ይሖዋ ወደ እውነተኛው ነፃነት ይምራችሁ!
ይሖዋ ወደ እውነተኛው ነፃነት ይምራችሁ!
“ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ በትኩረት [ተመልከቱ]።”—ያዕ. 1:25
ልታብራራ ትችላለህ?
ወደ እውነተኛ ነፃነት የሚመራው ሕግ የትኛው ነው? ከዚህ ሕግ ጥቅም ማግኘት የሚችሉትስ እነማን ናቸው?
እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት ቁልፉ ምንድን ነው?
ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ የሚጓዙ ሰዎች ወደፊት ምን ዓይነት ነፃነት ያገኛሉ?
1, 2. (ሀ) ከነፃነት ጋር በተያያዘ በዓለም ላይ የሚታየው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ? (ለ) የይሖዋ አገልጋዮች ከፊታቸው ምን ዓይነት ነፃነት ይጠብቃቸዋል?
የምንኖረው ስግብግብነት፣ ሕገ ወጥነትና ዓመፅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ባለበት ዘመን ውስጥ ነው። (2 ጢሞ. 3:1-5) በዚህም ምክንያት መንግሥታት ተጨማሪ ሕጎችን ለማውጣት፣ የፖሊስ ኃይላቸውን ለማጠናከርና የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ለመግጠም ተገደዋል። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ግለሰቦች ደኅንነታቸውን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ ሲሉ በቤታቸው ውስጥ የአደጋ ጥሪ የሚያሰሙ መሣሪያዎችን ይገጥማሉ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ቁልፎችን ይጠቀማሉ አልፎ ተርፎም የኤሌክትሪክ የአጥር ሽቦዎችን ይተክላሉ። ብዙዎች ደግሞ ከመሸ በኋላ ከቤታቸው መውጣት ይፈራሉ፤ እንዲሁም ልጆቻቸው፣ የሚጠብቃቸው ሳይኖር በቀንም ይሁን በምሽት ውጪ እንዲጫወቱ አይፈቅዱላቸውም። ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው ነፃነት ብርቅ እየሆነ መጥቷል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ የሚሻሻል አይመስልም።
2 በኤደን ገነት ውስጥ ስለተከሰተው ነገር መለስ ብለን ስናስብ በወቅቱ ሰይጣን፣ እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት ቁልፉ ይሖዋን ከመታዘዝ ይልቅ ራስን በራስ መምራት እንደሆነ ተናግሮ እንደነበር እናስታውሳለን። ሰይጣን እንዲህ ያለውን ዓይን ያወጣ ውሸት መናገሩ ምን ያህል ተንኮለኛና ጨካኝ እንደሆነ ያሳያል! ሰዎች የአምላክን መመሪያ ችላ በማለት በራሳቸው መንገድ መሄዳቸውን በቀጠሉ ቁጥር መላው ኅብረተሰብ ይበልጥ እየተሠቃየ ይሄዳል። እየተባባሰ የሚሄደው ይህ ሁኔታ ደግሞ የይሖዋ አገልጋዮችንም ይነካል። ያም ቢሆን ከኃጢአትና ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥተን መጽሐፍ ቅዱስ ‘የአምላክ ልጆች ክብራማ ነፃነት’ በማለት የሚጠራውን ሕይወት የማጣጣም ተስፋ አለን። (ሮም 8:21) እንዲያውም ይሖዋ አገልጋዮቹን ለዚህ ነፃነት ከወዲሁ እያዘጋጃቸው ነው። እንዴት?
3. ይሖዋ ለክርስቶስ ተከታዮች ምን ዓይነት ሕግ ሰጥቷቸዋል? የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ የሚረዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ ‘ነፃ የሚያወጣው ፍጹም ሕግ’ በማለት የተናገረው ሐሳብ ነው። (ያዕቆብ 1:25ን አንብብ።) ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሕግን የሚያያይዙት ከእገዳ ጋር እንጂ ከነፃነት ጋር አይደለም። ታዲያ ‘ነፃ የሚያወጣው ፍጹም ሕግ’ ምንድን ነው? ይህ ሕግ ነፃ የሚያወጣንስ እንዴት ነው?
