

2 ወቅታዊ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘታችን የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ እኛን ለመመገብ የገባውን ቃል እየጠበቀ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ለመሆኑ ኢየሱስ ይህን እያደረገ ያለው በማን በኩል ነው? የእሱን መገኘት የሚጠቁመውን ምልክት በተናገረበት ወቅት ‘በተገቢው ጊዜ ላይ ለአገልጋዮቹ ምግባቸውን ለመስጠት’ የሚጠቀመው ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ እንደሚሆን ገልጾ ነበር። * (ማቴዎስ 24:45-47ን አንብብ።) በዚህ የመጨረሻ ዘመን ላይ ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹን ለመመገብ የሚጠቀመው በዚህ ታማኝ ባሪያ አማካኝነት ነው። በመሆኑም የዚህን ባሪያ ማንነት ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። መንፈሳዊ ጤንነታችንም ሆነ ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና የተመካው በዚህ ባሪያ አማካኝነት የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ በመመገባችን ላይ ነው።—ማቴ. 4:4፤ ዮሐ. 17:3

3. ቀደም ሲል በጽሑፎቻችን ላይ ስለ ታማኙ ባሪያ የሚናገረውን ምሳሌ አስመልክቶ የሚሰጠው ማብራሪያ ምን ነበር?

3 ኢየሱስ ስለ ታማኙ ባሪያ የተናገረውን ምሳሌ መረዳት ያለብን እንዴት ነው? ቀደም ሲል በጽሑፎቻችን ላይ ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጠው ማብራሪያ የሚከተለው ነበር፦ በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት ኢየሱስ በአገልጋዮቹ ላይ ታማኝና ልባም ባሪያ ሾመ። ባሪያው፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በየትኛውም ዘመን በምድር ላይ የኖሩትን ሁሉንም ቅቡዓን ክርስቲያኖች በቡድን ደረጃ ያመለክታል። አገልጋዮቹ ደግሞ ቅቡዓኑን ራሳቸውን በግለሰብ ደረጃ ያመለክታሉ። ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ “በንብረቱ ሁሉ ላይ” ይኸውም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን በሙሉ እንዲያስተዳድር በ1919 ሾሞታል ተብሎ ይታመን ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ጥናት ብሎም በጸሎት የታገዘ ማሰላሰል ከተደረገ በኋላ ኢየሱስ ስለ ታማኝና ልባም ባሪያ የተናገረውን ምሳሌ የተረዳንበት መንገድ ማስተካከያ እንደሚያስፈልገው መገንዘብ ችለናል። (ምሳሌ 4:18) ተስፋችን በሰማይም  ይሁን በምድር ምሳሌው እኛን የሚመለከተው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ እስቲ ይህን ጉዳይ እንመርምር።

ምሳሌው ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው?

4-6. ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ አስመልክቶ የተናገረው ምሳሌ ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው ከ1914 ወዲህ መሆን አለበት ብለን የምንደመድመው ለምንድን ነው?

4 ስለ ታማኝና ልባም ባሪያ ከሚናገረው ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያመለክተው ምሳሌው ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ዕለት ሳይሆን በዚህ የመጨረሻ ዘመን ላይ ነው። እስቲ ቅዱሳን መጻሕፍት ወደዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

5 ኢየሱስ ስለ ታማኙ ባሪያ የተናገረው ምሳሌ፣ ከእሱ ‘መገኘትና ከዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት’ ጋር በተያያዘ የተናገረው ትንቢት ክፍል ነው። (ማቴ. 24:3) በማቴዎስ 24:4-22 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የዚህ ትንቢት የመጀመሪያ ክፍል ሁለት ፍጻሜዎች አሉት፤ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው ከ33 ዓ.ም. እስከ 70 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ሲሆን በላቀ ሁኔታ ሁለተኛ ፍጻሜውን ያገኘው ደግሞ በእኛ ዘመን ነው። ታዲያ ኢየሱስ ስለ ታማኙ ባሪያ የተናገረው ምሳሌም ሁለት ፍጻሜ ይኖረዋል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም።

