በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለደስታችን ከእኛ ጋር አብረው የሚሠሩት’ ክርስቲያን ሽማግሌዎች

‘ለደስታችን ከእኛ ጋር አብረው የሚሠሩት’ ክርስቲያን ሽማግሌዎች

“እኛ ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።”—2 ቆሮ. 1:24

1. ጳውሎስ በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲደሰት ያደረገው ምንድን ነው?

ጊዜው 55 ዓ.ም. ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ የሚገኘው የወደብ ከተማ በሆነችው በጥሮአስ ነው። ጳውሎስ እዚያም ሆኖ በቆሮንቶስ ስላሉት ክርስቲያኖች ማሰቡን አላቋረጠም። በቆሮንቶስ በሚኖሩ ወንድሞች መካከል አለመግባባት እንዳለ በዚያው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በመስማቱ በጣም አዝኖ ነበር። በመሆኑም ከአባታዊነት ስሜት በመነሳት እነሱን ለማረም ደብዳቤ ላከላቸው። (1 ቆሮ. 1:11፤ 4:15) በተጨማሪም ስለ ወንድሞቹ ለማወቅ የሥራ ባልደረባው የሆነውን ቲቶን ወደ ቆሮንቶስ የላከው ሲሆን የእነሱን ዜና ይዞ ሲመለስ ጥሮአስ ላይ ሊያገኘው አስቦ ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ጉባኤ ስላለበት ሁኔታ ለመስማት የቲቶን መምጣት በጉጉት እየተጠባበቀ ነው። ሆኖም ቲቶ ሳይመጣ በመቅረቱ ጳውሎስ በጣም አዘነ። ታዲያ ጳውሎስ ምን ያደርግ ይሆን? በመርከብ ወደ መቄዶንያ ተጓዘ፤ በዚያም ቲቶን ሲያገኘው በጣም ተደሰተ። ቲቶ፣ በቆሮንቶስ ያሉ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ደብዳቤ ጥሩ ምላሽ እንደሰጡና እሱን ሊያዩት እንደናፈቁ ነገረው። ጳውሎስ ይህን ጥሩ ዜና ሲሰማ ‘ይበልጥ ተደሰተ።’—2 ቆሮ. 2:12, 13፤ 7:5-9

2. (ሀ) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ እምነትና ስለ ደስታ ምን ብሎ ጽፏል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሁለተኛ ደብዳቤ ጻፈላቸው። እንዲህ አላቸው፦ “ጸንታችሁ የቆማችሁት በራሳችሁ እምነት ስለሆነ እኛ ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር አብረን የምንሠራ ነን እንጂ በእምነታችሁ ላይ የምናዝ አይደለንም።” (2 ቆሮ. 1:24) ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? ይህ አባባል በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን ትርጉም አለው?

እምነታችንና ደስታችን

3. (ሀ) ጳውሎስ ‘ጸንታችሁ የቆማችሁት በራሳችሁ እምነት ነው’ ሲል ምን ማለቱ ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ሽማግሌዎች የጳውሎስን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?

3 ጳውሎስ የአምልኳችንን ሁለት ወሳኝ ገጽታዎች ይኸውም እምነትንና ደስታን ጠቅሷል። እምነትን አስመልክቶ ሲጽፍ “ጸንታችሁ  የቆማችሁት በራሳችሁ እምነት ስለሆነ . . . በእምነታችሁ ላይ የምናዝ አይደለንም” እንዳለ አስታውሱ። ጳውሎስ እንዲህ ብሎ መናገሩ የቆሮንቶስ ወንድሞች የጸኑት እሱን ወይም ሌላ ሰው ብለው ሳይሆን በአምላክ ላይ እምነት ስላላቸው እንደሆነ መገንዘቡን ያሳያል። በመሆኑም እምነታቸውን በተመለከተ ወንድሞቹን መቆጣጠር እንደሚያስፈልገው አልተሰማውም፤ ደግሞም እንዲህ የማድረግ ፍላጎት አልነበረውም። ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚፈልጉ ታማኝ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ተማምኖ ነበር። (2 ቆሮ. 2:3) በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም የወንድሞቻቸውን እምነትና አምላክን ለማገልገል የተነሳሱበትን ምክንያት ባለመጠራጠር የጳውሎስን ምሳሌ ይከተላሉ። (2 ተሰ. 3:4) ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ድርቅ ያሉ ሕጎችን ከማውጣት ይልቅ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶችና የይሖዋ ድርጅት በሚሰጠው አመራር ይታመናሉ። ደግሞም በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች በወንድሞቻቸው ‘እምነት ላይ የሚያዝዙ አይደሉም።’—1 ጴጥ. 5:2, 3

