ስለ ይሖዋ ባሕርያት የተሟላ ግንዛቤ ይኑራችሁ
“የተወደዳችሁ ልጆች በመሆን አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ።”—ኤፌ. 5:1
1. (ሀ) አንድ ክርስቲያን ስለ የትኞቹ የይሖዋ ባሕርያት ምርምር ሊያደርግ ይችላል? (ለ) ስለ አምላክ ባሕርያት መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
ስለ ይሖዋ ባሕርያት ስታስብ ቶሎ ወደ አእምሮህ የሚመጡት የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? ብዙዎቻችን መጀመሪያ የምናስበው ፍቅሩን፣ ፍትሑን፣ ጥበቡንና ኃይሉን ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ በርካታ አስደናቂ ባሕርያትን የተላበሰ አምላክ እንደሆነ እንገነዘባለን። እንዲያውም ከ40 የሚበልጡ የተለያዩ ባሕርያቱ በጽሑፎቻችን ላይ ተብራርተዋል። በግል ወይም በቤተሰብ ጥናታችን ወቅት ምርምር ስናደርግ ስለ ይሖዋ ባሕርያት ምን ያህል አስደናቂ ነገሮችን ማወቅ እንደምንችል አስበው! እንዲህ ያለው ጥናት ምን ጥቅም ያስገኝልናል? በሰማይ ስላለው አባታችን ያለንን ግንዛቤ ያሳድግልናል። ስለ እሱ ያለን ግንዛቤ እያደገ በሄደ መጠን ደግሞ ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብና እሱን ለመምሰል እንገፋፋለን።—ኢያሱ 23:8፤ መዝ. 73:28
2. (ሀ) ስለ ይሖዋ ባሕርያት ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (ለ) በዚህና በሚቀጥሉት ርዕሶች ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 ስለ አንድ ነገር “የተሟላ ግንዛቤ ማግኘት” ሲባል ስለዚያ ነገር በሚገባ ማወቅ ማለት ነው። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ እውቀት የሚዳብረው ቀስ በቀስ ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ ከዚህ በፊት በልተነው የማናውቀው አንድ ምግብ መጀመሪያ ሲሸተን ግሩም መዓዛው ያውደን ይሆናል፤ ምግቡን ስናጣጥመው ብሎም ራሳችን ስንሠራው ደግሞ ስለዚያ ምግብ ያለን እውቀት ይጨምራል። በተመሳሳይም ስለ አንድ የይሖዋ ባሕርይ ያለን ግንዛቤ ይበልጥ እያደገ የሚሄደው ስለዚያ ባሕርይ ስንማር፣ በባሕርይው ላይ ስናሰላስል እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ ስናንጸባርቀው ነው። (ኤፌ. 5:1) የዚህና የቀጣዮቹ ሁለት የጥናት ርዕሶች ዓላማ እንደ ዋና ዋናዎቹ የይሖዋ ባሕርያት ትኩረት ስለማናደርግባቸው ሌሎች ባሕርያቱ ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ ነው። ስለ እያንዳንዱ ባሕርይ ስናነሳ የሚከተሉት ሦስት ጥያቄዎች ይብራራሉ፦ ይህ ባሕርይ ምን ማለት ነው? ይሖዋ ይህን ባሕርይ ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ ይህን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ ነው
3, 4. (ሀ) በቀላሉ የሚቀረብ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው? (ለ) ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ መሆኑን ያረጋገጠልን እንዴት ነው?