6 ከማቴዎስ 24:29 ጀምሮ ያሉትን ሐሳቦች ስንመለከት ኢየሱስ በዋነኝነት ያተኮረው በእኛ ዘመን በሚፈጸሙ ክንውኖች ላይ መሆኑን እናስተውላለን። (ማቴዎስ 24:30, 42, 44ን አንብብ።) በታላቁ መከራ ወቅት ስለሚፈጸመው ነገር ሲናገር የሰው ልጅ “በሰማይ ደመና ሲመጣ” እንደሚታይ ገልጿል። ከዚያም ነቅቶ የመጠበቅን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ሲጠቅስ “ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ” እንዲሁም “የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ” የሚሉ አባባሎችን ተጠቅሟል። * እነዚህ አባባሎች ይበልጥ ትርጉም የሚሰጡት በመጨረሻዎቹ ቀናት ለሚኖሩ ሰዎች ነው። ኢየሱስ ስለ ታማኝና ልባም ባሪያ የሚገልጸውን ምሳሌ የተናገረው ከዚህ ርዕስ ሳይወጣ ማለትም በመጨረሻዎቹ ቀናት ስለሚፈጸሙት ክንውኖች እየተናገረ ሳለ ነው። በመሆኑም ታማኙን ባሪያ አስመልክቶ የተናገረው ምሳሌ ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው ከ1914 ወዲህ ማለትም የመጨረሻዎቹ ቀናት ከጀመሩ በኋላ ነው ብለን መደምደም እንችላለን። እንዲህ ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

7. የመከሩ ወቅት ሲጀምር ምን ወሳኝ ጥያቄ ተነሳ? ለምንስ?

7 “ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?” የሚለውን ጥያቄ እስቲ ለአንድ አፍታ አስበው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ላይ እንዲህ ያለ ጥያቄ ለማንሳት የሚያበቃ ምንም ምክንያት አልነበረም። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ሐዋርያት መለኮታዊ ድጋፍ እንዳላቸው ለማረጋገጥ ተአምራትን መፈጸም አልፎ ተርፎም ተአምራዊ ስጦታዎችን ለሌሎች ማስተላለፍ ይችሉ ነበር። (ሥራ 5:12) ታዲያ አንድ ሰው ‘ክርስቶስ አመራር እንዲሰጥ የሾመው ማንን ነው?’ የሚል ጥያቄ የሚያነሳበት ምን ምክንያት ይኖራል? በ1914 ግን ሁኔታው በጣም የተለየ ነበር። የመከሩ ወቅት የጀመረው በዚህ ዓመት ነው። እንክርዳዱ ከስንዴው የሚለይበት ጊዜም ደርሶ ነበር። (ማቴ. 13:36-43) በመሆኑም የመከሩ ወቅት ሲጀምር አንድ ወሳኝ ጥያቄ ተነሳ፦ ብዙ አስመሳይ ክርስቲያኖች የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች እንደሆኑ በሚናገሩበት በዚያ ጊዜ ስንዴውን ማለትም ቅቡዓን ክርስቲያኖችን መለየት የሚቻለው እንዴት ነው? ስለ ታማኙ ባሪያ የሚናገረው ምሳሌ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። በምሳሌው መሠረት የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች በዚያን ወቅት በመንፈሳዊ በደንብ የሚመገቡት ናቸው።

ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?

8. ታማኙ ባሪያ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች የተውጣጣ ነው ብሎ ማሰቡ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

8 ታማኙ ባሪያ በምድር ላይ ካሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተውጣጣ መሆን አለበት። እነዚህ ክርስቲያኖች “ንጉሣዊ ካህናት” ተብለው የተጠሩ ከመሆኑም ሌላ “ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ” የጠራቸውን የአምላክን “ድንቅ ባሕርያት” በስፋት የማስታወቅ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥ. 2:9) የዚህ “ንጉሣዊ ካህናት” አባላት ለእምነት ባልንጀሮቻቸው እውነትን በማስተማር ረገድ ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኖራቸዋል ብሎ ማሰቡ ተገቢ ነው።—ሚል. 2:7፤ ራእይ 12:17