4. (ሀ) ጳውሎስ “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” ብሎ ሲጽፍ ምን ማለቱ ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

4 በተጨማሪም ጳውሎስ “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” በማለት ተናግሯል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ራሱንና የቅርብ የሥራ ባልደረቦቹን እየጠቀሰ ነበር። እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስነው ለምንድን ነው? ጳውሎስ በዚያው ደብዳቤ ላይ “እኛ ማለትም እኔ፣ ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ የሰበክንላችሁ” በማለት ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው ጊዜ ከሥራ ባልደረቦቹ መካከል ሁለቱን ጠቅሷል። (2 ቆሮ. 1:19) በተጨማሪም ጳውሎስ በደብዳቤዎቹ ላይ ‘አብረውኝ የሚሠሩ’ የሚለውን አገላለጽ ሲጠቀም ምንጊዜም የሚያመለክተው አጵሎስን፣ አቂላን፣ ጵርስቅላንና ቲቶን የመሰሉ የቅርብ የሥራ አጋሮቹን ነው። (ሮም 16:3፤ 1 ቆሮ. 3:6-9፤ 2 ቆሮ. 8:23) በመሆኑም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” ብሎ ሲናገር እሱና የሥራ ባልደረቦቹ፣ ሁሉም የጉባኤው አባላት ደስተኛ እንዲሆኑ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጫ መስጠቱ ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ ፍላጎት አላቸው። ወንድሞቻቸው ‘ይሖዋን በደስታ እንዲያገለግሉት’ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይፈልጋሉ።—መዝ. 100:2፤ ፊልጵ. 1:25

5. ለየትኛው ጥያቄ የተሰጠውን መልስ እንመረምራለን? በምንስ ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል?

5 በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ቀናተኛ ወንድሞችና እህቶች “አንድ ሽማግሌ ከነገራችሁ ወይም ካደረገላችሁ ነገር መካከል ይበልጥ ያስደሰታችሁ የትኛው ነው?” የሚል ጥያቄ በቅርብ ጊዜ ቀርቦላቸው ነበር። እነዚህ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሰጡትን ምላሽ እየመረመርን ስንሄድ እናንተ ብትሆኑ ኖሮ ምን መልስ ትሰጡ እንደነበረ እግረ መንገዳችሁን አስቡ። ከዚህም ባሻገር ሁላችንም በጉባኤያችን ውስጥ ደስታ እንዲሰፍን የበኩላችንን ሚና መጫወት የምንችለው እንዴት እንደሆነ አሰላስሉ። *

“የምንወዳትን ጰርሲስን ሰላም በሉልኝ”

6, 7. (ሀ) ሽማግሌዎች የኢየሱስን፣ የጳውሎስንና የሌሎች የአምላክ አገልጋዮችን ምሳሌ መከተል የሚችሉበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ወንድሞቻችን ስማቸውን አስታውሰን ስንጠራቸው ይበልጥ የሚደሰቱት ለምንድን ነው?

6 በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ ሽማግሌዎች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ስለሰጧቸው ደስታቸው እንደጨመረ ገልጸዋል። ሽማግሌዎች ይህን ማድረግ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ዳዊት፣ ኤሊሁና ኢየሱስ የተዉትን ምሳሌ መከተል ነው። (2 ሳሙኤል 9:6ንኢዮብ 33:1ን እና ሉቃስ 19:5ን አንብብ።) እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ሰዎችን በስማቸው በመጥራት ለእነሱ ያላቸውን ልባዊ አሳቢነት አሳይተዋል። ጳውሎስም ቢሆን የእምነት ባልንጀሮቹን ስም ማወቅና አስታውሶ መጥራት ያለውን ጥቅም ተገንዝቧል። ከደብዳቤዎቹ መካከል አንዱን የደመደመው ከ25 የሚበልጡ ወንድሞችንና እህቶችን በስማቸው ጠቅሶ ሰላምታ በመስጠት ነው፤ ከእነዚህ መካከል “የምንወዳትን ጰርሲስን ሰላም በሉልኝ”  በማለት የጠቀሳት እህት ትገኝበታለች።—ሮም 16:3-15