3 እስቲ በመጀመሪያ፣ በቀላሉ የሚቀረብ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት። በቀላሉ የሚቀረብ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው? ‘ደግ፣ ጊዜውን ለሌሎች ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነና ለማነጋገር የሚቀል’ ብለህ ትመልስ ይሆናል። አንድ ሰው፣ ምንም ቃል ባይናገር እንኳ ሁኔታውን ብቻ በማየት ይኸውም ፊቱ ላይ የሚነበበውን ስሜትና ሌሎች እንቅስቃሴዎቹን በመመልከት በቀላሉ የሚቀረብ ሰው መሆን አለመሆኑን ማወቅ ይቻል ይሆናል።
4 ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? ይሖዋ በጣም ግዙፍ የሆነው አጽናፈ ዓለም ፈጣሪና ሁሉን ቻይ አምላክ ቢሆንም ጸሎታችንን ለመስማትና ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነ እንዲያውም እንዲህ ለማድረግ እንደሚጓጓ አረጋግጦልናል። (መዝሙር 145:18ን እና ኢሳይያስ 30:18, 19ን አንብብ።) አምላክን በየትኛውም ሰዓትና በማንኛውም ቦታ የፈለግነውን ያህል ማነጋገር እንችላለን። ይሖዋ ወደ እሱ በመጸለያችን ፈጽሞ እንደማይነቅፈን ስለምናውቅ ምንም ሳንሳቀቅ እንቀርበዋለን። (መዝ. 65:2፤ ያዕ. 1:5) በአምላክ ቃል ውስጥ ስለ ይሖዋ የተገለጸው የሰው ልጆች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ መሆኑ ይሖዋ እንድንቀርበው እንደሚፈልግ ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙራዊው ዳዊት “የእግዚአብሔር ዐይኖች” ወደ እኛ እንደሆኑ እንዲሁም ‘ቀኝ እጁ ደግፎ እንደሚይዘን’ ጽፏል። (መዝ. 34:15፤ 63:8) ነቢዩ ኢሳይያስ ደግሞ ይሖዋን ከእረኛ ጋር በማመሳሰል “ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በዕቅፉም ይይዛቸዋል” ብሏል። (ኢሳ. 40:11) እስቲ አስበው! ይሖዋ፣ አፍቃሪ በሆነ እረኛ እቅፍ ውስጥ ያለች ግልገል እረኛውን የምትቀርበውን ያህል እኛም እንድንቀርበው ይፈልጋል። በእርግጥም ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብ አባት ነው! ታዲያ በዚህ ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባሕርይ
5. ሽማግሌዎች በቀላሉ የሚቀረቡ መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች “አንድ ሽማግሌ ከሁሉ በላይ እንዲኖረው የምትፈልጉት ባሕርይ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። አብዛኞቹ “በቀላሉ የሚቀረብ” ብለው መልሰዋል። ሁሉም ክርስቲያኖች በቀላሉ የሚቀረቡ ለመሆን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የማይካድ ቢሆንም በተለይ ሽማግሌዎች ይህን ባሕርይ ማዳበራቸው አስፈላጊ ነው። (ኢሳ. 32:1, 2) አንዲት እህት ይህ ባሕርይ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማት ለምን እንደሆነ ስትገልጽ “አንድ ሽማግሌ በቀላሉ የሚቀረብ ካልሆነ ሌሎች ጥሩ ባሕርያት ቢኖሩትም ያን ያህል ጥቅም ማግኘት አንችልም” ብላለች። አንተም እንደዚህች እህት ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድን ሰው በቀላሉ የሚቀረብ የሚያስብለው ምንድን ነው?
6. በቀላሉ የሚቀረቡ ለመሆን ቁልፉ ምንድን ነው?
6 በቀላሉ የሚቀረቡ ለመሆን ቁልፉ ለሌሎች ከልብ የመነጨ አሳቢነት ማሳየት ነው። አንድ ሽማግሌ አሳቢና ሌሎችን ለመርዳት ሲል የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆነ ትናንሽ ልጆችን ጨምሮ ሌሎች የጉባኤው አባላት በቀላሉ ሊቀርቡት እንደሚችሉ መገንዘባቸው አይቀርም። (ማር. 10:13-16) የ12 ዓመቱ ካርሎስ “ወደ መንግሥት አዳራሹ ስንመጣ ሽማግሌዎቹ ሁሌ ፈገግ ብለው ስለሚያናግሩንና ደግ ስለሆኑ ደስ ይሉኛል” ብሏል። እርግጥ ነው፣ አንድ ሽማግሌ በቀላሉ የሚቀረብ እንደሆነ መናገሩ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ይህን ባሕርይ በድርጊቱ ማሳየት አለበት። (1 ዮሐ. 3:18) ታዲያ ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?
7. የአውራጃ ስብሰባ ባጅ ማድረጋችን ብዙውን ጊዜ ውይይት እንዲጀመር በር የሚከፍተው ለምንድን ነው? ከዚህስ ምን ትምህርት እናገኛለን?