ነፃ የሚያወጣው ሕግ
4. ‘ነፃ የሚያወጣው ፍጹም ሕግ’ የተባለው ምንድን ነው? ከዚህ ሕግ፣ ጥቅም ማግኘት የሚችሉትስ እነማን ናቸው?
4 ‘ነፃ የሚያወጣው ፍጹም ሕግ’ የተባለው የሙሴ ሕግ አይደለም፤ ምክንያቱም የሙሴ ሕግ፣ ሕግ ተላላፊነትን ይፋ ያወጣ ከመሆኑም ሌላ በክርስቶስ አማካኝነት ፍጻሜውን አግኝቷል። (ማቴ. 5:17፤ ገላ. 3:19) ታዲያ ያዕቆብ እየተናገረ የነበረው ስለ የትኛው ሕግ ነው? ያዕቆብ ስለዚህ ሕግ ሲናገር “የክርስቶስን ሕግ” በአእምሮው ይዞ ነበር፤ የክርስቶስ ሕግ ደግሞ “የእምነት ሕግ” እና ‘ነፃ የሆኑ ሰዎች ሕግ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ገላ. 6:2፤ ሮም 3:27፤ ያዕ. 2:12) በመሆኑም ‘ፍጹሙ ሕግ’ ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቃቸውን ነገሮች በሙሉ ያካትታል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ “ሌሎች በጎች” ከዚህ ሕግ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።—ዮሐ. 10:16
5. ነፃ የሚያወጣው ሕግ ከባድ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
5 ‘ፍጹሙ ሕግ’ ብዙ አገሮች እንደሚያወጡት ሕግ የተወሳሰበ ወይም ከባድ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ቀላልና መሠረታዊ የሆኑ መመሪያዎችን የያዘ ነው። (1 ዮሐ. 5:3) ኢየሱስ “ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነው” ብሏል። (ማቴ. 11:29, 30) ከዚህም በላይ ‘ፍጹሙን ሕግ’ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ትእዛዞችን ወይም ቅጣቶችን መደርደር አያስፈልግም፤ ምክንያቱም ይህ ሕግ በፍቅር ላይ የተመሠረተና በድንጋይ ላይ ሳይሆን በሰዎች አእምሮና ልብ ውስጥ የተጻፈ ነው።—ዕብራውያን 8:6, 10ን አንብብ።
‘ፍጹሙ ሕግ’ ነፃ የሚያወጣን እንዴት ነው?
6, 7. ስለ ይሖዋ መሥፈርቶች ምን ማለት ይቻላል? ነፃ የሚያወጣው ሕግ እውነተኛ ነፃነት ያስገኛል የምንለው ለምንድን ነው?
6 ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ላላቸው ፍጡሮቹ ያወጣቸው ሕጎች ለእነሱ ጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ ጥበቃ ያስገኙላቸዋል። ኃይልንና ቁስ አካልን የሚቆጣጠሩትን የተፈጥሮ ሕጎች እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይችላል። ሰዎች ለእነዚህ ሕጎች በመገዛታቸው አያጉረመርሙም። እንዲያውም የተፈጥሮ ሕጎች ለደኅንነታቸው ወሳኝ ነገሮች እንደሆኑ ስለሚያውቁ እነዚህ ሕጎች በመኖራቸው ይደሰታሉ። በተመሳሳይም በክርስቶስ “ፍጹም ሕግ” ውስጥ የተካተቱት ይሖዋ ያወጣቸው መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ መሥፈርቶች ለሰው ልጆች ጠቃሚ ናቸው።
7 ነፃ የሚያወጣው ሕግ ጥበቃ የሚያስገኝልን ከመሆኑም ሌላ ራሳችንን ሳንጎዳ ወይም የሌሎችን መብትና ነፃነት ሳንጋፋ ተገቢ የሆኑ ፍላጎቶቻችንን በሙሉ እንድናረካ ያስችለናል። በመሆኑም ያሻንን ነገር ለማድረግ የሚያስችል እውነተኛ ነፃነት አለን የሚባለው ከይሖዋ ባሕርያትና መሥፈርቶች ጋር የሚስማሙ ትክክለኛ ፍላጎቶችን ማዳበር ከቻልን ብቻ ነው። በሌላ አባባል ይሖዋ የሚወድደውን መውደድንና የሚጠላውን መጥላትን መማር ይኖርብናል፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ነፃ የሚያወጣው ሕግ ይረዳናል።—አሞጽ 5:15