7 አንዳንድ ሽማግሌዎች፣ ስም ማስታወስ ይቸገራሉ። ያም ሆኖ በዚህ ረገድ ልባዊ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ የእምነት ባልንጀራቸውን ‘በእኔ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለህ’ ያሉት ያህል ነው። (ዘፀ. 33:17) በተለይ ሽማግሌዎች መጠበቂያ ግንብ ሲመሩ አሊያም ሌላ ክፍል ሲያቀርቡ ሐሳብ እንዲሰጡ የሚጋብዟቸውን ሰዎች በስማቸው የሚጠሯቸው ከሆነ የወንድሞቻቸው ደስታ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።—ከ⁠ዮሐንስ 10:3 ጋር አወዳድር።

“በጌታ ሥራ ብዙ የደከመችው”

8. ጳውሎስ የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ ከተከተለባቸው መንገዶች አንዱ የትኛው ነው?

8 ጳውሎስ ሌሎችን ከልቡ በማመስገንም አሳቢነት አሳይቷል፤ ይህ ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቹ ደስታ እንዲጨምር ከሚያደርጉ ዋና ዋና መንገዶች መካከል ሌላኛው ነው። በዚህም የተነሳ ለወንድሞቹ ደስታ ከእነሱ ጋር አብሮ እንደሚሠራ በጠቀሰበት ደብዳቤ ላይ “በእናንተ በጣም እኮራለሁ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 7:4) እነዚህ የምስጋና ቃላት የቆሮንቶስን ጉባኤ ወንድሞች በጣም እንዳስደሰቷቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ጳውሎስ ለሌሎች ጉባኤዎችም ተመሳሳይ የምስጋና ቃላት ተናግሯል። (ሮም 1:8፤ ፊልጵ. 1:3-5፤ 1 ተሰ. 1:8) እንዲያውም ለሮም ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለ ጰርሲስ ሲናገር “በጌታ ሥራ ብዙ የደከመችው” ብሏታል። (ሮም 16:12) ታማኝ የሆነችው ይህች እህት እነዚህን የአድናቆት ቃላት ስትሰማ ምን ያህል ተደስታ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል! ጳውሎስ ሌሎችን በማመስገን ረገድ የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ ተከትሏል።—ማርቆስ 1:9-11ን እና ዮሐንስ 1:47ን አንብብ፤ ራእይ 2:2, 13, 19

9. የምስጋና ቃላት መናገርም ሆነ መስማት የጉባኤው አባላት ደስታ እንዲጨምር የሚያደርገው እንዴት ነው?

9 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ለወንድሞቻቸው ያላቸውን አድናቆት በቃላት መግለጽ ያለውን አስፈላጊነት ይገነዘባሉ። (ምሳሌ 3:27፤ 15:23) አንድ ሽማግሌ እንዲህ ሲያደርግ ለእምነት ባልንጀራው ‘ያደረግከውን አስተውያለሁ። ስለ አንተም በጥልቅ አስባለሁ’ እያለው ነው። ወንድሞችና እህቶች ከሽማግሌዎች አንደበት እንዲህ ያለውን አድናቆት መስማት እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። በ50ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ አንዲት እህት እንደሚከተለው በማለት የተናገረችው ነገር የብዙዎችን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው፦ “በሥራ ቦታዬ የሚያመሰግነኝ ሰው የለም ማለት ይቻላል። አሳቢነት የሚባል ነገር የሌለበትና ፉክክር የበዛበት ስፍራ ነው። ስለዚህ አንድ ሽማግሌ በጉባኤ ውስጥ ያደረግኩትን ነገር ጠቅሶ ሲያመሰግነኝ መንፈሴ ይታደሳል፤ ብርታትም አገኛለሁ! የሰማዩ አባቴ እንደሚወደኝ ሆኖ ይሰማኛል።” ብቻውን ሁለት ልጆችን የሚያሳድግ አንድ ወንድምም ቢሆን ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶታል። በቅርቡ አንድ ሽማግሌ ለእሱ ያለውን ልባዊ አድናቆት ገልጾለት ነበር። በዚህ ጊዜ ወንድማችን ምን ተሰማው? “ሽማግሌው የተናገረው የአድናቆት ቃል ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል!” በማለት ተናግሯል። በእርግጥም አንድ ሽማግሌ የእምነት ባልንጀሮቹን ከልብ የሚያመሰግናቸው ከሆነ መንፈሳቸው የሚታደስ ከመሆኑም በላይ ደስታቸው ይጨምራል። ይህ ደግሞ በሕይወት መንገድ ላይ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ተጨማሪ ኃይል ስለሚሆናቸው “አይደክሙም።”—ኢሳ. 40:31