7 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ወንድም በሌላ አገር በተካሄደ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ በአውሮፕላን ሲመለስ የስብሰባውን ባጅ አድርጎ ነበር። የአውሮፕላኑ አስተናጋጅ “የአምላክ መንግሥት ይምጣ!” የሚለውን ባጅ ሲመለከት ለወንድም “ኧረ በመጣ!” አለው፤ አክሎም “ስለዚህ ጉዳይ ብንነጋገር ደስ ይለኛል” በማለት ተናገረ። በኋላ ላይ ይህን በተመለከተ የተወያዩ ሲሆን አስተናጋጁ ወንድም የሰጠውን መጽሔቶች በደስታ ተቀበለ። ብዙዎቻችን እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞን ያውቃል። ይሁንና የአውራጃ ስብሰባ ባጅ ማድረጋችን ብዙውን ጊዜ ውይይት እንዲጀመር በር የሚከፍተው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ባጁን ማድረጋችን ሰዎች ቀርበው እንዲያናግሩንና የት እንደምንሄድ ወይም ከየት እንደመጣን እንዲጠይቁን ይጋብዛቸዋል። ባጁ ስለምናምንበት ነገር ከሌሎች ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች እንደሆንን በግልጽ ያሳያል። በተመሳሳይም ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸው እንዲቀርቧቸው እንደሚፈልጉ በግልጽ ማሳየት አለባቸው። ይህን ማሳየት የሚችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
8. ሽማግሌዎች ለሌሎች ከልብ እንደሚያስቡ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋቸው በጉባኤው ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
8 የየአገሩ ባሕል የተለያየ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ሞቅ ባለ ፈገግታ ስንቀበላቸውና ሰላምታ ስንሰጣቸው እንዲሁም ጊዜ ሰጥተን ስናዋራቸው ከልብ እንደምናስብላቸው እያሳየን ነው። በዚህ ረገድ ቅድሚያውን መውሰድ ያለበት ማን ነው? የኢየሱስን ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲገናኝ ምን እንዳደረገ ማቴዎስ ሲዘግብ “ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው” ብሏል። (ማቴ. 28:18) በዛሬው ጊዜም ሽማግሌዎች ቅድሚያውን በመውሰድ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ቀርበው ያነጋግሯቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው በጉባኤው ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? የ88 ዓመት አረጋዊ የሆኑ አንዲት አቅኚ እህት “ወደ መንግሥት አዳራሹ ስመጣ ሽማግሌዎች ሞቅ ባለ ፈገግታ ስለሚቀበሉኝና ስለሚያበረታቱኝ እወዳቸዋለሁ” ብለዋል። አንዲት ሌላ ታማኝ እህት ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “ወደ ስብሰባ ስመጣ አንድ ሽማግሌ ፈገግ ብሎ ሰላም ሲለኝ ደስ ይለኛል፤ ይህ ቀላል ነገር ሊመስል ቢችልም ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው።”
በቀላሉ የሚቀረቡ እና ለሌሎች ጊዜ የሚሰጡ
9, 10. (ሀ) ይሖዋ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል? (ለ) ሽማግሌዎች ለሌሎች ጊዜ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆኑ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
9 ለሌሎች ጊዜያችንን ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆንን ሊቀርቡን እንደማይችሉ የታወቀ ነው። በዚህ ረገድ ይሖዋ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። “እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም።” (ሥራ 17:27) ሽማግሌዎችም ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በፊትና በኋላ ወጣት አረጋዊ ሳይሉ ከሁሉም ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ለመጨዋወት ጊዜ በመመደብ ይህን ማድረግ ይችላሉ። አቅኚ የሆነ አንድ ወንድም “አንድ ሽማግሌ ስለ ደኅንነቴ ሲጠይቀኝና ጊዜ ሰጥቶ ሲያዳምጠኝ ተፈላጊ እንደሆንኩ ይሰማኛል” ብሏል። ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት ይሖዋን ያገለገሉ አንዲት እህት ደግሞ “ሽማግሌዎች ከስብሰባ በኋላ ጊዜ ሰጥተው ሲያናግሩኝ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱኝ ይሰማኛል” በማለት ተናግረዋል።
10 ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሌሎች ኃላፊነቶችም እንዳሏቸው ግልጽ ነው። ያም ቢሆን ግን በስብሰባዎች ወቅት ዋነኛ ግባቸው ለበጎቹ ትኩረት መስጠት ሊሆን ይገባል።
ይሖዋ አያዳላም
11, 12. (ሀ) የማያዳሉ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ይሖዋ የማያዳላ አምላክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?