8, 9. ነፃ የሚያወጣውን ሕግ በጥብቅ የሚከተሉ ሰዎች ምን ጥቅም ያገኛሉ? ምሳሌ ስጥ።
8 ፍጹማን ባለመሆናችን መጥፎ ፍላጎቶችን መዋጋት ይኖርብናል። ያም ሆኖ ነፃ የሚያወጣውን ሕግ በጥብቅ ለመከተል የምንጥር ከሆነ በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ይህ ሕግ ነፃ የማውጣት ኃይል እንዳለው በራሳችን ሕይወት ማየት እንችላለን። የሚከተለው ተሞክሮ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል፦ የትንባሆ ሱስ ያለበት ጄይ የተባለ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይጀምራል። ይህ ልማዱ አምላክን እንደማያስደስተው ሲገነዘብ ማጨሱን ለማቆም ውሳኔ ማድረግ ነበረበት። በዚህ ጊዜ ጄይ ምን ያደርግ ይሆን? ሥጋዊ ፍላጎቶቹን ማርካቱን ይቀጥላል ወይስ ለይሖዋ ፈቃድ ይገዛል? አጭስ አጭስ የሚል ስሜት ቢታገለውም አምላክን ለማገልገል በመምረጥ ጥበበኛ መሆኑን አሳይቷል። ጄይ ከዚህ ሱስ ከተላቀቀ በኋላ ምን ተሰማው? “ከፍተኛ ደስታና ነፃነት ተሰማኝ” በማለት ተናግሯል።
9 ሰዎች ‘በሥጋዊ ነገር ላይ እንዲያተኩሩ’ የሚያደርገው ዓለም የሚሰጠው ነፃነት በእርግጥም ባርነት እንደሆነ በሌላ በኩል ደግሞ “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ [እንድናተኩር]” የሚያደርገን ይሖዋ የሚሰጠን ነፃነት “ሕይወትና ሰላም” እንደሚያስገኝ ጄይ ተገንዝቧል። ሮም 8:5, 6) ጄይ ባሪያ አድርጎ ከያዘው ሱሱ ለመላቀቅ ጥንካሬ ያገኘው እንዴት ነው? ይህን ጥንካሬ ያገኘው ከራሱ ሳይሆን ከአምላክ ነው። ጄይ እንዲህ ይላል፦ “አዘውትሬ መጽሐፍ ቅዱስን አጠና፣ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት እጸልይ እንዲሁም የክርስቲያን ጉባኤ የሚሰጠኝን ፍቅራዊ ድጋፍ በደስታ እቀበል ነበር።” ሁላችንም ቢሆን በእነዚህ ዝግጅቶች በመጠቀም እውነተኛ ነፃነት ማግኘት እንችላለን። እነዚህ ዝግጅቶች የሚጠቅሙን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
(የአምላክን ቃል በትኩረት ተመልከቱ
10. የአምላክን ቃል ‘በትኩረት መመልከት’ ሲባል ምን ማለት ነው?
10 ያዕቆብ 1:25 በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ በትኩረት የሚመለከትና በዚያም የሚጸና ሰው . . . ይህን በማድረጉ ደስተኛ ይሆናል።” ‘በትኩረት መመልከት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አንድን ነገር በደንብ ለማየት ወደፊት ዘንበል ማለት” የሚል ፍቺ የተሰጠው ሲሆን ትክ ብሎ ለማየት የሚደረግ ጥረትን ያመለክታል። እንግዲያው፣ ነፃ የሚያወጣው ሕግ በአስተሳሰባችንና በልባችን ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር የምንፈልግ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናትና ባነበብነው ነገር ላይ በጸሎት ጭምር በማሰላሰል የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል።—1 ጢሞ. 4:15
11, 12. (ሀ) ኢየሱስ እውነትን የሕይወታችን ክፍል ማድረጋችን አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ከላይ ያለው ሥዕላዊ መግለጫ እንደሚያሳየው በተለይ ወጣቶች ከየትኞቹ አደጋዎች ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል?