‘የአምላክን ጉባኤ ጠብቁ’

10, 11. (ሀ) ሽማግሌዎች የነህምያን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች በእረኝነት ጉብኝት ወቅት መንፈሳዊ ስጦታ ለማካፈል ምን ሊረዳቸው ይችላል?

10 ሽማግሌዎች ለወንድሞቻቸው አሳቢነት እንዳላቸው ከሚያሳዩባቸውና የጉባኤው ደስታ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ከሚያደርጉባቸው ወሳኝ መንገዶች መካከል ሌላኛው ምንድን ነው? ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን የጉባኤ አባላት ቅድሚያ ወስዶ መጠየቅ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 20:28ን አንብብ።) ሽማግሌዎች እንዲህ ሲያደርጉ በጥንት ዘመን የኖሩ መንፈሳዊ እረኞችን ምሳሌ እየተከተሉ ነው። ለምሳሌ ታማኝ የበላይ ተመልካች የሆነው ነህምያ አንዳንድ አይሁዳዊ ወንድሞቹ በመንፈሳዊ መድከማቸውን ሲያይ ያደረገውን ነገር እንመልከት። ነህምያ ወንድሞቹን ለማበረታታት እንደተነሳ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይናገራል። (ነህ. 4:14 የ1954 ትርጉም)  በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይፈልጋሉ። የእምነት ባልንጀሮቻቸው በእምነት እንዲጸኑ ለማድረግ ‘ይነሳሉ’ በሌላ አባባል ቅድሚያውን ይወስዳሉ። ሁኔታው አመቺ ከሆነ ቤታቸው ድረስ በመሄድ እንዲህ ያለውን ማበረታቻ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው በግለሰብ ደረጃ ይሰጣሉ። በእረኝነት ጉብኝት ወቅት ለወንድሞቻቸው “መንፈሳዊ ስጦታ” ያካፍላሉ። (ሮም 1:11) ታዲያ ሽማግሌዎች እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

11 ሽማግሌዎች የእረኝነት ጉብኝት ለማድረግ ከመነሳታቸው በፊት፣ ስለሚጠይቁት ግለሰብ ጊዜ ወስደው ማሰብ ይኖርባቸዋል። ግለሰቡ ምን ችግሮች አሉበት? ምን ሐሳብ ባካፍለው ሊታነጽ ይችላል? እሱ ካለበት ሁኔታ አንጻር ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነው የትኛው ጥቅስ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ነው? አንድ ሽማግሌ እንዲህ ያለ የታሰበበት እረኝነት ማድረጉ የመጣለትን ከመናገር ይልቅ ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያደርግ ያስችለዋል። ሽማግሌዎች በእረኝነት ጉብኝት ወቅት ወንድሞችና እህቶች የውስጣቸውን አውጥተው እንዲናገሩ በማድረግ በጥሞና ያዳምጧቸዋል። (ያዕ. 1:19) አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሽማግሌ ከልቡ ሲያዳምጠኝ በጣም እጽናናለሁ።”—ሉቃስ 8:18

አንድ ሽማግሌ ጥሩ ዝግጅት ማድረጉ በእረኝነት ጉብኝት ወቅት “መንፈሳዊ ስጦታ” ለማካፈል ያስችለዋል

12. በጉባኤ ውስጥ ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው? ለምንስ?