11 ተወዳጅ ከሆኑት የይሖዋ ባሕርያት መካከል ሌላው ደግሞ የማያዳላ መሆኑ ነው። የማያዳሉ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? አንዱን ከአንዱ አለማበላለጥ፣ ልዩነት አለማድረግ ወይም ወገንተኛ አለመሆን ማለት ነው። የማያዳሉ መሆን ሁለት ነገሮችን ማለትም አመለካከትንና ተግባርን አጣምሮ የያዘ ነው። ሁለቱም ነገሮች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንድ ሰው አመለካከቱ ከአድልዎ ነፃ ካልሆነ ሌሎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ መያዝ አይችልም። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው ‘የማያዳላ’ የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም ‘ፊት የማያይ’ ይኸውም ፊት አይቶ አንዱን ከሌላው የማያበላልጥ የሚል ፍቺ አለው። (ሥራ 10:34፤ ኪንግደም ኢንተርሊንየር) በመሆኑም አድልዎ የማያደርግ ሰው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለሰዎች ውጫዊ ገጽታ ወይም ላሉበት ሁኔታ ሳይሆን ለባሕርያቸው ነው።
12 አድልዎ ባለማድረግ ረገድ ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። ይሖዋ “እንደማያዳላ” ወይም “አድልዎ የማያደርግ” አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35ን እና ዘዳግም 10:17ን አንብብ።) በሙሴ ዘመን የተፈጸመ አንድ ሁኔታ ይህን ሐቅ ያረጋግጣል።
13, 14. (ሀ) አምስቱ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር? (ለ) ይሖዋ የማያዳላ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
13 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በተቃረቡበት ወቅት አምስት ያላገቡ እህትማማቾች አንድ አስቸጋሪ ነገር አጋጠማቸው። ችግሩ ምን ነበር? እነዚህ እህትማማቾች በደንቡ መሠረት እስራኤላውያን የተስፋይቱን ምድር ሲከፋፈሉ እንደ ማንኛውም ቤተሰብ ሁሉ የእነሱ ቤተሰብም ለአባታቸው የተመደበው ርስት ሊደርሰው እንደሚገባ ያውቁ ነበር። (ዘኍ. 26:52-55) ይሁንና ከምናሴ ነገድ የሆነው አባታቸው ሰለጰዓድ በሕይወት አልነበረም። በተለምዶ መሬቱን የመውረስ መብት የነበራቸው የሰለጰዓድ ወንዶች ልጆች ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ሰለጰዓድ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም። (ዘኍ. 26:33) ታዲያ የቤተሰቡ ርስት ሊተላለፍለት የሚችል ወንድ ልጅ ስለሌለ ርስቱ ለዘመዶቻቸው ተሰጥቶ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ባዶ እጃቸውን ይቀራሉ ማለት ነው?
14 አምስቱ እህትማማቾች ወደ ሙሴ ቀርበው “አባታችን ወንድ ልጅ ባለመውለዱ ስሙ ከጐሣዎቹ ተለይቶ እንዴት ይጠፋል? ለእኛም በአባታችን ዘመዶች መካከል ርስት [ይሰጠን]” አሉ። በዚህ ጊዜ ሙሴ ‘እንግዲህ መመሪያው አንድ ነው፤ ምንም ልረዳችሁ አልችልም’ አላቸው? በፍጹም፤ ከዚህ ይልቅ “ጕዳያቸውን ወደ እግዚአብሔር አቀረበ።” (ዘኍ. 27:2-5) ታዲያ ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ? ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የሰለጰዓድ ልጆች ጥያቄ ትክክል ነው፤ በእርግጥ በአባታቸው ዘመዶች መካከል ድርሻቸውን ርስት አድርገህ ልትሰጣቸው ስለሚገባ የአባታቸውን ድርሻ ለእነርሱ አስተላልፍላቸው።” ይሖዋ እንዲህ ዓይነት መመሪያ በመስጠት ብቻ አልተወሰነም። ይህ አሠራር ለሰለጰዓድ ልጆች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም እስራኤላውያን የሚያገለግል ደንብ እንዲሆን ሲል “አንድ ሰው ወንድ ልጅ ሳይተካ ቢሞት ውርሱን ለሴት ልጁ አስተላልፉ” የሚል መመሪያ ለሙሴ ሰጠው። (ዘኍ. 27:6-8፤ ኢያሱ 17:1-6) ከዚያ በኋላ እንደ ሰለጰዓድ ልጆች ያለ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው እስራኤላውያን ሴቶች በሙሉ ከዚህ ዝግጅት ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።
15. (ሀ) ይሖዋ፣ ሕዝቡን በተለይም ረዳት የሌላቸውን የሚይዘው በምን መንገድ ነው? (ለ) ይሖዋ የማያዳላ አምላክ መሆኑን የሚያሳዩት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች የትኞቹ ናቸው?