11 የአምላክን ቃል ከማጥናት ባለፈ ያጠናነውን ነገር በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ‘መጽናት’ ይኖርብናል፤ እንዲህ ስናደርግ እውነት የሕይወታችን ክፍል ይሆናል። ኢየሱስ በእሱ ለሚያምኑ አንዳንድ ተከታዮቹ እንዲህ በማለት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ ነግሯቸዋል፦ “በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ ዮሐ. 8:31, 32) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ከሆነ ‘ማወቅ’ የሚለው ቃል ‘አንድ ሰው ያወቀው ነገር ያለውን ዋጋ ወይም ጥቅም’ ሲረዳ የሚሰማውን የአድናቆት ስሜትም ሊያመለክት ይችላል። በመሆኑም እውነትን ሙሉ በሙሉ አውቀናል ሊባል የሚችለው እውነትን የሕይወታችን ክፍል ስናደርገው ነው። በዚህ ጊዜ “የአምላክ ቃል” በውስጣችን ‘እየሠራ ነው’ ብለን መናገር እንችላለን፤ የአምላክ ቃል ደግሞ ባሕርያችንን በመቅረጽ የሰማዩን አባታችንን ይበልጥ እየመሰልን እንድንሄድ ያደርገናል።—1 ተሰ. 2:13
እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።” (12 እስቲ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በእርግጥ እውነትን አውቃለሁ? የሕይወቴስ ክፍል አድርጌዋለሁ? ወይስ ዓለም የሚሰጣቸውን አንዳንድ “ነፃነቶች” ለማግኘት እጓጓለሁ?’ በእውነት ቤት ያደገች አንዲት እህት የወጣትነት ጊዜዋን አስታውሳ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “እውነት ውስጥ ስታድጉ ስለ ይሖዋ ከልጅነታችሁ ጀምሮ ትማራላችሁ። እኔ ግን ይሖዋን አውቀዋለሁ ማለት አልችልም ነበር። የሚጠላቸውን ነገሮች አልጠላም ነበር። የማደርገው ነገር እሱን ሊያስደስተው ወይም ሊያሳዝነው እንደሚችል አይሰማኝም ነበር። ችግር ሲያጋጥመኝ ወደ እሱ ዞር የማለት ልማድ አልነበረኝም። የምደገፈው በራሴ ማስተዋል የነበረ ሲሆን እንዲህ ማድረግ ሞኝነት እንደሆነ የገባኝ አሁን ነው፤ ምክንያቱም ምንም ነገር አላውቅም ነበር።” ደስ የሚለው ነገር ይህች እህት ከጊዜ በኋላ አስተሳሰቧ ስህተት እንደሆነ በመገንዘቧ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ችላለች። እንዲያውም ዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀምራለች።
መንፈስ ቅዱስ ነፃ ያወጣችኋል
13. የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነፃነት ያለው ሕይወት ለመምራት የሚረዳን እንዴት ነው?
13 ሁለተኛ ቆሮንቶስ 3:17 “የይሖዋ መንፈስ ባለበት . . . ነፃነት አለ” ይላል። ለመሆኑ መንፈስ ቅዱስ ነፃነት ያለው ሕይወት ለመምራት የሚረዳን እንዴት ነው? መንፈስ ቅዱስ በብዙ መንገዶች ሊረዳን ቢችልም አንደኛው መንገድ፣ ነፃነት ያለው ሕይወት ለመምራት የሚረዱንን ባሕርያትን እንድናዳብር ማስቻሉ ነው። እነዚህም “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት [እና] ራስን መግዛት” ናቸው። (ገላ. 5:22, 23) ሰዎች እነዚህን ባሕርያት በተለይ ደግሞ ፍቅርን የማያንጸባርቁ ከሆነ ማንኛውም ኅብረተሰብ እውነተኛ ነፃነት ሊኖረው አይችልም፤ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የሚታየው ነገር የዚህን እውነተኝነት ያረጋግጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ከዘረዘረ በኋላ “እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚከለክል ሕግ የለም” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው። ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? የአምላክ መንፈስ ፍሬ በሰዎች ውስጥ እድገት እንዳያደርግ ሊገታው የሚችል ምንም ዓይነት ሕግ እንደሌለ መጥቀሱ ነበር። (ገላ. 5:18) ደግሞስ እንዲህ ያለውን ሕግ ማውጣት ምን ጥቅም አለው? ይሖዋ፣ ምንጊዜም የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያት ማዳበራችንን እንድንቀጥልና እነዚህን ባሕርያት ያለ ምንም ገደብ እንድናንጸባርቅ ይፈልጋል።
14. የዓለም መንፈስ፣ ሰዎችን ባሪያ የሚያደርገው እንዴት ነው?