12 እረኝነት የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው? ጳውሎስ ‘ለመንጋው ሁሉ ተጠንቀቁ’ ሲል ክርስቲያን ሽማግሌዎችን አሳስቧል። አዎን፣ ሁሉም የጉባኤው አባላት ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል፤ ይህም ከዓመት እስከ ዓመት አገልግሎታቸውን በታማኝነት የሚፈጽሙ አስፋፊዎችንና አቅኚዎችን ይጨምራል። እነዚህ ክርስቲያኖች የመንፈሳዊ እረኞች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ያለ ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው ክርስቲያኖችም እንኳ ይህ ክፉ ሥርዓት የሚያሳድረውን ጫና መቋቋም ከአቅማቸው በላይ የሚሆንበት ጊዜ አለ። አንድ ጠንካራ የአምላክ አገልጋይም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ከእምነት አጋሩ ማበረታቻ እንደሚያስፈልገው መረዳት እንድንችል ንጉሥ ዳዊት በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት።

“አቢሳ . . . ዳዊትን ለመታደግ መጣ”

13. (ሀ) ይሽቢብኖብ ዳዊትን ለመግደል የትኛውን አጋጣሚ ለመጠቀም አስቦ ነበር? (ለ) አቢሳ ዳዊትን ያዳነው እንዴት ነው?

13 ወጣቱ ዳዊት ለንግሥና ከተቀባ ብዙም ሳይቆይ ከግዙፎቹ የራፋይም ዘሮች አንዱ ከሆነው ከጎልያድ  ጋር ፊት ለፊት ተጋጠመ። ከዚያም ደፋሩ ዳዊት ይህን ግዙፍ ሰው ገደለው። (1 ሳሙ. 17:4, 48-51፤ 1 ዜና 20:5, 8) ይሁንና ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ፣ ዳዊት ከፍልስጤማውያን ጋር እየተዋጋ ሳለ በጣም ግዙፍ ከሆነ ሌላ ሰው ጋር በድጋሚ ተጋጠመ። ይህ ሰው ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነው ይሽቢብኖብ ነው። (2 ሳሙ. 21:16) በዚህ ጊዜ ግን ዳዊት ከሞት የተረፈው ለጥቂት ነው። ዳዊት ድፍረት አጥቶ ይሆን? በፍጹም፤ በዚህ ወቅት በጣም ዝሎ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ዳዊትም . . . ደከመው” ይላል። ይሽቢብኖብ ዳዊት እንደደከመው ሲመለከት ‘ሊገድለው አሰበ።’ ይሁንና ይህ ግዙፍ ሰው በዳዊት ላይ መሣሪያ ከማንሳቱ በፊት “የጽሩያ ልጅ አቢሳ . . . ዳዊትን ለመታደግ መጣ፤ ፍልስጥኤማዊውንም ወግቶ ገደለው።” (2 ሳሙ. 21:15-17) ዳዊት አልቆለት ነበር! አቢሳ ሁኔታውን አስተውሎ በነፍሱ ስለደረሰለት ዳዊት በጣም አመስጋኝ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም! ታዲያ ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14. (ሀ) እንደ ጎልያድ ያሉ ችግሮችን መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ብርታታችንና ደስታችን እንዲመለስ የሚረዱን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