9. የታማኙ ባሪያ ክፍል የሆኑት ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው? አብራራ።

9 ታዲያ የታማኙ ባሪያ ክፍል የሚሆኑት በምድር ላይ ያሉ ሁሉም ቅቡዓን ናቸው? እንደዚያ ማለት  አይደለም። እውነታው እንደሚያሳየው በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቻቸው መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ ሚና ያላቸው ሁሉም ቅቡዓን አይደሉም። ከስንዴው መካከል፣ በጉባኤያቸው ውስጥ በአገልጋይነት ወይም በሽምግልና የሚሠሩ ቅቡዓን ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ወንድሞች ከቤት ወደ ቤትም ሆነ በጉባኤያቸው ውስጥ ያስተምራሉ፤ እንዲሁም ከዋናው መሥሪያ ቤት የሚመጣውን መመሪያ በታማኝነት ይደግፋሉ። ይሁንና ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር መንፈሳዊ ምግብ በማቅረቡ ሥራ አይካፈሉም። በተጨማሪም ከቅቡዓኑ መካከል ትሑት የሆኑ እህቶች ይገኙበታል፤ እነዚህ እህቶች በጉባኤ ላይ ማስተማር ይቅርና እንዲህ የማድረግ ሐሳቡም እንኳ የላቸውም።—1 ቆሮ. 11:3፤ 14:34

10. ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?

10 ታዲያ ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን መመገብ የሚለውን ኢየሱስ የተጠቀመበትን መንገድ በአእምሯችን ከያዝን ይህ ባሪያ በክርስቶስ መገኘት ወቅት መንፈሳዊ ምግብ በማዘጋጀትና በማቅረቡ ሥራ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚኖራቸውን ጥቂት ቁጥር ያላቸው የተቀቡ ወንድሞች ያቀፈ እንደሚሆን እንጠብቃለን። የመጨረሻዎቹ ቀናት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ታማኙን ባሪያ የሚያስገኙት እነዚህ የተቀቡ ወንድሞች በዋናው መሥሪያ ቤት በመሆን በኅብረት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል፣ ይህ ባሪያ እንደሆነ ተደርጎ ሲገለጽ ቆይቷል። ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው “ባሪያ” የሚለው ቃል ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎችን እንዳቀፈ ግልጽ ቢሆንም እዚህ ላይ የገለጸበት መንገድ እንደ አንድ ባሪያ አድርጎ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። በመሆኑም የበላይ አካል አባላት ውሳኔ የሚያደርጉት በጋራ ሆነው ነው።

አገልጋዮቹ እነማን ናቸው?

11, 12. (ሀ) ታማኝና ልባም ባሪያ የትኞቹን ሁለት ሹመቶች ይቀበላል? (ለ) ኢየሱስ ታማኝና ልባም ባሪያን በአገልጋዮቹ ላይ የሾመው መቼ ነው? ታማኝና ልባም ባሪያ እንዲሆን የመረጠውስ ማንን ነው?

11 ኢየሱስ፣ በምሳሌው ላይ ታማኝና ልባም ባሪያ ሁለት የተለያዩ ሹመቶችን እንደሚቀበል መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው። የመጀመሪያውን ሹመት የሚያገኘው በአገልጋዮቹ ላይ ሲሆን ሁለተኛውን ሹመት የሚያገኘው ደግሞ በጌታው ንብረቶች ሁሉ ላይ ነው። ምሳሌው ፍጻሜውን የሚያገኘው በዚህ ዘመን መደምደሚያ ላይ በመሆኑ ሁለቱንም ሹመቶች የሚያገኘው ኢየሱስ በ1914 በሥልጣኑ ላይ ከተገኘ በኋላ መሆን አለበት።