14 የዓለም መንፈስ የሚያማልላቸውና የሥጋቸውን ምኞት እንደ ልብ የሚፈጽሙ ሰዎች ነፃነት ያለው ሕይወት እንደሚመሩ ሆኖ ይሰማቸዋል። (2 ጴጥሮስ 2:18, 19ን አንብብ።) እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው። እንዲያውም መጥፎ ፍላጎቶቻቸውንና ባሕርያቸውን ለማስወገድ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕጎችና መመሪያዎች የሚያስፈልጓቸው እነሱ ናቸው። ጳውሎስ “ሕግ የሚታወጀው ለጻድቅ ሰው ሳይሆን ሕግ ለሚተላለፉና ለዓመፀኞች” እንደሆነ ተናግሯል። (1 ጢሞ. 1:9, 10) በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች ‘የሥጋቸውን ፈቃድ ለማድረግ’ ያደሩ በመሆናቸው ጨካኝ ጌታ ለሆነው ለኃጢአት ባሮች ሆነዋል። (ኤፌ. 2:1-3) በሌላ አባባል እነዚህ ሰዎች ማር ወደተቀመጠበት ዕቃ ዘው ብለው እንደሚገቡ ነፍሳት ናቸው። ማሩን ለመብላት ከመጓጓታቸው የተነሳ ዕቃው ውስጥ ሰፍ ብለው ቢገቡም መውጣት ግን አይችሉም።—ያዕ. 1:14, 15
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው ነፃነት
15, 16. ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ኅብረት መፍጠራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ከወንድሞች ጋር መሆን ምን ዓይነት ነፃነት ያስገኛል?
15 ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ኅብረት መፍጠር ጀመርክ ማለት ከሰዎች ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ተብሎ በተቋቋመ ማኅበር ውስጥ ታቀፍክ ማለት አይደለም። ዮሐ. 6:44) ይሖዋ የሳበህ ለምንድን ነው? ጻድቅና አምላክን የምትፈራ ሰው በመሆንህ ነው? “በፍጹም!” ብለህ ትመልስ ይሆናል። ታዲያ አምላክ በአንተ ውስጥ የተመለከተው ነገር ምንድን ነው? ነፃ የሚያወጣውን ሕግ ለመከተልና እሱ በደግነት የሚሰጠውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆነ ልብ እንዳለህ ተመልክቶ ነው። አምላክ በጉባኤው አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብ እንድታገኝና ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ብሎም ከአጉል እምነቶች ነፃ እንድትሆን በማድረግ እንዲሁም የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያት ማዳበር የምትችለው እንዴት እንደሆነ በማስተማር የልብህን ፍላጎት አርክቶልሃል። (ኤፌሶን 4:22-24ን አንብብ።) በዚህም የተነሳ በዓለም ላይ “ነፃ የሆኑ ሰዎች” ተብለው ሊጠሩ ከሚችሉ ብቸኛ ሕዝቦች መካከል የመቆጠር መብት አግኝተሃል።—ያዕ. 2:12
ከዚህ ይልቅ ወደ ጉባኤው የመጣኸው ይሖዋ ስለሳበህ ነው። (16 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ይሖዋን ከልባቸው ከሚወዱ ሕዝቦች ጋር ስትሆን ፍርሃት ይሰማሃል? አሁንም አሁንም ዞር እያልክ በጥርጣሬ ዙሪያህን ታማትራለህ? በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከወንድሞች ጋር ስትጫወት ንብረትህ እንዳይሰረቅ በመፍራት ዕቃዎችህን በዓይነ ቁራኛ ትከታተላለህ? በፍጹም! እንዲያውም በአዳራሹ ውስጥ ዘና ብለህ በነፃነት ትንቀሳቀሳለህ። በዓለማዊ ዝግጅቶች ላይ ስትገኝ እንዲህ ይሰማሃል? እንደማይሰማህ ግልጽ ነው! በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያገኘነው ነፃነት ወደፊት ለምናገኘው ታላቅ ነፃነት ቅምሻ ነው።
‘የአምላክ ልጆች ክብራማ ነፃነት’
17. የሰው ልጆች የሚያገኙት ነፃነት ‘ከአምላክ ልጆች መገለጥ’ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