14 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች፣ ሰይጣንና ወኪሎቹ በመንገዳቸው ላይ ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢያስቀምጡም አገልግሎታቸውን ይፈጽማሉ። አንዳንዶቻችን ግዙፍ ከሆኑ ችግሮች ጋር ፊት ለፊት የተፋጠጥንባቸው ጊዜያት አሉ፤ ይሁንና በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ስለታመንን እነዚህን “ጎልያዶች” ማሸነፍ ችለናል። ያም ቢሆን ይህ ዓለም የሚያሳድርብንን ጫና ለማሸነፍ የምናደርገው ያልተቋረጠ ትግል አንዳንድ ጊዜ እንድንዝልና ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርገን ይችላል። በሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ ልንቋቋማቸው የምንችላቸው ነገሮች በዚህ ወቅት በመንፈሳዊ ‘ሊገድሉን’ ይችላሉ። በብዙዎች ሕይወት እንደሚታየው፣ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሽማግሌዎች የሚያደርጉልን ወቅታዊ እርዳታ ደስታችንና ብርታታችን እንደገና እንዲመለስ ያደርጋል። በ60ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ አንዲት አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ከተወሰነ ጊዜ በፊት ጥሩ ስሜት አይሰማኝም ነበር፤ እንዲሁም አገልግሎት መውጣት አድካሚ ሆኖብኝ ነበር። ከዚያም አንድ ሽማግሌ ኃይሌ እንደተሟጠጠ ስለተገነዘበ ጠጋ ብሎ አነጋገረኝ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የሚያንጽ ውይይት አደረግን። የሰጠኝን ምክር በሥራ ላይ ማዋሌ ጠቅሞኛል።” አክላም “ይህ ሽማግሌ መድከሜን አስተውሎ እኔን ለመርዳት መነሳሳቱ አፍቃሪ እንደሆነ ያሳያል!” ብላለች። ሁኔታችንን የሚከታተሉና ልክ እንደ አቢሳ እኛን ‘ለመታደግ’ ዝግጁ የሆኑ አፍቃሪ ሽማግሌዎች እንዳሉ ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው?

“ለእናንተ ያለኝን . . . ፍቅር እንድታውቁ ነው”

15, 16. (ሀ) ጳውሎስ በእምነት ባልንጀሮቹ በጣም ይወደድ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) አሳቢ የሆኑትን የጉባኤ ሽማግሌዎቻችንን የምንወዳቸው ለምንድን ነው?

15 እረኝነት በጣም ከባድ ሥራ ነው። ሽማግሌዎች ስለ ወንድሞቻቸው ሲያስቡና ሲጸልዩ ወይም የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በመንፈሳዊ ለመርዳት ሲሉ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩበት ጊዜ አለ። (2 ቆሮ. 11:27, 28) ያም ቢሆን ሽማግሌዎች ልክ እንደ ጳውሎስ ኃላፊነታቸውን በደስታ ስሜት ሙሉ በሙሉ ይወጣሉ። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ስለ ነፍሳችሁ ያለኝን ሁሉ፣ ራሴንም ጭምር ብሰጥ እጅግ ደስ ይለኛል።” (2 ቆሮ. 12:15) በእርግጥም ጳውሎስ ለወንድሞቹ ካለው ፍቅር የተነሳ እነሱን ለማበረታታት ራሱን ሙሉ በሙሉ ሰጥቶ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 2:4ን አንብብ፤ ፊልጵ. 2:17፤ 1 ተሰ. 2:8) ጳውሎስ በወንድሞቹ ዘንድ በጣም የተወደደ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም!—ሥራ 20:31-38

16 እኛ የአምላክ አገልጋዮችም አሳቢ የሆኑ ክርስቲያን ሽማግሌዎቻችንን እንወዳቸዋለን፤ እንዲሁም እነሱን ስለሰጠን በግለሰብ ደረጃ ይሖዋን በጸሎት ለማመስገን እንገፋፋለን። ለእያንዳንዳችን ትኩረት በመስጠት ደስታችንን ይጨምሩልናል። በሚያደርጉልን የእረኝነት ጉብኝት እንበረታታለን። በተጨማሪም ይህ ዓለም የሚያሳድርብን ተጽዕኖ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ሲሰማን ወዲያውኑ ሊረዱን ዝግጁ በመሆናቸው አመስጋኝ ነን። በእርግጥም እንዲህ ያሉ ትጉህ ሽማግሌዎች ‘ለደስታችን ከእኛ ጋር አብረው የሚሠሩ’ ናቸው።

^ စာပိုဒ်၊ 5 እነዚሁ ወንድሞችና እህቶች “ሽማግሌዎች የትኛው ባሕርይ ቢኖራቸው ይበልጥ ትመርጣላችሁ?” የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር። የሚገርመው አብዛኞቹ የሰጡት መልስ “የሚቀረቡ ቢሆኑ” የሚል ነው። በጣም አስፈላጊ የሆነው ይህ ባሕርይ ወደፊት በሚወጣ እትም ላይ ይብራራል።