12 ታዲያ ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ በአገልጋዮቹ ላይ የሾመው መቼ ነው? ይህን ለማወቅ የመከሩ ወቅት ወደጀመረበት ወደ 1914 መለስ ማለት ይኖርብናል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በዚያ ወቅት ብዙ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ክርስቲያን እንደሆኑ ይናገሩ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ የሚመርጠውና የሚሾመው  ከየትኛው ቡድን ይሆን? ይህ ጥያቄ መልስ ያገኘው እሱና አባቱ ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ ባለው ጊዜ ውስጥ ቤተ መቅደሱን ይኸውም ለአምልኮ የተደረገውን መንፈሳዊ ዝግጅት ለመመርመር ከመጡ በኋላ ነው። * (ሚል. 3:1) በዚህ ወቅት አነስተኛ ቁጥር ያለውና ታማኝ የሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን አገኙ፤ የዚህ ቡድን አባላት ልባቸው ያረፈው በይሖዋና በቃሉ ላይ በመሆኑ ኢየሱስም ሆነ አባቱ ተደስተውባቸው ነበር። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ክርስቲያኖች በተወሰነ መጠን መንጻት ያስፈልጋቸው ነበር፤ ያም ሆኖ ለአጭር ጊዜ በቆየው የፈተናና የማጥራት ወቅት ትሑት በመሆን ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። (ሚል. 3:2-4) እነዚህ ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በስንዴ የተመሰሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን አሳይተዋል። በመንፈሳዊ የማንሰራራት ጊዜ ላይ ማለትም በ1919 ኢየሱስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መካከል ብቃት ያላቸውን ቅቡዓን ወንድሞች ታማኝና ልባም ባሪያ አድርጎ በመምረጥ በአገልጋዮቹ ላይ ሾማቸው።

13. አገልጋዮች ከተባሉት መካከል እነማን ይገኙበታል? ለምንስ?

13 አገልጋይ የተባሉትስ እነማን ናቸው? በአጭሩ ለመመለስ አገልጋይ የተባሉት የሚቀርበውን ምግብ የሚመገቡት ናቸው። የመጨረሻዎቹ ቀናት በጀመሩበት ወቅት ሁሉም አገልጋዮች ቅቡዓን ነበሩ። በኋላ ላይ ግን የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብም ከአገልጋዮቹ መካከል ተካተቱ። ሌሎች በጎችም ሆኑ ቅቡዓን በክርስቶስ አመራር ሥር ባለው “አንድ መንጋ” ውስጥ የተጠቃለሉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከሁለቱ ቡድኖች ትልቁን ቁጥር የያዙት ሌሎች በጎች ናቸው። (ዮሐ. 10:16) ታማኙ ባሪያ ለሁለቱም ቡድኖች የሚያዘጋጀው ወቅታዊ መንፈሳዊ ምግብ አንድ ዓይነት ሲሆን ሁለቱም ከሚቀርብላቸው ማዕድ ይጠቀማሉ። በአንድነት ታማኝና ልባም ባሪያ ተብለው ስለሚጠሩት የበላይ አካል አባላትስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱም ቢሆኑ መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም እንደተቀሩት እውነተኛ የኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ እነሱም በግለሰብ ደረጃ አገልጋዮች መሆናቸውን በትሕትና አምነው ይቀበላሉ።

ተስፋችን በሰማይም ይሁን በምድር ሁላችንም አገልጋዮች ነን፤ እንዲሁም ወቅታዊ የሆነ አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገናል

14. (ሀ) ታማኙ ባሪያ ምን ኃላፊነት ተጥሎበታል? ኃላፊነቱስ ምን ነገሮችን ያካትታል? (ለ) ኢየሱስ ለታማኝና ልባም ባሪያ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? (“ያ ባሪያ ክፉ ቢሆን . . .” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

14 ኢየሱስ ለታማኝና ልባም ባሪያ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቶታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እምነት የሚጣልበት ባሪያ ወይም መጋቢ የቤት አስተዳዳሪ ተደርጎ ይሾም ነበር። (ሉቃስ 12:42) በመሆኑም ታማኝና ልባም ባሪያ የእምነት ቤተሰቡን እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ይህ ኃላፊነት ቁሳዊ ንብረቶችን፣ የስብከቱን ሥራ፣ የትላልቅ ስብሰባ ፕሮግራሞችን እንዲሁም ለመስክ አገልግሎት፣ ለግልና ለጉባኤ የሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የማዘጋጀቱን ሥራ በበላይነት መከታተልን ይጨምራል። አገልጋዮቹ ባሪያው በኅብረት የሚያቀርባቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች በሙሉ ያስፈልጓቸዋል።

 በጌታው ንብረት ሁሉ ላይ የሚሾመው መቼ ነው?