15 ይህ እንዴት ያለ ደግነት የተንጸባረቀበትና ከአድልዎ ነፃ የሆነ ውሳኔ ነው! ይሖዋ የተሻለ ሁኔታ ለነበራቸው ሌሎች እስራኤላውያን እንደሚያደርገው ሁሉ ከጎናቸው የሚሆን ረዳት የሌላቸውን እነዚህን ሴቶችም በአክብሮት ይዟቸዋል። (መዝ. 68:5) ይሖዋ ያለውን አስደሳች ባሕርይ ይኸውም ሁሉንም አገልጋዮቹን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ የሚይዝ መሆኑን ከሚያሳዩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ይህ አንዱ ብቻ ነው።—1 ሳሙ. 16:1-13፤ ሥራ 10:30-35, 44-48
ይሖዋን መምሰል እንችላለን
16. አድልዎ የማድረግን ባሕርይ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 የማያዳሉ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? የማያዳሉ መሆን ሁለት ነገሮችን እንደሚያካትት አስታውስ። ሌሎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ መያዝ የምንችለው አመለካከታችን ከአድልዎ ነፃ ከሆነ ብቻ ነው። ማንኛችንም ብንሆን ሁሉንም ሰው እኩል እንደምንመለከትና እንደማናዳላ እናስብ ይሆናል። ይሁንና ብዙውን ጊዜ ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር እንደሚከብደን የታወቀ ነው። ታዲያ በዚህ ረገድ ምን ዓይነት ስም እንዳለን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ሰዎች ስለ እሱ ምን እንደሚሉ ለማወቅ በፈለገ ጊዜ የሚያምናቸውን ወዳጆቹን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” በማለት ጠይቋቸው ነበር። (ማቴ. 16:13, 14) አንተም ለምን እንዲህ አታደርግም? ያሉብህን ድክመቶች በሐቀኝነት ወደሚነግርህ አንድ ወዳጅህ ቀርበህ በዚህ ረገድ ማሻሻል ያለብህ ነገር እንዳለ ልትጠይቀው ትችላለህ። የአንድን ሰው ዘር፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ ወይም ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውን አይተህ አድልዎ የማድረግ አዝማሚያ እንዳለህ ወዳጅህ ከጠቆመህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? አመለካከትህን ማስተካከልና እንደ እሱ ሙሉ በሙሉ ከአድልዎ ነፃ መሆን እንድትችል እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ተማጸነው።—ማቴ. 7:7፤ ቆላ. 3:10, 11
17. የማናዳላ መሆናችንን በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን?
17 እኛም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በአክብሮት በመያዝና ለእነሱ ፍቅራዊ ደግነት በማሳየት የማያዳላውን ይሖዋን መምሰል እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ግብዣ በምናዘጋጅበት ወቅት ከእኛ የተለየ አስተዳደግ ያላቸውን እንዲሁም ድሆችንና ወላጆቻቸውን ወይም የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡትን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማካተት እንችላለን። (ገላትያ 2:10ን እና ያዕቆብ 1:27ን አንብብ።) ከዚህም ሌላ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ሥራ ስንካፈል፣ ከሌላ አገር የመጡትን ጨምሮ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ምሥራቹን እንሰብካለን። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን 600 በሚያህሉ ቋንቋዎች ማግኘት በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን። ይህ በእርግጥም የይሖዋ ድርጅት ከአድልዎ ነፃ መሆኑን የሚያሳይ ጉልህ ማስረጃ ነው!
18. ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብና የማያዳላ አምላክ መሆኑን እንደምታደንቅ በሕይወትህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
18 በእርግጥም ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብና የማያዳላ አምላክ መሆኑን በሚያሳዩት ምሳሌዎች ላይ ጊዜ ወስደን ስናሰላስል ለእሱ ያለን አድናቆት እየጨመረ ይሄዳል። አድናቆታችን መጨመሩ ደግሞ የይሖዋን ባሕርያት በማሳየት እሱን እንድንመስል እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮቻችንም ሆነ ምሥራቹን ከምንሰብክላቸው ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት እነዚህን ባሕርያት እንድናንጸባርቅ ሊያነሳሳን ይገባል።