17 ጳውሎስ፣ ይሖዋ በምድር ላይ ለሚኖሩ አገልጋዮቹ ስላዘጋጀው ነፃነት ሲናገር “ፍጥረት የአምላክን ልጆች መገለጥ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው” በማለት ጽፏል። አክሎም “ፍጥረት ራሱ . . . ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” እንደሚያገኝ ተናግሯል። (ሮም 8:19-21) “ፍጥረት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በመንፈስ የተቀቡት የአምላክ ልጆች ‘በመገለጣቸው’ ምክንያት ጥቅም የሚያገኙትን ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ነው። የአምላክ “ልጆች” የሚገለጡት ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ በሚሄዱበት ጊዜ ነው፤ በዚህ ወቅት ከክርስቶስ ጋር በመሆን ክፉዎችን ከምድረ ገጽ የሚያጠፉ ሲሆን ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦችን’ ደግሞ ወደ አዲሱ ሥርዓት ያስገባሉ።—ራእይ 7:9, 14
18. ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ምን ተጨማሪ ነፃነት ያገኛሉ? በመጨረሻስ ምን ዓይነት ነፃነት ያገኛሉ?
18 በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ተጽዕኖ ነፃ ስለሚሆኑ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ነፃነት ያገኛሉ። (ራእይ 20:1-3) ያ ወቅት እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል! ከዚያም ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑት 144,000ዎቹ፣ በቤዛዊ መሥዋዕቱ ተጠቅመው የአዳም ኃጢአትና አለፍጽምና ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ የሰው ልጆችን ነፃ ማውጣታቸውን ይቀጥላሉ። (ራእይ 5:9, 10) በመጨረሻም ከኃጢአት ነፃ የወጡት ሰዎች ታማኝነታቸው ይፈተናል፤ በኋላም ታዛዥ መሆናቸውን ያስመሠከሩት የሰው ልጆች ይሖዋ መጀመሪያ ለሰው ዘር ያሰበውን ፍጹም ነፃነት ማለትም “የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” ያገኛሉ። እስቲ አስቡት! ከዚያ ወዲህ በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ አበሳችንን ማየት አያስፈልገንም፤ ምክንያቱም ሁለመናችን ፍጹም ይሆናል፤ እንዲሁም የአምላክን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መልኩ ማንጸባረቅ እንችላለን።
19. ወደ እውነተኛው ነፃነት በሚወስደው ጎዳና ላይ መጓዛችንን ለመቀጠል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
19 “የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” በጉጉት እየተጠባበቅክ ነው? ‘አዎ’ ብለህ እንደምትመልስ ጥርጥር የለውም፤ እንግዲያው አእምሮህንም ሆነ ልብህን የሚመራው ‘ነፃ የሚያወጣው ፍጹሙ ሕግ’ ይሁን። ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት አጥና። በእውነት በመመላለስ እውነትን የራስህ አድርግ። መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጸልይ። ከክርስቲያን ጉባኤና ይሖዋ ከሚያዘጋጅልህ መንፈሳዊ ምግብ ሙሉ በሙሉ ተጠቀም። ሰይጣን የአምላክ ሕጎች ከሚገባው በላይ ጥብቅ እንደሆኑ እንድታስብ በማድረግ ልክ እንደ ሔዋን እንዳያታልልህ ተጠንቀቅ። ዲያብሎስ መሰሪ እንደሆነ መዘንጋት አይኖርብህም። ይሁንና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው “የእሱን ዕቅድ እናውቀዋለን።”—2 ቆሮ. 2:11
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዓለም የሚሰጣቸውን አንዳንድ “ነፃነቶች” ለማግኘት እጓጓለሁ?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነትን የሕይወቴ ክፍል አድርጌዋለሁ?