15, 16. ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ በንብረቱ ሁሉ ላይ የሚሾመው መቼ ነው?

15 ኢየሱስ ለባሪያው ሁለተኛውን ኃላፊነት የሚሰጠው ማለትም “በንብረቱ ሁሉ ላይ” የሚሾመው መቼ ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ጌታው ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው! እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” (ማቴ. 24:46, 47) ኢየሱስ ሁለተኛውን ሹመት የሚሰጠው ተመልሶ በሚመጣበትና ባሪያው “እንዲህ ሲያደርግ” ማለትም በታማኝነት መንፈሳዊ ምግብ ሲያቀርብ በሚያገኘው ጊዜ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ስለዚህ በሁለቱ ሹመቶች መካከል የተወሰነ ጊዜ እንደሚያልፍ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ባሪያውን በንብረቱ ሁሉ ላይ የሚሾመው እንዴትና መቼ እንደሆነ ለመረዳት ሁለት ነገሮችን ይኸውም ጌታው የሚመጣበትን ጊዜና ንብረቱ የሚያካትተውን ነገር ማወቅ ይኖርብናል።

16 ታዲያ ኢየሱስ የሚመጣው መቼ ነው? የጥቅሱን አውድ በመመልከት መልሱን ማወቅ ይቻላል። ከዚህ በፊት ባሉት ጥቅሶች ላይም ስለ ኢየሱስ ‘መምጣት’ ተጠቅሶ እንደነበረ ማስታወስ ይኖርብናል፤ ‘መምጣት’ የሚለው ቃል የሚያመለክተው ኢየሱስ በሥርዓቱ ፍጻሜ ላይ ፍርድ ለመስጠትና ፍርዱን ለማስፈጸም የሚመጣበትን ጊዜ ነው። * (ማቴ. 24:30, 42, 44) በመሆኑም ስለ ታማኙ ባሪያ በሚናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው የኢየሱስ ‘መምጣት’ የሚፈጸመው በታላቁ መከራ ወቅት ነው።

17. የኢየሱስ ንብረት ምን ነገር ያካትታል?

17 ‘የኢየሱስ ንብረት ሁሉ’ ሲባል ምን ነገር ያካትታል? ኢየሱስ “ሁሉ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት መንገድ ንብረቱ በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ብቻ እንደሚያመለክት የሚያሳይ አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ በሰማይ ከፍተኛ ሥልጣን አለው። “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ብሏል። (ማቴ. 28:18፤ ኤፌ. 1:20-23) በአሁኑ ጊዜ ከንብረቱ መካከል መሲሐዊው መንግሥት ይገኝበታል፤ ይህ መንግሥት የእሱ ንብረት የሆነው ከ1914 ጀምሮ ሲሆን ይህን ሥልጣኑን ለቅቡዓን ተከታዮቹ ያጋራል።—ራእይ 11:15

18. ኢየሱስ በጣም በመደሰት ባሪያውን በንብረቱ ሁሉ ላይ የሚሾመው ለምንድን ነው?

 18 ከላይ ከተመለከትናቸው ሐሳቦች አንጻር ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? ኢየሱስ በታላቁ መከራ ወቅት ለፍርድ ሲመጣ ታማኙ ባሪያ ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ለአገልጋዮቹ በታማኝነት ሲያቀርብ ያገኘዋል። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በጣም ስለሚደሰት ለዚህ ባሪያ ሁለተኛውን ኃላፊነት ይሰጠዋል፤ በሌላ አባባል በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። የታማኝና ልባም ባሪያ አባላት ይህ ሹመት የሚሰጣቸው ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች በመሆን በሰማይ ሽልማታቸውን ሲቀበሉ ነው።

19. ታማኙ ባሪያ በሰማይ ከተቀሩት ቅቡዓን የበለጠ ሽልማት ያገኛል? አብራራ።

19 ታዲያ እንዲህ ሲባል ታማኙ ባሪያ በሰማይ ከተቀሩት ቅቡዓን የበለጠ ሽልማት ይቀበላል ማለት ነው? በፍጹም። አነስተኛ ቁጥር ያለው አንድ ቡድን ሽልማት እንደሚሰጠው በሆነ ወቅት ላይ ቃል ቢገባለትም ሽልማቱ ሲሰጥ ግን ሌሎችም የሚካተቱበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለ11ዱ ታማኝ ሐዋርያት ምን እንዳላቸው እንመልከት። (ሉቃስ 22:28-30ን አንብብ።) ኢየሱስ ጥቂት ወንዶችን ያቀፈው ይህ ቡድን ላሳየው ታማኝነት ሽልማት እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል። የዚህ ቡድን አባላት ከክርስቶስ ጋር በመሆን አብረው ይገዛሉ። ይሁን እንጂ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ሁሉም የ144,000 አባላት ዙፋን ላይ ተቀምጠው አብረውት እንደሚገዙ ተናግሯል። (ራእይ 1:1፤ 3:21) በተመሳሳይም በማቴዎስ 24:47 ላይ እንደተገለጸው ታማኙን ባሪያ ያስገኙትን በመንፈስ የተቀቡ ጥቂት ወንድሞችን ያቀፈውን ቡድን በንብረቱ ሁሉ ላይ እንደሚሾመው ኢየሱስ ቃል ገብቷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በሰማይ ከፍተኛ ሥልጣን የሚያገኙት ሁሉም የ144,000 አባላት ናቸው።—ራእይ 20:4, 6

ሁሉም የ144,000 አባላት ኢየሱስ በሰማይ ያለውን ከፍተኛ ሥልጣን ይጋራሉ (አንቀጽ 19ን ተመልከት)

20. ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ የሾመው ለምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

20 ኢየሱስ በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብ ማቅረቡ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይጠቀምበት የነበረውን መንገድ እየተከተለ እንደሆነ ይኸውም በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን እየመገበ እንዳለ ያሳያል። ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ የሾመው ቅቡዓን ወይም ሌሎች በጎች ሳይል ለሁሉም እውነተኛ ተከታዮቹ የመጨረሻዎቹ ቀናት እስኪፈጸሙ ድረስ ወቅታዊ መንፈሳዊ ምግብ በቋሚነት እንዲያቀርብ ነው። በመሆኑም ሁላችንም ታማኝና ልባም ባሪያን ያስገኙትን ቅቡዓን ወንድሞቻችንን በታማኝነት በመደገፍ ኢየሱስ ላደረገልን ዝግጅት ያለንን አድናቆት ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ዕብ. 13:7, 17

 

^ አን.2 አንቀጽ 2፦ ቀደም ሲል ኢየሱስ ተመሳሳይ የሆነ ሌላ ምሳሌ የተናገረ ሲሆን በዚህ ምሳሌ ላይ ‘ባሪያውን’ “መጋቢ” ሲል ጠርቶታል።—ሉቃስ 12:42-44

^ አን.6 አንቀጽ 6፦ የክርስቶስ ‘መምጣት’ (በግሪክኛ ኤርኮማይ) ከእሱ ‘መገኘት’ (ፓሩሲያ) የተለየ ነው። ኢየሱስ በማይታይ ሁኔታ መገኘት የሚጀምረው ለፍርድ ከመምጣቱ በፊት ነው።

^ አን.12 አንቀጽ 12፦ በዚህ እትም ላይ የሚገኘውን “ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚለውን ርዕስ ከአንቀጽ 5-8 ተመልከት።

^ አን.16 አንቀጽ 16፦ በዚህ እትም ላይ የሚገኘውን “ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ ከአንቀጽ 14-18 ተመልከት።